Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአንድ ቢሊዮን ዶላር የቡና ዕድሎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ሰንጠረዥ ውስጥ ከሁሉም የወጪ ንግድ ምርቶች  ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ቡና በመሪነቱ ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ የአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ መረጃዎች በተደራጀ መልክ መተንተን ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ዋና የወጪ ምንዛሪ ምንጭ ከሆኑ ምርቶች ሁሉ በመላቅ በአንደኛነት ደረጃ እንደሚገኝ መዛግብቱ ያሳያሉ፡፡ በአገሪቱ ቡናን በመቅደም የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ የሚችል ምርት እስካሁን ሊመጣ አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንደሚገልጹትም፣ እስካሁን ቡናን የሚተካ ተወዳዳሪ ምርት አልመጣም፡፡ ወደፊትም ቡና የአገሪቱ የጀርባ አጥንት በመሆን እንደሚቀጥል ያምናሉ፡፡

ሆኖም ግን ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ አኳያ፣ ቡና ይዞት የቆየው ድርሻ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት እንደነበረው ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ ከ60 ወይም ከ70 በመቶ የሚደርስ የገቢ ድርሻ የለውም፡፡ የገቢ ድርሻው እየቀነሰ መጥቶ ወደ 20 በመቶ ገደማ ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የአገሪቱን የወጪ ንግድ የገቢ መጠንና የእያንዳንዱን ምርት የንግድ ድርሻ የሚያመላክቱ ጥናቶች፣ የቡና ድርሻ በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያሉ፡፡ ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1976 በነበሩት ዓመታት የአገሪቱ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአማካይ 397.43 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የቡና ዓመታዊ ገቢ 247.07 ሚሊዮን ዶላር ስለነበር፣ ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ድርሻው 62.14 በመቶ ይሸፍን ነበር፡፡

ከ1978 እስከ 1981 ዓ.ም. አገሪቱ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአማካይ 399.2 ሚሊዮን በሆነበት ዓመታት ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ የቡና ድርሻ 63.8 በመቶውን በመያዝ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከ1982 እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ በየዓመቱ ሲመዘገብ የነበረው ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ 274.6 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሽቆለቆለበት ጊዜም ቢሆን፣ የቡና ድርሻ 53.4 በመቶ እንደነበር የተሰባሰቡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከ1986 ዓ.ም. በኋላም የቡና የበላይነት ዘልቋል፡፡ እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ የአገሪቱ የወጪ ንግድ አማካይ ገቢ ወደ 517 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ሲል፣ የቡና ድርሻም ወደ 61.4 በመቶ አሻቅቧል፡፡ በወጪ ንግድ ገበያ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይይዝ የነበረው የቡና ድርሻ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ግን እየቀነሰ መጥቷል፡፡

በተለይ ካለፉት አሥርታት ወዲህ መረጃዎች የድርሻው ቅናሽ እየጎላ መምጣቱን አኃዞቹ አመላክተዋል፡፡ በ2003 ዓ.ም. አገሪቱ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ 2.74 ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ፣ ከቡና የተገኘው ደግሞ 841.8 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይሁንና ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ አንፃር ሲመዘን ድርሻው 30.6 በመቶ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ካስመዘገበችባቸው ዓመታት አንዱ 2004 ዓ.ም.  ነው፡፡ በወቅቱ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 3.15 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የቡና ገቢ 833.1 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ድርሻውም 26 በመቶ ነበር፡፡ ሆኖም የቡና ድርሻ ከዚህ በኋላ እየቀነሰ መምጣቱን ሳይገታ በ2005 ለአገሪቱ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ከቀደሙት ዓመታት ይባሱን ቀንሶ 746.6 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ ነበር፡፡ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ ድርሻውም ወደ 24 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ወደ 21.6 በመቶ በመቀነስ ባለፉት 15 ዓመታት ከነበረው ድርሻ በታች እያሽቆለቆለ ቀጠለ፡፡

የቡና ገቢ እንዲህ እየዋለለ ለመቀጠሉ የሚቀርቡት ምክንያቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ መውደቅ፣ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው ቡና መጠን መቀነስ ደጋግመው ይጠቀሳሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህም ቢሆን እነዚህ ምክንያቶች አሁንም የሚደመጡ የተለመዱ ሰበቦች ቢሆኑም፣ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች እየጨመሩ በመምጣታቸውና እንደ አበባ ያሉ ለአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ እንግዳ  ምርቶች የወጪ ንግዱን መቀላቀላቸው ምንም እንኳ ዋነኛ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ቁንጮነቱን፣ የቡናን ከፍተኛ የበላይነት ድርሻ ግን ሸርሽሮታል፡፡

ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት አኳያ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ይዞት የቆው ድርሻም ቢሆን እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ሲባል የቡና ጠቀሜታ መቀነስን ወይም የቡና ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚቀንስ ምክንያት ሆኖ ሳይሆን፣ በስታስቲካዊ አገላለጽ፣ ቡና ባደገና በያዘው ድርሻ መጠን በዚያው አግባብ ሌሎች ምርቶችም ለውጭ ገበያ እየቀረቡ በመምጣታቸው በቡና የተያዘውን የአንድ ምርት የበላይነት ድርሻ የሚጋሩ ሸቀጦች ለውጭ ገበያ መቅረብ መጀመራቸውን የሚያመላክት አካሄድ ነው፡፡ 

ይህም ቢባል የ2009 በጀት ዓመት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ከቡና ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ ያስመዘገበችበት ዓመት ተብሎ መጠቀሱን ነው፡፡ ከፍተኛ መጠን ያስመዘገበ የ882.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ 2009 ዓ.ም. ከሌሎቹ ጊዜያት ለየት እንዲል አድርጎታል፡፡ ይህም ሆኖ ከዘንድሮ የወጪ ንግድ ምርቶች አኳያ የቡና ድርሻ 24 በመቶ ነው፡፡

አገሪቱ ካላት የቡና ማሳና ልታመርት ከምትችለው መጠን አንፃር፣ ከፍተኛነቱ የተነገረለት የቡና ገቢ፣ ያን ያህል ብዙ እንደማያኩራራ አቶ ዘሪሁን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን የቡና የወጪ ንግድ መጠን ወደፊት የተሻለ መሆኑ እንደማይቀር ያምናሉ፡፡ ለዚህም ከምርት ጀምሮ አጠቃላይ የቡና ግብይት ሒደት ላይ አዳዲስ አሠራሮች እየተተገበሩና ነባሮቹ እየተለወጡ መምጣታቸው፣ የቡና ገቢ እያደገ ይመጣል የሚል እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡

ዘንድሮ ከቡና የተገኘው ገቢ ለመጨመሩ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው፣ በዓለም ገበያ የተወሰነ የዋጋ ለውጥ መታየቱና በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ወቅት በቡና ላይ መተግበር የተጀመረው ለውጥ አስተዋጽኦ እንደነበረው የኢትዮጵያ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ግብይትና ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ይስማሙበታል፡፡

ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጀመረው የ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ፣ አገሪቱ ከዘንድሮውም በላይ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ በቡና ታስመዘግባለች ተብሎ የሚታመንበት አንዱ ምክንያትም የለውጥ እንቅስቃሴው መጀመር እንደሆነ የሚያመላክቱ ጠቋሚ መረጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ሪፎርሙ ገና ከጅምሩ ተስፋ እየታየበት ስለመሆኑም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሐምሌ 2009 ዓ.ም. የቡና ግብይት ላይ የተመዘገበው መረጃ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ምርት ገበያው በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ያገበያየው የቡና መጠንና የግብይቱ ዋጋ ከቀደመው ዓመት ብልጫ ይዞ መገኘቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግዱ ማኅብረሰብ ጋር በተነጋገሩበት መድረክ፣ ብዙ ቡና በማይላክበት የሐምሌ ወር እንኳ ከቡና የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ በቅርቡ መተግበር የጀመረው የቡና ሪፎርም ውጤት እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ 

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የታየው የለውጥ አዝማሚያ በ2010 በጀት ዓመት የቡናን የወጪ ንግድ ገቢ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንደሚያሳድገው ተስፋ አሳድሮባቸዋል፡፡

በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞት በተግባር ከታየ፣ ቡና አዲስ ታሪክ ማስመዝገቡ አይቀሬ ነው፡፡ ይኸውም በ2009 ዓ.ም. የተመዘገበው 882.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ በትንበያዎች መሠረት በአማካይ በ25 በመቶ መጨመር ከቻለ፣ ከቡና የሚገኘው ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት አዲስ ታሪክ ሆኖ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ውስጥ ከምንጊዜው ይልቅ ከፍተኛውን ድርሻ ያስገኝለታል ማለት ነው፡፡

 ለአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ወርቃማ ዕድል እንደሆነ የሚቆጠረው ሌላው ምክንያት፣ የዓለም ቡና ዋጋን በማስመልከት ከሰሞኑ ይፋ የወጡ መረጃዎች ናቸው፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ እያንሰራራ መምጣቱ ብቻም ሳይሆን፣ ቀዳሚዋ የቡና አምራችና ላኪ ብራዚል፣ የቡና ምርቷ ችግር ውስጥ መግባቱ በመሰማቱ ነው፡፡ እንደ ዓለም ቡና ድርጅት መረጃ ከሆነ፣ ባለፈው ሐምሌ ወር የቡና ዋጋ የአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ዋጋው አሁንም በመጨመር ላይ እንደሚገኝ የገበያ መረጃው ያሳያል፡፡

ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ የቡና ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተመዝግቧል፡፡ ጭማሪው በየወሩ እየታየ መቀጠሉም ድርጅቱ አስፍሯል፡፡ የቡና ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን፣ በሐምሌ ወር ለገበያ የቀረበው ከሰኔ ወር ይልቅ በመጠን ረገድ ብልጫ እንዳሳየ ታውቋል፡፡

የቡና የወጪ ንግድ እያደገ የመጣው ከገዥዎች በመጣ ከፍተኛ ፍላጎት እንደሆነ የሚጠቁመው ይህ መረጃ፣ የቡና ገዥዎች ፍላጎት መጨመር የቡና ዋጋ ከፍ እንዲል በማድረጉ፣ የዓለም ቡና ገበያ መነቃቃት እንዲታይበት አስችሏል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ላኪዎች፣ በተሻለ ዋጋ ቡናቸውን መሸጥ የሚችሉበት ዕድል በመከሰቱ፣ በ2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የቡና የወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም ሊያስመዘግብ እንደሚችል ይገመታል፡፡ አቶ ሳኒ እንደሚጠቅሱት፣ የዓለም ቡና ዋጋ መጨመሩ እርግጥ ቢሆንም፣ ጭማሪው ቀድሞ ወርዶ የነበረውን የቡና ዋጋ ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ እንደሚያስችለው አመላካች መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከእነዚህ ሁለት ዕድሎች ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ‹‹ጠንካራ ፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል›› በሕገወጥ መንገድ የሚወጣውን ቡና መጠን በመቀነስ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን መጠን ለማሳደግ ይረዳል ተብሏል፡፡ አቶ ሳኒ እንደገለጹት፣ ‹‹በመረጃ ላይ የተመሠረተ ገበያ ማራመድ ከተቻለ በቡና ላይ የተጀመሩት አዳዲስ አሠራሮች በደንብ ሲተገበሩና ሕገወጥ ተግባራትን መቆጣጠር ሲቻል የቡና ገቢም ያድጋል፤›› ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች