Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሜሳ የንግድና የልማት ባንክ ለሦስት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ማሔ ደሴት ሲሼልስ

ራሱን በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የንግድና የልማት ባንክ በማለት ስያሜውን ያሻሻለው የቀድሞው ፒቲኤ (Preferential Trade Agreement- PTA Bank)፣ በዚህ ዓመት ጥር ወር ይፋ ባደረገው መሠረት ለሦስት ኩባንያዎች በአጠቃላይ የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጥያቄ ቀርቦት ሲመለከት ቆይቶ ፈቀደ፡፡

የባንኩ 33ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ በሲሼልስ በተካሄደበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ፣ እንዲሁም እንይ ጄኔራል ቢዝነስ በጠቅላላው የ60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጥያቄያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ ባንኩ ብድሩን ለቆላቸዋል፡፡

አዲሱን ስያሜውን በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እንይ ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ፣ እንዲሁም ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እያንዳንዳቸው የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ከሦስቱ ኩባንያዎች በተጨማሪ ሌሎችም በድርድር ሒደት ላይ የሚገኙ እንዳሉና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴል ለመክፈት በካሊብራ አማካሪ ኩባንያ አማካይነት ከፈረንሣዩ አኮር ግሩፕ ጋር ስምምነት ያደረገው እንይ ኩባንያ፣ አኮር ከሚያስተዳድራቸው ውስጥ ፑልማን የተባለውን ብራንድ ሆቴል በኢትዮጵያ ለመክፈት የ20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውና ከፈረንሣይ አበዳሪ ተቋማት ብድሩን ለማግኘት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ ተቋም (ኮሜሳ) ባንክ ከሆነው የንግድና የልማት ባንክ ብድሩ ስለተለቀቀለት፣ የሆቴል ፕሮጀክቱን በቅርቡ ዕውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያም ያቀረበው የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመለቀቁ፣ የብረታ ብረት ፋብሪካውን ዕውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

አቶ አድማሱ በሲሼልሱ ጉባዔ ወቅት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች የሚውል 600 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመልቀቅ ባንካቸው ዝግጁ ነው፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥም በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ብድር ለኢትዮጵያ ለመስጠት ባንኩ ፍላጎት እንዳለው ይፋ አድርገዋል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ በስኳር ልማት፣ በኢነርጂ፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋቸክሪንግና ለሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለሚያመርቱ ዘርፎች ማበደር የሚቻልበት ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመኖሩ እንደሆነ አቶ አድማሱ ጠቁመዋል፡፡

የአሁኑ የንግድና የኢንቨስትመንት ባንክ ከዚህ ቀደም ለሐበሻ ሲሚንቶ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁን አቶ አድማሱ አስታውሰዋል፡፡ ከሐበሻ ሲሚንቶ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ተቋማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ብድር እንደሚለቀቅለት መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ይሁንና የብድሩ ዓይነት በአብዛኛው የአጭር ጊዜ በመሆኑ ለተበዳሪ ተቋማት በተለይም ለንግድ ባንክና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጠው ብድር በየጊዜው እንደሚለዋወጥ ገልጸው፣ በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብድር ባስፈለገው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርብለት አስታውቀዋል፡፡

ከወራት በፊት ባንኩ በታሪኩ በአንድ ጊዜ ሲፈቅድ የመጀመርያው የሆነውን የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኬንያ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ የባንኩን ስያሜ መቀየር ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል በየጊዜው እያደገና ለውጥ እያሳየ ከመምጣቱ ጋር እንደሚያያዝ፣ ከዚህም በተጨማሪ የኮሜሳ አባል ያልሆኑ አገሮችንም ለማካተት ታስቦ እንደሆነ ያወሱት አቶ አድማሱ በዚህም እንደ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ ያሉ አገሮች በቅርቡ ወደ አባልነት መቀላቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ማዳጋስካር ያሉ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ ደሴቶችም ባንኩን ለመቀላቀል እየተቃረቡ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኩ 21 አባል አገሮችን ጨምሮ አሥር ተቋማት አክሲዮን በመግዛት የባንኩ ባለድርሻ መሆናቸው ታውቋል፡፡

እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማትን በባለድርሻነት ያቀፈው ይህ ባንክ፣ በአቶ አድማሱ መመራት ከጀመረ ወዲህ የነበረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ችሏል፡፡ ለዚህ ለውጥ ትልቁን ሚና የተጫወቱት አቶ አድማሱ በአባል የቦርድ ገዥ አገሮች ዘንድ ተሞካሽተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ ባንኩን ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ሲመሩም የባንኩን ጠቅላላ ሀብት በእጥፍ በማሳደግ ወደ አሥር ቢሊዮን ዶላር የሚያደርሱበት፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም ከእጥፍ በላይ በማደግ ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስበት፣ የባንኩ የተጣራ ትርፍ አሁን ካለው 101 ሚሊዮን ዶላር ወደ በ180 ሚሊዮን ዶላር ከፍ የሚልበትን የኮርፖሬት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የቦርድ አባላት አፅድቀውላቸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች