Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ባለፉት ሁለት ዓመታት አንዣበው የነበሩ በጣም ዘረኛ የሆኑ አመለካከቶች በአገሪቱ ጤናማ አየር እንዳይሸት አድርገው ነበር››

አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አዲሱ አምባሳደር

አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡ የደርግ መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)፣ ደርግ ከወደቀ በኋላ ደግሞ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በተባለው ውስጥ ሆነው ታግለዋል፡፡ ከድል በኋላም በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አምባሳደር ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ የመጨረሻው ኃላፊነታቸው የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ነበሩ፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ በኦርጋናይዜሽናል ሊደርሽፕ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በመጪው መስከረም መጨረሻ በአሜሪካ የአምባሳደርነት ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሎች መካከል ተፈጥሮ ስለነበረው የአስተዳደራዊ ወሰን ግጭት፣ ስለሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችና በአምባሳደርነታቸው ወቅት በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውያን (ዳያስፖራ) ጋር ተግባብተው ለመሥራት  ስለያዙት ዕቅድና ተያያዥ ጉዳዩችን በተመለከተ ከነአምን አሸናፊና ከዘመኑ ተናኘ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡  

ሪፖርተር፡- በቅድሚያ ለዚህ ቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡ እርስዎ በሚኒስትርና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ስለዚህ ሹመት የተሰማዎት ምንድነው? ከፖለቲከኝነት ገለል ማለት ነው? ወይስ እንደ አዲስ ሥራ ለመጀመር መንቀሳቀስ ነው? ከሚኒስትርነት ወደ አምባሳደርነት ሲሾሙ ምንድነው የተሰማዎት?

አምባሳደር ካሳ፡- ዕድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ፡፡ እኔ ወደ ትግል ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በጣም ብዙ የሥራ ቦታዎች ላይ ሠርቻለሁ፡፡ እነዚህ ሥራዎች አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡ ዓላማቸው ተደምሮ ግን አንድ ነበር፡፡ መንግሥት ከሆንንበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ብንወስድ አስተዳደርና ፀጥታ ወይም ሴኩሪቲ ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ መከላከያ ላይ ሠርቻለሁ፣ ግብርና ላይ ሠርቻለሁ፣ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ላይ ሠርቻለሁ፣ አፈ ጉባዔ ሆኜ የአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በቅርብ ጊዜ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ እንዲህ እያልን ብንቆጥራቸው በጣም በርካታ የሥራ መስኮች አሉ፡፡ ሁሉም ግን አገርና ሕዝብን ማገልገል ነበር፡፡ እኔ አሁን በዲፕሎማሲው መስክ የመጣውን ኃላፊነት ከዚህ ነጥዬ አላየውም፡፡ ልዩነቱ የበፊቱ ከሕዝቡና ከአገሪቱ ችግር ጋር በቀጥታና እዚያው አንድ ቦታ ሆነህ ነው የምትሠራው፡፡ ያኛው ደግሞ ለአገር ብትሠራም ከአገሪቱ ራቅ ብለህ ነው፡፡ በአገሪቱ አጀንዳ ውስጥ ያለ በሌላ አገር ውስጥ ሆነህ የምትሠራው ብቻ መሆኑ ነው ልዩነቱ፡፡ እኔ ለመታገልና ፖለቲከኛ ለመሆን ስወስን ነው ምርጫዬ የተወሰነው፡፡ ከዚያ በኃላ ያለው የጋራ ኃላፊነትና የጋራ ሥምሪት ነው፡፡ በምርጫችን ማናችንም ተመድበን አናውቅም፡፡ ስለዚህ ለእኔ አዲስ ነገር የለውም ማለት ነው፡፡ ልዩነቱ የሚሆነው አዲስ ሥምሪት መሆኑና አዲስ ግንባር መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎ አምባሳደር ሆኖ መሾምን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር፡፡ በአንድ ወገን ጥሩ በማለት፣ በተለይ ከአገሪቷ ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ካላቸው አገሮች ጋር በፖለቲካው መስክ ብዙ ልምድ ያላቸውን አምባሳደሮች መላክ ይጠቅማል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የለም ፖለቲከኞችን ገለል ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ካሳ፡- የተለያዩ አስተያየቶችና ሐሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እውነታው ግን ያን ያህል ሰው በሚያስበው መንገድ የተደረገ ነው ብዬ አልወስድም፡፡ የማውቀውም እሱን አይደለም የሚናገረው፡፡ አሜሪካም ሆነች ሌሎቹ አገሮች ለአገራችን በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲው፣ በሴኩሪቲውና በሌሎችም፡፡ አሜሪካ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት አካባቢ በመሆኑ ሕይወታቸው ከአገራችን ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው፡፡ አሁን በአገራችን ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከሌሎቹ አገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነት መጠናከር ጠቀሜታው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ ሊታይ የሚችልበት ዕድል ያለን ይመስለኛል፡፡ ብዙ ምርቶች አሉ፡፡ አሁን ገበያ የሚፈልጉ በርካታ ናቸው፡፡ ኢንቨስትመንት ከዚያ በላይ ከፍ ያለ ትኩረት የሚፈልግ ነው እስካሁን አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ካደረገችው ጥረት በላይ የምንፈልገውም የምንፈለግበትም ጊዜ ስለሆነ አመራሩ በዚያ መንገድ ነው የተመለከተው፡፡

     ሰው የተለያየ አስተያየት በተለያየ መንገድ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሁለተኛ ፖለቲካ ላይ መገለል ይሆናል ወይ ብለን ብስናስብ እንዴት ሆኖ ነው መገለል የሚሆነው? ከእንዲህ ዓይነት አገር ጋር የምትሠራው ከፖለቲካ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፉና የአገር ውስጥ ፖለቲካው ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነውና፡፡ በዚያ ደረጃም ብዙ የሥጋት ምንጭ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ልምድ የሌላቸው ሰዎች በዚህ ደረጃ ይሰማራሉ የሚለው ብዙ አገሮች የሚያደርጉት ነው፡፡ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶች ይኖራሉ፡፡ በዚያ መንገድ የሚወጡ አሉ፡፡ ለአንዳንድ ጠቃሚ ለሆኑ አገሮች ደግሞ በመንግሥት ሹመኝነትም የሚሄዱ አሉ፡፡ የእኛ አገር ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ አገሮችም ይህን ልምድ ይጠቀማሉ፡፡ ለእኔ የዲፕሎማሲ ሥራው መጀመርያ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በዲፕሎማሲው ሥር የሚሠራው ምንድነው? ግንኙነቱ በምን ጉዳይ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት? የሚለው ግን ፖሊሲውና ስትራቴጂው ላይ ሠፍሯል፡፡ የአገሪቱ ጥቅም ምን እንደሆነ ከሚገነዘቡት ሰዎች መካከልም አንዱ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት የሚጎድለውን የዲፕሎማሲ ዕውቀትና ቴክኒካዊ ክህሎት በአጭር ጊዜ መማር ይቻላል፡፡ ዋናው መሠረቱ እስካለ ድረስ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ነው የተሾሙት፡፡ በአሜሪካ ደግሞ በርካታ ዳያስፖራዎች አሉ፡፡ መንግሥትን የሚቃወሙም ሆኑ የሚደግፉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን አካላት አግባብቶ በመሥራትና ለአገሪቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ከማድረግ አኳያ ምን አስበዋል?

አምባሳደር ካሳ፡- በዲፕሎማሲያችን ትልቁ ሥራ ተደርጎ ከሚወሰደው ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በአገራቸው ጉዳይ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎችና በትልልቅ ኩባንያዎችና ድርጅቶች የሚሠሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ በሁሉም የሙያ መስኮች የሚሠሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ ዕድል ባይኖራቸውም በተለያዩ መንገዶች ለአገራቸው አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ አቅም ያላቸው ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ዞሮ ዞሮ አንድ አገር ነው ያለን፡፡ ለዚህች አገር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ቀደም ሲል የወጣው የመንግሥት ፖሊሲ ይህንን ደንግጓል፡፡ የሚለውም በኢንቨስትመንት፣ በዕውቀት፣ በገበያ ትስስር፣ ወይም ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ለቤተሰቦቻቸው በሚልኩት ገንዘብ አማካይነት አገራቸውን ያገለግላሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም እንደየአቅማቸው በአገራቸው ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር መሥራት አለብን ነው የሚለው፡፡ ይህ እንግዲህ ከመንግሥት ጋር ከሚደረገው ግንኙነት በተጨማሪ፣ ለኢትዮጵያዊያንና ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራው ነው፡፡ የተጀመረ ነገር አለ፡፡ በበቂ ሁኔታና በሚፈለገው ደረጃ እንዳልደረስን በየጊዜው በሚደረጉ ግምገማዎች የሚታይ ነው፡፡ አሁን በእኔም በኩል አንዱ ትልቅ ትኩረት ይኖረዋል ብዬ የማስበው፣ እነዚህ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሊያግዱን አይገባም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማድረግ ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡

      አገር ሁላችንም የያዝነውን አስተሳሰብና አመለካከት የምናንፀባርቅበት የጋራ ቤት ነው፡፡ ሁላችንም አንድ ዓይነት አመለካከትና አስተሳሰብ እንዲኖረን አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን በሰከነና በሠለጠነ መንገድ፣ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ለጋራ አገራችን አስተዋጽኦ የምናበረክትበት ሁኔታ እንዲፈጠርና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እኔም ይህንን መርህ ነው ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት የማደርገው፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩትም የጀማመሯቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ላይ ይበልጥ የማሳደግና የማጠናከር ይሆናል፡፡ ምናልባት ካነሳኸው ጥያቄ አኳያ በተለያዩ አመለካከቶች ምክንያት የሚኖር ክፍተት ካለ ይህን ክፍተት ቁጭ ብለን በመነጋገር፣ ለመፍታትና ተቀራርበን ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ነው የሚኖርብን፡፡ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች እምነት ስለሆኑ አንድ ማድረግ ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ዘረኛ አመለካከት ከያዙ ጀምሮ ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካን የምንላቸው አንድ አገር ላይ ይኖራሉ፡፡ በአገራችን ጉዳይ ላይ የማንደራደርባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ በፊት እኮ ሌላ ሥልጣን ያለው መንግሥት ነበር፡፡ ከዚያ በፊት የተለያዩ መንግሥታት ነበሩ፡፡ አገርና ሕዝብ የማስቀጠል ጉዳይ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁጭ ብለን በሰከነ መንገድ ነገሮችን ማየት ይኖርብናል፡፡ ይህንንም ቁጭ ብለን እስከተነጋገርን ድረስ ብዙዎችን ነገሮች ልናቃልላቸው እንችላለን፡፡    

ሪፖርተር፡- የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር እያሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩባቸው ወቅቶች ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምን አሳካ ብለው ያስባሉ? የነበሩ ፈተናዎችስ ምን ነበሩ? እንዴት ታለፉ?

አምባሳደር ካሳ፡- ማንኛውም ተቋም ላይ መሪ ሆነህ ስትመደብ የመጀመርያው መለኪያ ብዬ የማስበው ማንኛውንም ፈተና የመጋፈጥ ጉዳይ ነው፡፡ ፈተና ሳታልፍ ውጤት የሚባል ነገር ስለሌለ፡፡ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ትልቅ ዕድልና ትልቅ ፈተና እንደነበሩ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ትልቁ ዕድል በአንድ ተቋም ውስጥ ብዙ የተማሩና ብዙ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የተከማቹበት መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ከእኛም በላይ ዕውቀት ያላቸው፣ አገር የሚወዱ ሰዎች ተቋሙ ውስጥ መኖራቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ገጽታ በዚያ ተቋም ውስጥ ያለው ይኼ ሁሉ ግዙፍ የሆነ ኃይል በሚፈለገው መንገድ ውጤታማ ሳይሆን የቆየባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ ይህንን ፈተና ደግሞ እዚያ ያለውን ትልቅ ዕድል በመጠቀም መለወጥ ይቻላል የሚለው ነው የእኔም ሆነ የሥራ ባልደረቦቼ አስተዋጽኦ የነበረው፡፡ በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲው፣ በምሁራኑ፣ በተማሪውና በድጋፍ ሰጪው መካከል የነበረውን ክፍተት የሚመስል ነገር አስተካክሎ ለአንድ ለጋራ አገራዊ ዓላማ የማዋል ጥያቄ ነው ትልቁ ስኬት ብዬ የምወስደው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይኼ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ያለው፡፡ ይኼን በጥሩ ሁኔታ ለማከናወን እንግዲህ አንደኛው የጋራ አስተሳሰብ መፍጠር ነው፡፡ አሁን ብዙ ውጤቶች መጥተዋል፡፡ ከዚያ ወዲህ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ የምርምር ውጤቶች በጣም ነው የጨመሩት፡፡ በአገር ልማት ላይ ተፅዕኖ ያላቸው ትልልቅ የምርምር ሥራዎች ነው የተሠሩት፡፡ በፒኤችዲና በሁለተኛ ዲግሪ በጣም በርካታ ሰዎችን ለማፍራት፣ በየጊዜው ተቀራርቦ ለመሥራት የተቻለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሁን ከ53 ሺሕ በላይ ተማሪዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 17 ሺሕ የሚሆኑት የሁለተኛ ዲግሪና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ይኼ በአገሪቱ ውስጥ ትልቁ ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ሚና በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲው መካከል ትክክለኛው ድልድይ እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እዚያ ውስጥ የተከማቸው አቅም በሚገባ እንዲወጣና ለአገር ሀብት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የጨመርነው ነገር ይኼን ነው፡፡ ጥሩ ጊዜ ነው የነበረው፡፡ ፈተናዎች ብዙ ጊዜ ነበሩ ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲነሳ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይም እርስዎ የቦርድ ሰብሳቢ ከመሆንዎ በፊትም ሆነ ከነበሩ በኋላ ከኦዲት ሪፖርት ጋር በተገናኘ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ ለብዙ ዘመናት ኦዲት ሳይደረጉና ሲንከባለሉ የመጡ ጉዳዮች እንዳሉ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱን በአንድ ወቅት ስናነጋግርም ይኼንን ገልጸውልን ነበርና አሁንም በቅርቡ ትልቅ የሆነ የኦዲት ሪፖርት ወጥቷል፡፡ ምናልባት እነዚህን የኦዲት ክፍተቶች ከመሙላት አንፃር እርስዎ የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ጊዜ ቦርዱ ምን ሠርቷል? ክፍተቶችስ ለምንድነው በተከታታይ ሲቀጥሉ የኖሩት?

አምባሳደር ካሳ፡- ልክ ነው፡፡ ይህ ችግርና ግኝት አለ፡፡ ግን እኛም ከመጀመራችን አንድ ወይም ሁለት ዓመት በፊት ይኼ ችግር ነበር፡፡ እኛም በመጀመርያ ያደረግነው ይኼን የሚያህል ግዙፍ ዩኒቨርሲቲና የተማረ የሰው ኃይል ያለው ተቋም አሠራሩ ጠፈፍ ያለ መሆን አለበት፣ ጥራት ሊኖረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች የፋይናንስ ተማሪዎች የሚመረቁት እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነውና ተቃርኖም እንዳይሆን ይህ መስተካከል ይኖርበታል የሚለው የሁላችንም ትኩረት ነበር፡፡ ለስልሳ ዓመታት ይኼ ዩኒቨርሲቲ በቆየበት ጊዜ ብዙ ያልተስተካከሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ ኦዲት ለማድረግ ማመሳከሪያው ችግር አለው፡፡ ወደኋላ ያሉ ፋይሎችና መረጃዎች ብዙ ጊዜ ስለማይገኙ ችግር እየተፈጠረ ነው የቆየው፡፡ ያደረግነው በተቻለ መጠን ይኼን ማመሳከሪያ መሥራት ነው፡፡ አሁን ያለው አመራር ከመምጣቱ በፊት የቆየ ችግርም ቢሆን ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል በማለት በኦዲት ተቋማትም ተገቢ የሆነ ድጋፍ እንዲኖር ጥያቄውም ከእኛ ነው የተነሳው፡፡ ሌላ ኃይል መጥቶ አይደለም ኦዲት ያደረገው፡፡ ጥያቄውም የተነሳው ከራሱ ከቦርዱ ነው፡፡ ያንን ለማስተካከል የነበረውን ጤናማነት የሚያሳይ ነው፡፡ ግን ውጤቱ ብቻ ስለሚገለጽና የነበረው ታሪክ ምን እንደነበር ስለማይገለጽ ለኅብረተሰቡ ትክክለኛውን ሥዕል የመስጠት ውስንነት አለው፡፡  

      ሁለተኛው በሕግና በአሠራር መሠረት የተሠሩትንም ጭምር ስህተት አድርጎ የቀረበበት ሁኔታ አለ፡፡ በሁለት አዋጆች መካከል ለቦርድ የሚሰጥ ሥልጣንና ለገንዘብና ኢኮኖሚ በሚሰጥ ሥልጣን መካከል የሚታይ ክፍተት ነበር፡፡ የተሠራው ሥራ ሕጋዊ ነው፡፡ ለኦዲት አድራጊ ድርጅት አንደኛውን የሕግ ድጋፍ ወስዶ ሌላኛውን ካለመውሰድ የሚነሳ ነው፡፡ ያን ያህል የጠፋና የባከነ ገንዘብ ስለነበር አይደለም፡፡  በሦስተኛ ደረጃ ዞሮ ዞሮ ሥራው ውስብስብ ነው፡፡ በጣም ብዙ ነገሮች ናቸው የሚሠሩት፡፡ በጣም ብዙ ነገሮች ናቸው ዘመናዊ ለማድረግ ሙከራ የተደረገው፡፡ ላይብራሪው 24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ፣ ምግብ ቤቶች ብዙ ተማሪ ስላሏቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው አለመረጋጋት ሲፈጥሩ የነበሩትን ነገሮች በሙሉ በተስተካከለ መንገድ እንዲፈቱ፣ በኮንትራት ቅጥር ለረዥም ጊዜ የቆየውን ሁሉ ሕጋዊና ሥርዓት ወዳለው መንገድ ለማስገባት ተሞክሯል፡፡ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ የኮንትራት ሠራተኛ የነበሩትን በሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆ ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት ብዙ ነገሮች ናቸው የተሠሩት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ዩኒቨርሲቲውን አሁን ወደ ተሻለ መንገድ እያስገቡት ነው፡፡ ግን የኋላው ሳይጠናቀቅ ደግሞ የሚመጣውንም ነገር ከማየት ጋር በተያያዘ የተገኙ ውጤቶች ናቸው የቀረቡት፡፡ በእርግጥም ደግሞ ይህን ያህል ተቋም ሲንቀሳቀስ የሚኖሩ ጉድለቶች አሉ፡፡ እነዚያ ደግሞ ተለይተውና ተለቅመው እንዲስተካከሉና እንዲታረሙ እየተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት እንዲያውም ትልቁ ስኬት መጀመሪያ ከጠየቅከው ጥያቄ አንፃር ሥርዓት እንዲኖረውና መልክ እንዲይዝ የተሠራው ሥራ ነው፡፡ ሁለት ሥራዎች ናቸው ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ የተደረገው፡፡ አንድ ኦዲት አካል ተቀጥሮ መረጃ እያሰባሰበ ነው ያለው፡፡ ሁለተኛ ቅርብ የሆኑትን በማስተካከልና ትክክለኛዎችን ደግሞ በመለየት እየቀጠለ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወጣ እንበልና እርስዎ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ክልሎች መካከል ባለው አስተዳደራዊ ወሰን የተለያዩ ግጭቶች ሲነሱ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያና በሶማሌ፣ በአማራና በትግራይ በተለይ በጠገዴና በፀገዴ መካከል፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች መካከል ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ እርስዎም ችግሮች በሚፈጠሩባቸው አካባቢዎች በአካል ሳይቀር እየሄዱ ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ ነበርና የእነዚህ ችግሮች ዋነኛ መንስዔ ምንድነው? አሁንስ ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

አምባሳደር ካሳ፡- በሁለት ከፍለን እንየው፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ነው፡፡ እንደ ሥርዓት ወስደን ከተመለከትነው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነትና ኃላቀርነት በሙሉ በመቋጨት መብቶችን ያለገደብ ለሕዝቦች ሰጥቷል፡፡ የሕዝቦች መብት ደግሞ ራስን በራስ እስከ ማስተዳደር የሚደርስ የጋራ ሥልጣንና የተናጠል ሥልጣን የሚባል ነው፡፡ ሁለተኛው ትንሽም ይሁን ትልቅ ብሔረሰብ በአገሪቱ ሥርዓት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓት አበጅቷል፡፡ የአከፋፈል ሥርዓቱም በዚያ መንገድ ነው የተሠራው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለዚህ በግልጽ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ ሥርዓቱ በመሠረታዊነት የሰላም ምንጭ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓላማውም የሚለው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና ፈጣን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ነው፡፡ ሁሉም ተደምሮ ግን እንደ አገር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ይኼ ፍላጎት ተቋም ይፈልጋል፡፡ ይኼን ለማሳካት ትክክለኛ ዓላማና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በአመራር ቦታ ላይ መቀመጥ አለባቸው፡፡ ይኼን ትክክለኛ ዓላማ በትክክል የተገነዘበ ኅብረተሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ በማይሆንበት ጊዜ ለመፍትሔ በተቀመጠው ሥርዓትና በፈጻሚዎች መካከል ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ክፍተቶች ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡

ሁለተኛው በጣም የሚገርመው ሥርዓቱ መፍትሔም አስቀምጧል፡፡ ግጭት መቼም አይኖርም አይልም፡፡ ግጭት በማንኛውም ጊዜ በአንድ ወይም በሌላ ሊከሰት ይችላል፡፡ እንዴት ይፈታል ለሚለው ጥያቄም መፍትሔ አስቀምጧል፡፡ ለምሳሌ በሁለት ክልሎች መካከል በወሰን ጉዳይ የሚነሳ ጥያቄ ሁለት ተጎራባች ክልሎች አንድ አገር ነው ያላቸው፡፡ ዴሞክራሲን በሚመለከት አንድ ዓላማ ነው ያላቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ መኖር አይችልም፡፡ መዋጋት የለባቸውም ነው የሚባለው፡፡ መጋጨትም የለባቸውም፣ መዋጋትም የለባቸውም፡፡ ይኼን ወደ ቀውስ ሳትወስደው፣ ወደ ግጭት ሳትወስደው፣ ወደ ደም መፋሰስና ንብረት መጥፋት ሳትወስደው ልትፈታው ትችላለህ ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ይኼ ካልሆነስ? ሳይስማሙ ቢቀርስ? ሳይስማሙ ቢቀሩ ደግሞ አይዋጉም ነው የሚለው፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁሉም ክልሎች የሚወከሉበት ነው፡፡ ይኼ ምክር ቤት ይውሰደውና አጥንቶ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ያ ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ ይህንን ሁሉም በፀጋ ይቀበላል፡፡ ወደዚህ ሄዶብኛል ወደዚያ ሄዶብኛል በማለት ወደ ግጭት አናመራም ነው የሚለው የቃል ኪዳን ሰነዱ፡፡ ያ የቃል ኪዳን ሰነድ ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ዕውቀት ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ እንዴት ነው የተቀመጠው ብለህ ነው መጠየቅ ያለብህ፡፡ የራስህን መፍትሔ አይደለም የምታስቀምጠው፡፡ ሁለተኛው የክልሎች ምክር ቤቶችም አሉ፡፡ አቅማቸው የተሟላ ነው፡፡ ይኼ ነው ሥርዓቱ፡፡ ታዲያ ይኼ ሆኖ እያለ ለምንድነው ግጭቶች የተበራከቱት የሚለውን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔም መስጠት ያስፈልጋል፡፡

      መጀመርያ መሠረታዊ ቅራኔዎችን እንደ አገር አጥፍተናል፡፡ አሥራ ሰባት የታጠቁ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ የእርስ በርስ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ አሁን የዚያ ዓይነት ጦርነቶች የሉም፡፡ ያለን ግጭት ወይ በወሰን የሚነሳ ነው ወይ ደግሞ በአንድ ክልል ውስጥ በራሱ የሚነሳ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ተጠቅሜያለሁ አልተጠቀምኩም በሚል፡፡ ከዚያ ደግሞ በሁለት አካባቢዎች የሚነሱ የወሰን ውጥረቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ግጭቶች መኖር አልነበረባቸውም፡፡ ከኖሩ ደግሞ የሚፈቱበትን ሥርዓት አግባብ ተከትሎ መስተካከል ነበረባቸው ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ ችግሮቹ አሁን እንዳያችሁት በ2008 ዓ.ም. እና በ2009 ዓ.ም. ጋምቤላ ላይ የተከሰተው በኑዌርና በአኙዋ፣ ኦሮሚያ ውስጥ በኦሮሚያና በሶማሌ መካከል በወሰን ይመሰላል፡፡ ግን በሃይማኖት ማለትም በእስልምናና በክርስትና መካከል፣ በአማራና በትግራይ መካከል ደግሞ በጠገዴና በፀገዴ የሚታይ ውጥረት አለ፡፡ እነዚህ ሁለት ሦስት ናቸው የተለዩት፡፡ አንደኛው የፌዴራል ሥርዓቱንና ሕገ መንግሥቱን በደንብ የመገንዘብ ችግር መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ሁለተኛው በተጋጩ ወገኖች መካከል ያሉ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ ላይ ከግጦሽና ከውኃ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ግጭቶች አሉ፡፡ እነዚህን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት በቅርብ ጊዜ በተሻለ ደረጃ ውጤት የምናይበት ይሆናል፡፡ በጋምቤላና በኦሮሚያ እንዲሁም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ መካከል ያለው ጉዳይ ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡ አሁን ነጥቡ የእኛ የፌዴራል ሥርዓት በጣም ደስ የሚል ነገር አለው፡፡ ብዙ ነን፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ወደድንም ጠላንም ብዝኃነት አለ፡፡ ዕጣ ፈንታችንና ዕድላችን የሚወሰነው አንድ ላይ ነው፡፡ አንዳችን ያለአንዳችን ህልውና የለንም፡፡ አንድ አካባቢ ግጭት ሲነሳ ተጎጂዎች ሁላችንም ነን፡፡ ስለዚህ መርሆው ራስን ብቻ መውደድ ያጠፋናል ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ከውጭ አገሮች ጋር ያለው የድንበር ጉዳይስ? ለምሳሌ ከሁለቱ ሱዳኖች፣ ከኬንያና ከሌሎች ጋር ያለው የድንበር ሁኔታ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ካሳ፡- ይኼ ጉዳይ በዋናነት የሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ነው፡፡ ነገር ግን እኔ እንደ መንግሥት ኃላፊነቴ የማውቀው ነገር አለ፡፡ በወሰን ዙሪያ ብዙ ያላለቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ የታወቁም አሉ፡፡ በደንብ መስመር መያዝ የሚገባቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ከአገሮቹ ጋር በቅንጅትና በኅብረት በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ተመሥርተህ የምትሠራው ነገር መሆን አለበት፡፡ አንዳንዴ አገርን መውደድ አንድ ነገር ሆኖ የአገር ፍላጎት ግን በሕግ ነው የሚመራው፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት አድርገህና ለረዥም ጊዜ የቆየውን የሕዝብ ግንኙነትና የአገር ጥቅም አሳልፈህ ሳትሰጥ የምትሠራው መሆን አለበት፡፡ ይኼ በሁለት መንገድ የተጀመረ አለ፡፡ ከሱዳን ጋር ያለው እኔም በተወሰነ ጊዜ አባል የነበርኩበት የጋራ የድንበር ኮሚሽን የሚባል አለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የጋራ ድንበር ቴክኒክ ቡድን የሚባል አለ፡፡ በዚህ አማካይነት በርከት ያሉ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ ሥራውን ለማከናወን ግን በጣም ትልቅ ሀብትና በጊዜ ገደብ ደግሞ ሁለቱ አገሮች በሚስማሙት መሠረት እንዲያልቅ ተደርጎ እየተሠራ ያለ አለ፡፡ የተወሰነ ጊዜ የወሰደ ቢሆንም በዚያ ምክንያት መሬት ለሱዳን የተሰጠ ወይም ወደኛ የመጣ የለም፡፡ ይህ ስምምነት በሒደት ላይ ነው ያለው፡፡

      ከሌሎች ጋር ያለው ነገር በግልጽ የሚታወቅ ስለሆነ በተለየ አስተዳደር እንዲሠራ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ሁለተኛው ግን ከዚያ ጋር የተነሳው ጥያቄ ከኬንያ ጋር ይኼ ይገባኛል፣ ያ ይገባኛል በማለት የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡ ከእሱ ይልቅ በልማት ሕዝቡን ለማስተሳሰር ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለቱ የአገር መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ የመግባቢያ ስምምነት ሞያሌ ላይ ከተፈረመ በኋላ፣ የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በእኛ መሥሪያ ቤት አስተባባሪነት ሲሠራ ቆይቶ በቅርብ ጊዜ ፕሮጀክቱ ይፋ ተደርጓል፡፡ ከድንበሩ በላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነት ነው ይበልጥ የተሻለ የሚሆነው፡፡ በነገራችን ላይ በዓይነቱም የመጀመርያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው ግን የውስጥ ችግሮቻችንን መፍታት ነው፡፡ የውስጥ ጉዳዮቻችንን ስንፈታ ጠንካራ እንሆናለን፡፡ አቅም ይኖረናል፡፡ እንከበራለን፡፡ መከበር ብቻ ሳይሆን ተፅዕኖ የማሳደር አቅማችንም ፖዘቲቭ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ጥቅማችን በላቀና በተሻለ ደረጃ ማስከበር የምንችልበት ዕድል ይመጣል የሚለው ትክክለኛ አቅጣጫ ይመስለኛል፡፡     

ሪፖርተር፡- በአገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ከማንነት ጋር የተያያዙ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጥያቄያቹን በዋናነት የሚፈታው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እርስዎ ደግሞ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሆነው ሠርተዋልና በአሁኑ ወቅት የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ተቋማዊ አቅሙን እንዴት ነው የሚገመግሙትበተለይ የማንነት ጥያቄዎችን በተገቢው ከማስተናገድና ከመፍታት አኳያ?

አምባሳደር ካሳ፡- እንግዲህ እኔ ልነግርህ የምችለው ከሁለት ዓመት በፊት ስለነበረው ነው፡፡፡ ይህን ጥያቄ መመለስ ያለባቸው አሁን በሥራ ላይ ያሉት ናቸው፡፡ አጠቃላይ ነገር ለማንሳት ግን በማንነት ጥያቄ ላይ ሦስት አራት ጉዳዮች አሉ፡፡ የማንነት ጥያቄ በመሠረቱ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የማንነት ጥያቄ ሰጪና ከልካይ የለውም፡፡ ገና ሕገ መንግሥቱ እንደፀደቀ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን ለመጠበቅ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተመዘገቡት ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች 76 ናቸው፡፡ አብዛኛዎቻችን በልማድ ከሰማንያ በላይ ነው የምንለው፡፡ ሦስተኛውና በጣም የተዛባው አመለካከት የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ መሬት በእርግጥ ጠቃሚ ነው፡፡ ከሕዝብ በላይ ግን አይደለም፡፡ እነዚህ ሕዝቦች በሰላም ሲኖሩ ነው ትርጉም የሚኖረው፡፡ ያንን መሬት ሺሕ ዓመት ኑረንበታል እኮ፡፡ ዓባይን ለሺሕ ዓመታት ዘፍነንበታል፡፡ ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ የቻለው ሰው ሲረጋጋ፣ ሰው ሲያስብና ያለውን ዕውቀትና ችሎታ ተግባራዊ ማድረግ ሲችል ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ነው ክብሩ፡፡ ከሰው በላይ ለመሬትና ለአካባቢ ስትሰጥ ወደ ግጭት ልታመራ ትችላለህ፡፡ አራተኛው በጣም የተዛባው ችግር ሥዕሉን በትልቁ አለማየት ነው፡፡ እነዚህ ውስን አካባቢ ያሉ ችግሮች አካባቢን በስፋት ሲሸፍኑ ጠቅላላ ዓላማ ነው የሚደናቀፈው፡፡ የሕዝብና የአገር ጥቅም ነው የሚደናቀፈው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያሉ የአስተሳሰብ ችግሮች የወለዷቸው ናቸው፡፡

      የፖለቲካ ሥልጣን ያለን ሰዎች ሥልጣኑን ለምንድነው የወሰድነው? ሥልጣኑን የወሰድነው የሕዝብን ችግር፣ የአገርን ችግር ልንፈታበት ነው፡፡ የሕዝብ ሕመም የማያመን ከሆነ ስህተት አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ባንለቅም፣ ከመስመራችን ወጥተን ባንፈጠፈጥም ዝንባሌዎቹ ግን ልክ አይደሉም፡፡ ቶሎ ቶሎ ማረም አለብን፡፡ አሁን ሁኔታዎችን በዚህ መንፈስ ለማቃለል እየተሞከረ ነው ያለው፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ መካከል በ142 ቀበሌዎች ላይ ስምምነት ተደርጓል፡፡ አሁን ወደ ኦሮሚያ የሚሄዱት፣ ወደ ሶማሌም የሚሄዱት መሬት እንዲነኩ እየተደረገ ነው፡፡ በትግራይና በአማራ መካከል ለነበረው ትልልቅ አገራዊ ኮንፍረንሶች ተጀምረዋል፡፡ መሬት ላይ ያለው የጠገዴና የፀገዴ ጉዳይም ዕልባት እንዲያገኝ እየተሠራ ነው፡፡ አሁን የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ከአሥር ያላነሱ አሉ፡፡ የማንነት ጥያቄውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡ አንድ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ የሚለይበትን ነገር ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ጉዳዩ የዘገየ ነው ወይስ በትክክል የቋንቋ የማንነት ጉዳይ አለበት የሚለው ጥያቄ ሊታይ ይችላል፡፡ እኔ በነበርኩ ጊዜ ለምሳሌ የማንነት ጥያቄ አይደሉም ተብለው ምላሽ የተሰጣቸው አሉ፡፡ አስታውሳለሁ ከሁለት በላይ ናቸው፡፡ ደቡብ ላይ የሚኖር መንጃ የሚባል ሕዝብ አለ፡፡ መንጃ የሚባለው ከፋ ላይ አለ፡፡ ዳውሮም አለ፡፡ ሌሎች ቦታዎችም ላይ እናገኘዋለን፡፡ ከፋ ላይ ያለው የመንጃ ሕዝብ ከፍኛ ነው የሚናገረው፡፡ ዳውሮ ያለው ዳውሮኛ ነው የሚናገረው፡፡ የመንጃ ሕዝብ በኅብረተሰቡ ደረጃ የተናቀና ዝቅ ተደርጎ የሚታይ፣ የተዋረደ፣ እሱ በበላበትና በጠጣበት ሌላ ሰው የማይበላበትና የማይጠጣበት ነው፡፡ ከዚህ ብሶት ተነስቶ እኛ ራሳችንን የቻልን ነን የሚል ጥያቄ ነበረ፡፡

መፍታት ያለብህ ይህን ኋላ ቀር አመለካከት ነው፡፡ ማስተካከል ያለብህ በሰው መካከል ልዩነት የለም፣ ይህ ባህል በረዥም ጊዜ የተፈጠረ አድልኦ ነው ብለህ ይህን ኋላቀር አመለካከት ነው መታገል ያለህብ፡፡ መንጃዎችም ይህንን ነው መታገል ያለባቸው፡፡ ሌሎች ዴሞክራት ነን የሚሉትም ይህንን ችግር ነው ለመፍታት መሥራት ያለባቸው፡፡ ይኼ ሳይፈታ ሲቀር ወደ ማንነት ጥያቄ ይመጣል፡፡ ኋላ ተለይቶ ሲታይ የማንነት ጥያቄ አይደለም ተብሎ መፍትሔ አግኝቷል፡፡ ሁለተኛው ሸካሽ የሚባል ሶማሌ ውስጥ ለ13 ዓመት የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ እነሱ አንድ ሆነው ሲዋጉ ሁሉ ነበር፡፡ ኋላ ስናጠናው ይኼኛውም የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ የማንነት ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ሆኖ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የማንነት ጥያቄ ትክክል የሆነ የማንነት ጥያቄ ሆኖ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል የተነሳው የቅማንት የማንነት ጥያቄ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ቅማንት የሚባል ሕዝብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ግን ተዋህዶ ጠፍቷል የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ አልጠፋንም አለን የሚል መጣ፡፡ ይኼ በሚሆንበት ጊዜ በብቃት ጥያቄውን መመለስ ያስፈልግ ነበር፡፡ ሲወዛወዝ ሲወዛወዝ ብዙ ጉዳቶችና ጥፋቶች የዳረገበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ አንዳንዴም በዚሁ ቀዳዳ ለረዥም ጊዜ ተሳስቦና ተፋቅሮ የኖረውን ሕዝብ የሚያሻክሩ ችግሮች ተፈጸሙ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ባህሪ አለ ማለት ነው፡፡ ይህንን አንጥረህና አጣርተህ ለመመለስ ተቋማዊ ብቃት ይፈልጋል፡፡ እዚህ ተቋም ውስጥ የሚሠራ ሙያውም፣ ዕውቀቱም ችሎታውም ያለው ሰው ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በሁሉም መስክ ያለን ተቋማዊ አቅም ብዙ ጠንካራ አይደለም፡፡ ገና እየተፈጠረ ያለ ነው፡፡ እየተሠራ ያለ፡፡

ሁለተኛው ይህን ጥያቄ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን የሚፈታው መጀመርያ የሚያስተናግደው ክልል ነው፡፡ ጥያቄውን በአግባቡ አቅርበህ ያንን በአግባቡ መፍታት አለብህ፡፡ ይህም ተቋማዊ አቅምና የፀዳ አመለካከት ይፈልጋል፡፡ ምክንቱም ቅድም እንዳልኩት ማንነትን ሰጪም ከልካይም የለውም፡፡ እኔ እከሌ ነኝ ካለ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተከበረ ነውና አንተ ነህ አይደለህም ብለህ አንተ አትከለክለውም፡፡ ይልቁንስ የምታሳምነው የገፋህ ነገር ይኼ ስለሆነ ይኼ ነው ትላለህ፡፡ እውነተኛ ማንነት ከሆነ ደግሞ ትቀበላለህ፡፡ ይህን ለመለወጥ የአመለካከት ጥራትና ብቃት መያዝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጥረት ላይ ያለ እንጂ ሁሉ ነገሩ ያበቃ ያለቀ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ እየተማርን የምንፈታው ነገር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ባለፈው ጊዜ የአማራና የትግራይ የሕዝብ ተወካዮች መቀሌ አድርገውት በነበረው ኮንፈረንስ እርስዎም ተገኝተው ነበር፡፡ ከተሳሳትኩ ያርሙኛል በነበረው ውይይት የእርስዎ ስሜት በጣም ተጎድቶ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ማልቀስ ድረስ ደርሰዋል ይባል ነበርና ያስለቀሰዎት ጉዳይ ምንድን ነበር?

አምባሳደር ካሳ፡- ሰው ስትሆን ስሜት ይኖርሃል፡፡ እኔ ደግሞ የሚያዝንም የሚደሰትም ጥሩ ሰው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በወቅቱ የነበረው ስሜት እኔ በትግራይና በአማራ ሕዝብ የሁለቱን ድርጅቶች ትግል የመራሁ፣ ታሪክ ለማወቅም አብሬ ለማለፍም ዕድሉ ነበረኝና ያ ትልቅ ሥዕል በአዕምሮዬ መጣ፡፡ በወቅቱ እኔ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ (ብአዴን) ወይም (ኤሕዴን) ታጋይ ነኝ፡፡ እኛ በቁጥር ትንሽ ነበርን፡፡ ወደ ውጊያ ስንገባ እኛ እንዳንጎዳና እንዳንጠፋም ለአገር በነበረን ጠቀሜታና አስፈላጊነት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (የሕወሓት) ታጋዮች መስዋዕትነት እኛ እንከፍላለን ቆዩ ብለው ወደ ኋላ ያስቀሩን ነበር፡፡  ይኼን እያደረጉ ያለፉ ልጆች አሉ፡፡ በጣም ብዙ ልጆች፡፡ ሕዝቡ ኢሕዴን ተመሥርቶ በትግራይ አካባቢ ራሱን ሲያስተዋውቅ የሞራል ምንጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ግንባራችሁን ለጥይት እንጂ ጀርባችሁን ለጥይት ሰጥታችሁ እንዳትሞቱ ይል ነበር፡፡ እንዲህ ብለን የመጣን ነን እኛ፡፡ በኋላ ደግሞ ወደ መሀል አገር እየገባን ስንሄድ የትግራይ ልጆች ለሕወሓት ተሠልፈው ቆስለው ሲያዙ የአማራ አርሶ አደር ደብቆ፣ አክሞና አድኖ ይይዛቸው ነበር፡፡ ቦታውን ደርግ ይዞት ማለት ነው፡፡ ደርግ ከያዘው በኋላ እነዚህን ሰዎች እንዳይወስዳቸው ሲያደርግ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ እኛ ስንመለስ ያስረክቡን ነበር፡፡ ይኼ ነው ታሪካችን፡፡ ይህ የአጭር ጊዜው ታሪክ ነው፡፡ የረዥም ጊዜውን ታሪክ ወደኋላ ተመልሰን ብንመለከተው ደግሞ፣ በመሳፍንቶች ጊዜ እዚያም እዚህም በሕዝቡ መካከል ኃይለኛ መስተጋብር ነው የነበረው፡፡ በሃይማኖት፣ በአገር ግንባታ እነዚህ ሕዝቦች የነበራቸው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ እኛ በዚህ ዘመን ወደ ውጊያ ባናመራም አንዣቦ የነበረው ነገር ደስ አይልም ነበር፡፡ አንዣቦ የነበረው አስተሳሰብ ብቻ አይደለም፣ በጣም ዘረኛ የሆኑ ጤነኛ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ከአካባቢው አልፈው በአገሪቱንም ጭምር ጤናማ ያልሆነ አየር ያሸቱት ነበር፡፡  እኛ እንግዲህ ከዚያ አልፈን የግል የምንለው ሕይወትም ሳይኖረን በሕይወት እዚህ ደርሰናል፡፡ ብዙ ሰው እየቀበርን መጥተን ይህ አሁን ያለው ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የሚመጣው ትውልድ ይለፍለት ብለው ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይጠይቁ ያለፉ ሰዎች ጥለን የመጣን ሰዎች ነን፡፡ ያ ነበር እኔን ስሜት ውስጥ የከተተኝ፡፡ ያኔ ሰማዕታትን ስንቀብር እኮ በፅናት ዓላማችሁን ዳር እናደርሳለን፣ ዓላማችሁ ወደኃላ እንዳይመለስ እናደርጋለን ብለን ነው ቃል ኪዳን የምንገባው እንጂ አልቅሰን አናውቅም፡፡ አሁን አንድ ደረጃ ላይ ሆነን፣ ባለሥልጣንም ሆነን ቤት ኖሮን፣ ጥሩ መኪና መንዳት ደረስን፡፡ ስለዚህ ይህ ትውልድ ሳይጠፋ እንዲህ ዓይነት አደገኛ ነገር ቢመጣ አሳፋሪ ነው፡፡ መጥፎ ነው፡፡ ያ ነበር የእኔ ነጥብ፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሳስበው ጥሩ ስሜት አይሰማኝም፡፡    

ሪፖርተር፡- አሁን እርስዎም ጠቃቅሰውት ነበር፡፡ የታገላችሁለት ዓላማ ይህን አስተሳሰብ ከመፍጠር አንፃር፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠሩትን ነገሮች ብናያቸው አለመረጋጋቶችና ግጭቶች አሉ፡፡ ከዚህ አለመረጋጋትና ግጭት በመነሳት የፌዴራል ሥርዓቱ መዳከም ጀመረ እያሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የለም አሁን ነው እንዲያውም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ቅርፅ እየያዘ የመጣው የሚሉ አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል? ወይስ ቅርፅ እየያዘ መጥቷል?

አምባሳደር ካሳ፡- በሁለት መንገድ እንየው፡፡ ለእኔ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የበለጠ ጠንካራ እየሆነ የሚሄድበትን ዕድል እያገኘ ነው፡፡ ይኼ ግጭት ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ የመጀመርያው ሥራ የፌዴራል ሥርዓት ግንዛቤ እንዲፈጠር እያደረገ ነው ያለው፡፡ ጥያቄዎች እዚህም እዚያም ቢነሱም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በይዘቱ የሚለውን ብዙ ሰው እንዲያውቀው ዕድል የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የፌዴራል ሥርዓት በይበልጥ ለሕዝቡ የቀረበ ሥልጣን ነው፡፡ የአካባቢህን ተፈጥሮ ሀብትና አቅም እንድታሳድግ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ በእኩልነትና በአንድነት እንዲወሰን የሚያደርግ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ  ጥለውት በሚያልፉበት ጠባሳ ግን መሆን የለበትም፡፡ ዋጋም የሚያስከፍል መሆን የለበትም፡፡ ክርክር ሲነሳ ሰው አገር የሚፈርስ ይመስለዋል፡፡ ግን አይደለም፡፡ መከራከር አለበት፡፡ እያንዳንዱ የጋራ ኃላፊነት አለበት፡፡ የተናጠልም ኃላፊነት አለበት፡፡ የተናጠል ኃላፊነቱን ለመወጣት የግዴታ ከሚመራውና ከሚያስተዳድረው ሕዝብ አንፃር ያሉትን ሁኔታዎች ይዞ መነሳት ይችላል፡፡ የራስን ጥያቄ በሌላው ላይ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጫን የሚደረግ ጥረት ከሆነ ግን የጋራ ቤቱ ደግሞ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ እዚህ ላይ ነው ሚዛኑ የሚያስፈልገው፡፡ ስለዚህ ለእኔ መጀመርያም መሠረቱ ጠንካራ ስለሆነ አሁን የፌዴራል ሥርዓቱ እየፈረሰ ነው የሚለው አይታየኝም፡፡ እንደሚባለው አይደለም አሁን ያለው ሁኔታ፡፡ ስለዚህ የፌዴራል ሥርዓቱ ለሰላም፣ ለልማትና ለሕዝቦች ተሳትፎ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ወይም ጋምቤላ ሄደህ ብታይ አሁን መሠረት ያለው ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ስለመኖራቸው የማይታወቁና እንኳንስ መንግሥትን ማስተዳደር፣ ልማትን ማምጣት፣ አካባቢያቸውን መንከባከብና በአገር ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ይቅርና ጫፍ ላይ እንዲኖሩ፣ ዋና መስመርና ከተሞች ላይ ወታደርና ድንበር ጠባቂ ኃይል ብቻ የሚንቀሳቀስበት ዘመን ነው የነበረው፡፡ አሁን እነዚህ ወገኖች ተምረው መንግሥትን ያስተዳድራሉ፣ በጀት ይመራሉ፣ አካባቢያቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በጣም ጠንካራ በሆነ መሠረት ውስጥ ነው ያለው፡፡ እዚህ ላይ ግን መሠራት ያለበት ይህንን የሚመሩ ሰዎች ትክክለኛ አመለካከትና አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ይህ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ደግሞ ይህንን ይበልጥ እንድናውቅ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በኦሮሚያ አሁን ይኼ ጎድሎኛል ብሎ የሚነሳ ጥያቄ ካለ የኦሮሞ ሕዝብ ትክክለኛው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ሲመለስ ግን የአማራን፣ የትግራይን፣ የአፋርን፣ የሶማሌን . . . የማይጎዳ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ትክክለኛ ተፈጥሮ ይኼ ነው፡፡ ምንድነው ለሚለው የራስን ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ አንሳ፣ የሌላውን መብት ደግሞ አለመጋፋትህን እርግጠኛ መሆን አለብህ፡፡ አብረህ የምትኖረውም ይህን ስታደርግ ነው፡፡ ስስታም የሆንክ ዕለት የብቻህን ያሰብክለት ግን ወደድክም ጠላህም ሄደህ ሄደህ መድከምህ አይቀርም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣንም በተመሳሳይ፡፡ እኔ አሁን እዚህ ቦታ ሆኜ አገርና ሕዝብን አገለግላለሁ ብዬ ሳስብ ስለመጣሁበት ብሔር ብቻ የምጨነቅ ከሆነ አለቀልኝ ማለት ነው፡፡ ሁሉም ሕዝብ ለእኔ እኩል ነው፡፡ የሁሉም ሕዝብ መጠቀም ነው እኔ የመጣሁበትን ሕዝብ የሚጠቅመውና ኑሮውን የሚያሻሽለው፡፡ ሁሉም ሕዝብ ሳይጠቀም እኔ የመጣሁበት ሕዝብ ብቻ ይጠቀማል ብዬ ካሰብኩ ፈንጂ ነው እየቀበርኩ ያለሁት ማለት ነው፡፡

ፌዴራል ሥርዓቱ ትንሽ የውድድር ባህሪ አለው፡፡ የአመራር ልዩነትና የሕዝብ የሥራ ባህል አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ትንሽ የመበላለጥ ምልክት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህንን እንደ ዕድል መጠቀም ነው የፌዴራል ሥርዓቱ የሚለው፡፡ ይኼ የተሻለ ክልል እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕዝብን አሳትፎ ሀብት የሚፈጥር ክልል ካለ እንዴት አድርጎ እንዳሳተፈ ሌላው ክልል መጥቶ ያለ ክፍያ በነፃ እንዲማረው፣ ወይም ከዚህ ሄዶ ልምዱን እንዲያካፍል ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም የዚህ መሻል ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህ የፌዴራል ሥርዓቱ ባህሪ ይኼ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- እርስዎ ብአዴን (ኢሕአዴግ) ውስጥ ለረዥም ዓመታት በትግል ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ከድል በኋላ ደግሞ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ሠርተዋልና ይህንን ያሳለፉትን ጊዜ እንዴት ነው የሚገመግሙት? ምንስ ስኬት አስመዝገቤአለሁ ብለው ያስባሉ? ምንስ ዓይነት ፈተና ነበረው?

አምባሳደር ካሳ፡- እውነት ለመናገር ደርግ እስኪደመሰስ በነበረው ጊዜ ማናችንም ውስጥ  ደርግ ተደምስሶ ወደ መንግሥት ሥልጣን እንደርሳለን ብሎ ያለመ ሰው የነበረ አይመስለኝም፡፡ ካለም የሚሳሳት መስለኛል፡፡ በግሉ እንደ ድርጅት ሊደርስ እንደሚችል፣ መንግሥት ሊኖረው እንደሚችል ያውቃል፡፡ ግን ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያውቅ ሰው አልነበረም፡፡ በግሌም እንደዚያ ነው፡፡ ከደርግ መደምሰስ በኋላ ሳስበው በጣም ብዙ ጥሩ ነገሮች ተሠርተዋል፡፡ እዚህ አገር ውስጥ እኔ የምከራከረው አለ፡፡ እኔ ለወጣቱ ትውልድ የሚሆን አገር መሠራት ተጀምሯል ብዬ አስባለሁ፡፡ አላለቀም ግን ተጀምሯል፡፡ በአቅሜ ለዚህ አገር ጥሩ ዋጋ የከፈልኩበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የባከነ ዕድሜ አለኝ ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ይኼ ሁሉ የተጀመረ ሥራ ነው፡፡ ነገር ግን ካላለቀ በሕይወት ሆኜ ይኼ ነገር ቢበላሽ በጣም ከሚቆጩ ሰዎች አንዱ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የቤተሰብና የትምህርት ሁኔታዎ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ካሳ፡- ሦስት ልጆች አሉኝ፡፡ በቅርብ አንድ ሊመጣ ይችላል፡፡ ትምህርቱን በተመለከተ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ተምሬያለሁ፡፡ የመጀመርያ ዲግሪዬን በኢኮኖሚክስ ሠርቻለሁ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በኦርጋናይዜሽን ሊደርሽፕ ነው፡፡ በጣም ብዙ ትምህርት ተማርኩ የምለው ግን ሕዝብ በማገልገል ያገኘሁት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...