በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም 309 ሚሊዮን ብር በጀት ተያዘ፡፡
በአሁኑ ወቅት በችግር ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸውን ለማቋቋም ኃላፊነት የተሰጠው የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ በድጋሚ ሊቋቋሙ ይገባቸዋል ያላቸውን በመለየት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ከአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መረጃ በመውሰድ፣ የራሱን ባለሙያዎች በማሰማራት ባካሄደው ቆጠራ 7,072 አባወራና እማወራዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በአጠቃላይ ከነቤተሰቦቻቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ቁጥር 22,209 እንደሚሆን፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታምራት መክት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አቶ ታምራት እንደገለጹት፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በ2009 ዓ.ም. ቢቋቋምም በአብዛኛው ዝግጅትና ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ አርሶ አደሮችን በመለየት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃም ቢሆንም የአርሶ አደር ልጆችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ታምራት እንዳሉት፣ በ2010 በጀት ዓመት ግን ሊደገፉ የሚገባቸውን አርሶ አደሮች የበለጠ በመለየት ለማቋቋም 309 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄዱ ሰፋፊ ግንባታዎች አርሶ አደሮች ሲያፈናቀሉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ የአትሌቲክስ ማዘውተሪያና በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ በርካታ ግንባታዎች አርሶ አደሮችን አፈናቅለዋል፡፡
በልማት ምክንያት ነባር ነዋሪዎችን የማፈናቀል ጉዳይ አሁንም ቢሆን በአስተዳደሩ የሚቀጥል ቢሆንም፣ ቀደም ሲል በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በድጋሚ ለማቋቋም ከዚህ በኋላ የሚፈናቀሉ የተሟላ ድጋፍ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ ለማድረግ ታስቧል፡፡ በቂ ምትክ ቦታና በቂ ካሳ ያልተሰጣቸው፣ ምትክ ቦታ የተሰጣቸውም ቢሆኑ ለመኖሪያ አመቺ ባልሆኑ ወንዝ ዳር ቦታዎችና ተዳፋት ሥፍራዎች ላይ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃና መንገድ ስለሌሉ ጭምር ኑሯቸውን የከፋ እንዳደረገው ተፈናቃይ አርሶ አደሮቹ በየካቲት 2009 ዓ.ም. በተካሄዱ ስብሳባዎች መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ዘግይቶም ቢሆን የፌዴራል መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልማት ምክንያት ለጉዳት የተዳረጉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አምነዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል፡፡