Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊስኳር ኮርፖሬሽን በአገሪቱ የስኳር እጥረት የለም አለ

ስኳር ኮርፖሬሽን በአገሪቱ የስኳር እጥረት የለም አለ

ቀን:

  • የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አዲስ የሥርጭት ካርድ ማደል ጀመረ

ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም የከተማና የክልል ንግድ ቢሮዎች ስኳር በኮታ እያደሉ ቢሆንም፣ ስኳር ኮርፖሬሽን በየወሩ 569 ሺሕ ኩንታል እያቀረበ መሆኑንና የክምችት ችግር እንደሌለበት አስታወቀ፡፡

      ስኳር ኮርፖሬሽን 200 ለሚጠጉ የቢራ፣ የለስላሳ፣ የምግብ፣ የከረሜላና እንዲሁም ለምርቶቻቸው ስኳር ለሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች በየወሩ 170 ሺሕ ኩንታል ያቀርባል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አሥር ክፍላተ ከተሞች 112 ሺሕ ኩንታል ስኳር፣ ለክልሎች ደግሞ 287 ሺሕ ኩንታል ያቀርባል፡፡

      በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት በወጣው ኮታ መሠረት የክልል ቢሮዎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በሸማቾች ማኅበራት፣ በቀድሞዎቹ ኢትፍሩትና ጅንአድ አማካይነት ለተጠቀሚዎቹ ያከፋፍላሉ፡፡

- Advertisement -

የስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን ኮርፖሬሽኑ የስኳር እጥረትን በተመለከተ የቀረበለት ሪፖርት የለም፡፡

‹‹የአቅርቦትም የክምችትም ችግር የለብንም፡፡ ፍላጎት ማርካት ካልተቻለ እንኳ ከውጭ እናስገባለን፤›› ሲሉ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ከ3.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ያመርታሉ፡፡ ፍላጎቱን ለማሟላት ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ መጠን በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ክፍተት እንዳይኖር ያደርጋል ተብሏል፡፡

በሚቀጥለው 2010 በጀት ዓመት ደግሞ ነባሮቹን ጨምሮ ስምንት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት እንደሚገቡ፣ የአገሪቱ የማምረት አቅምም ሰባት ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ስኳር በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አለመሆኑን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየገለጹ ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን በኬንያ መንግሥት ጥያቄ መሠረት ከኢትዮጵያ 44 ሺሕ ኩንታል ስኳር ወደ ጂቡቲ መላኩ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ፣ ከተለያዩ ክፍላተ ከተሞች በተለይ የስኳርና የዘይት እጥረት እየገጠመ መሆኑ ሪፖርት እየቀረበለት ነው፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ቢሮው የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቢቆይም፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ‹‹የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አባወራና እማወራ ከቸርቻሪ ሱቆች ጋር ለማስተሳሰር የተዘጋጀ የሥርጭት ካርድ›› የሚል የግብይት ካርድ ማደል ጀምሯል፡፡

የሥርጭት ካርዱ እንደሚያብራራው አንድ አባወራ/እማወራ ወርኃዊ የስኳር ኮታ አምስት ኪሎ ግራም፣ የዘይት ኮታ ደግሞ እስከ አምስት ሊትር ድረስ ነው፡፡ የዘይት መጠኑ እንደየአቅርቦቱ የሚለያይ ይሆናል ይላል፡፡

‹‹የሥርጭቱ ካርድ በየ15 ቀናት ወይም በወር ለአንድ ጊዜ ግብይት የሚያገለግል ነው፤›› ይላል አዲሱ የግብይት ካርድ፡፡ ይህ አዲስ የመገበያያ ካርድ የተዘጋጀው ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ካለ መደብር እንዲገበዩ ለማድረግና ክልከላን ለማስቀረት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይህ አሠራር በቅርቦትና በፍላጎት መካከል አለመጣጣም መኖሩን ያሳያል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚገልጹት ግን፣ በዚህ ንግድ ዘርፍ የአየር በአየር ንግድ በመኖሩና በኮንትሮባንድ ስኳር ከአገር የሚወጣ በመሆኑ ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡

ኤክስፖርቱን በተመለከተ አቶ ጋሻው ሲያስረዱ፣ በዓለም ብራዚልና ታይላንድ ብቻ ስኳር ወደ አገራቸው አያስገቡም፡፡ ሌሎች አምራች አገሮች ግን ጥሩ ዋጋ ሲያገኙ ኤክስፖርት ያደርጋሉ፡፡ በአገራቸው እጥረት ሲከሰት ደግሞ ጥሩ ዋጋ ከሚያገኙበት ገበያ ኢምፖርት ያደርጋሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዚህ መሠረት በአገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ስትራቴጂ መንደፉን አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

‹‹የኬንያ ጥያቄ የመጣው ይህንን ስትራቴጂ በነደፍንበት ወቅት ነው፤›› ሲሉ አቶ ጋሻው የኮርፖሬሽኑን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ምርቶች አዲስ ገበያ እየሆነች ወደመጣችው ኬንያ ስኳር በ110 ተሽከርካሪዎች እየተጓዘ ባለበት ወቅት ግን ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡

ለችግሩ መነሻ የሆነው ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በሚወስደው መንገድ ላይ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ ከ280 ኩንታል በላይ መጫን አለመቻሉ ነው፡፡ ነገር ግን ከወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የተነሱት ከባድ ተሽከርካሪዎች 400 ኩንታል ጭነው፣ አስፈላጊውን ሰነድ አሟልተው፣ እንዲሁም ተሽከርካሪዎቹ ለቆሙበት ዴሚሬጅ የሚከፍለው አካል ባለመለየቱ ለቀናት ተጉላልተው እንደነበር ታውቋል፡፡

አቶ ጋሻው እንዳሉት ይህ ችግር ተፈትቶ ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተሽከርካሪዎቹ ወደ ኬንያ ጉዞ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...