Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አተርፍ ብለን አጉዳይ እንዳንሆን

ሚያዚያ 2009 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ እንግዳ የሆነ ደብዳቤ ከባንኩ የፕሮጀክት ብድር ለመውሰድ ጥያቄ ላቀረቡ ደንበኞቹ ያድላል፡፡ በአጭሩ የደብዳቤው መልዕክት ለፕሮጀክት ብድር መስጠት እንዳቆመና የብድር ጥያቄያቸው ወደ ልማት ባንክ እንደተዘዋወረ የሚያስታውቅ ነው፡፡ 
ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ብድር በማቅረብ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአሁን በኋላ ለፕሮጀክት የሚሆን ፋይናንስ አልሰጥም ብሎ ሲገልጽ፣ ዕርምጃው ያልተጠበቀ ሆኖ ብዙዎችን ማስደንገጡ አልቀረም፡፡ ጥቂት የማይባሉ ብድር ጠያቂዎች ለኢንቨስትመንታቸው የጠየቁት ብድር ተፈቅዶላቸው የብድሩን መለቀቅ ይጠባበቁ ስለነበር ዕርምጃው ቢያስደነግጣቸው አይገርምም፡፡ 
ዕርምጃው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጅምር እንዲቀሩ አድርጓል፡፡ ቢያንስ ከጠቅላላ ኢንቨስትመንት ወጪያቸው እስከ 50 በመቶ ሥራ የሠሩም ነበሩበት፡፡ በተለይ ባንኩ ይለቅልናል ብለው ከሚጠብቁት ገንዘብ ውጭ ፕሮጀክቱን ለማስጨረስ የሚያስችል የፋይናንስ ምንጭ የሌላቸውን ምን ያህል እንደሚጎድል መገመት አይከብድም፡፡ ምክንያቱም ያላቸውን ገንዘብ አሟጠው ጨርሰው ባንኩ የሚለቀውን ገንዘብ ሲጠባበቁ የሰሙትን ዜና ፈጽሞ ስለማይጠብቁት ነው፡፡  
ንግድ ባንክ ለፕሮጀክት ብድር መስጠት ያቆመው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ነው፡፡ ከብሔራዊ ባንኩ ትዕዛዙ የመጣውም ንግድ ባንክ ዋና ሥራ ለፕሮጀክት ፋይናንስ ማቅረብ ባለመሆኑና ይህ ሥራ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚሠራ በመሆኑ ነው፡፡ 
እንደ መንግሥት ፖሊሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለፕሮጀክት ፋይናንስ ማድረግ አትችልም ሊባል ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ግን እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ ለፕሮጀክት በማበደር ቀዳሚ ባንክ እንደነበር መዘንጋት የለበትም፡፡ ደንበኞችም ይህንን ስለሚያውቁ ነበር ወደ ተለያዩ ፕሮጀክቶች የገቡት፡፡ ነገር ግን ለብድር ጥያቄያቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሰጣቸውን ደብዳቤ ይዘው ወደ ልማት ባንክ ሲሄዱ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከንግድ ባንክ ፈልሰው የመጡትን ተበዳሪዎች ማስተናገድ አልቻለም፡፡ 
የልማት ባንኩም የመጡትን ጥያቄዎች ሁሉ እንደማያስተናግድ እየገለጸ መለሰ፡፡ ስለተላለፈውም መመርያ ብዥታ ነበር፡፡ በተለይ የብድሩን መለቀቅ የሚጠብቁ ኢንቨስተሮች ጉዳዩን ወደዚህና ወዲያ ቢያደርጉም፣ ይኼ ነው የሚባል ምላሽ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ቆይቶ ደግሞ ንግድ ባንክ የፕሮጀክት ፋይናንስ ብድርን ወደ ነበረበት ለመመለስ እየተሠራ ነው የሚል መረጃ ወጣ፡፡ የዚህ መልስ ሲጠበቅ መልሶ ምንም ነገር ጠፋ፡፡ 
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግድ ኅብረተሰቡ ጋር ሲመክሩ  የፕሮጀክት ፋይናንስ ጉዳይ ተነስቶላቸው ነበር፡፡ የእርሳቸው መልስ የመንግሥት ፖሊሲን የሚያሳይ ነው፡፡ ልማት ባንክ የፕሮጀክት ፋይናንሶችን ጥያቄ ስለሚመልስ፣ ንግድ ባንክ እዚህ ውስጥ አይገባም አሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ አንድ የንግድ ድርጅት የንግድ ባንክ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበትና ሌሎች ንግድ ባንኮች እንደሚያደርጉት የሚሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ የልማት ሥራዎችን በተለይ መንግሥት አነስተኛ ወለድ በማመቻቸት የፖሊሲ ባንክ አድርጎ ሊጠቀመው ስለማይችል፣ ከዚህ አኳያ የልማት ባንክ ኃላፊነቱን ሊወጣ በሚችልበት ጥንካሬ ደረጃ እንዲደራጅ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን ካለው አቅም አኳያ ይህ ሊከብደው እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ልማት ባንክ ለሰጣቸው ብድሮች ሥራ ማስኬጃው ከንግድ ባንክ ይሰጥ የሚል ለመተግበር ተሞክሮ ያለመሳካቱም የሚያሳየው አሁንም በብድር አሰጣጡ ላይ ክፍተት መኖሩን ነው፡፡ 
የልማት ባንክ ፕሮጀክቶችንም ሆነ ሥራ ማስኬጃዎችንም እዚያው በመስጠት እንዲያስተዳድረው ስለተደረገ ተበዳሪዎች ዋናው ጉዳያቸው ብድሩን ማግኘታቸው ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፕሮጀክት ፋይናንስ ጠያቂዎች ልማት ባንክን ጠቁመዋል፡፡ 
‹‹የተበዳሪዎች ጥያቄ መሆን ያለበት ብድር አግኝተናል ወይም አላገኘንም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የትኛውም ባንክ ቢሆን የሚፈለገው ገንዘብ ነው፡፡ በዚህ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፤›› ቢሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግሩ ወደ ልማት ባንክ ሲሄድ የተባለውን አገልግሎት አለመገኘቱ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት እንደተረዳነው፣ መንግሥት ይኼ ፖሊሲዬ ነው ብሎ ማስቀመጥ መብቱ መሆኑን ነው፡፡ የመንግሥት የፖሊሲ ባንክ አንድና አንድ ብቻ መሆኑንና ይኼ የፖሊሲ ባንክ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ 
ንግድ ባንክ ደግሞ እንደ ማንኛውም ባንክ ተወዳድሮ የሚሠራ በመሆኑ በእንጥልጥል ላይ የነበሩ የብድር ጉዳዮች የጠራ መልስ ሳይሰጥባቸው ታልፈዋል፡፡ 
ይህ ገለጻ በፕሮጀክት ፋይናንስ ላይ አሁንም የጠራ ነገር ያለመኖሩን ያሳያል፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ የመሆኑ አንድ ነገር ሆኖ አሠራሩን በተግባር ለመለወጥ ብዙ የታሰበበት አይመስልም፡፡
በተበላሸ ብድሩ ሪከርድ የሰበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በንግድ ባንክ የተቋረጠውን የብድር ጥያቄ እንዴት ሊያስተናግድ ይችላል? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በግልጽም የፕሮጀክት ፋይናንሶችን እየተቀበለ በምን ዓይነት መንገድ እያስተናገደ እንደሆነ አልተብራራም፡፡ 
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ሲባል ሳይታሰብ ሊለቀቁ የደረሱ ብድሮች ሁሉ መቋረጣቸው አንዱና ትልቁ ስህተት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ልማት ባንክም ቢሆን ለዚህ ብቁ ደረጃ ላይ አለመሆኑ እየታወቀ፣ ለእሱ እንዲተላለፍ ከተደረገ በኋላ እየታየ ያለው አካሄድ የፕሮጀክት ብድር ጥያቄዎችን የመለሰ አልሆነም፡፡ 
ይህ ብቻ አይደለም አዲሱን አሠራር ለመተግበር ቢያንስ ጉዳያቸው ጫፍ የደረሱ ተበዳሪዎችን ጉዳይ መገምገምና ለእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ብድሩ ካልተሰጠ ምን ሊፈጠር ይችላል? ብሎ መታየት ነበረበት፡፡ ልማት ባንክ ካልቻለ ጅምር ሥራዎች ምን ሊሆኑ ነው? ይህም መታየት ነበረበት፡፡ በእንጥልጥል የነበሩ ፕሮጀክቶች በእዚያው ከቀሩ ሀብትም ንብረትም ወደመ ማለት ነው፡፡ ጉዳዩ ከዚህ አንፃርም መታየት አለበት፡፡ ለጉዳዩም ቁርጥ ያለ መልስ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ስለዚህ አተርፍ ብለን አጉዳይ እንዳንሆንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት