Friday, July 19, 2024

አስመሳዮች በተሰባሰቡበት ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ይበዛል!

አስመሳይነት የአድርባዮች መገለጫ ነው፡፡ በዚህ ድርጊት የሚታወቁ ሰዎች ደግሞ በሞራልና ሥነ ምግባር ዝቅጠት፣ በራስ ወዳድነት፣ በማይገባ ጥቅም ፈላጊነት፣ በዓላማ ቢስነት፣ በብቃት የለሽነትና በሕገወጥነት ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ደግሞ በመንግሥት የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ በብዛት አሉ፡፡ አስመሳዮች የተሰባሰቡበት መንግሥት ደግሞ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን እያቃተው ሰበብ መደርደር ይወዳል፡፡ የረባ ዕቅድ ሳይኖረው ይቀርና የሚጠበቀው ውጤት ሲጠፋ የአፈጻጸም ጉድለት ይጠቀሳል፡፡ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ዕቅድ ግን በጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ስለሚታገዝ ውጤቱ አመርቂ ነው፡፡ ብቃት ያላቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ያቀዱትን አሳክተው በድል ሲገሠግሡ፣ ደካሞችና አስመሳዮች ግን ሁሌም ሰበብ አያጣቸውም፡፡ ለእነሱ ሥራ ማለት ወሬና መፈክር ብቻ ነው፡፡ ቀልባቸው ሁሉ ያለው ሌብነት ላይ ስለሆነ ሲሰርቁ እንኳ በአደባባይ ሕግ እየጣሱ ነው፡፡ ካለማፈራቸው የተነሳ ሙስናን ለማውገዝና ያለኛ ማንም የለም ለማለት ደግሞ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ለአገር ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ለመብቶች መከበርና ለእኩልነት ደንታ የላቸውም፡፡ በእነሱ ምክንያት ሕዝብ መንግሥትን ቢጠላ ምን ይገርማል?

አስመሳዮች እንደምንም ተንጠላጥለው ያገኙትን ሹመት ላለማጣት ግን እንቅልፍ የላቸውም፡፡ በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ዓላማ ስለሌላቸው፣ ሀቀኞችንና አገር ወዳዶችን በማበሳጨት የሥራ አካባቢዎችን ይረብሻሉ፡፡ በቅጥር፣ በምደባ፣ በዝውውር፣ በዕድገት፣ በልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችና በትምህርት ዕድሎች አድልኦ በመፈጸም የሠራተኞችን ሞራል ይገድላሉ፡፡ የአገልጋይነት ስሜትን ያጠፋሉ፡፡ በመላ አገሪቱ ለመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ለፍትሕ መጓደል፣ ለሙስና መስፋፋት፣ ለኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል መፈጠር፣ ለሕዝብ ቅሬታዎች መበራከትና ለመሳሰሉት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ሕገወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደ መከላከል በምን ቸገረኝ ያልፋሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮች እንዲሰፍኑ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ፍትሕ ሲዛባ ግድ የላቸውም፡፡ ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ያስቀድማሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአባልነት የተጠለሉበትን ፓርቲና መንግሥት ሳይቀር ለጉዳት ይዳርጋሉ፡፡ የመውቀስ፣ የማረምና የመገሰፅ ኃላፊነት እንዳለባቸው እያወቁ፣ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ እያሳደዱ ገደሉን ሜዳ ነው ይላሉ፡፡ የአስመሳይነታቸው ደረጃ ከፍ ያለ በመሆኑም በሐሰተኛ መረጃና ሪፖርት ማሳሳት ተግባራቸው ነው፡፡ በአገር ላይ ነውጥና ሁከት ሲቀሰቀስ ደግሞ ይደበቃሉ፡፡ ትንፍሽ አይሉም፡፡

ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት የሚያጣው በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ችግር ሲፈጠርበት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት እንዳይበላሽ ኃላፊነት ያለባቸው በየደረጃው ያሉ ተቋማትና ኃላፊዎቻቸው ተጠያቂነት ሊኖርባቸው ይገባል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ሕዝብ አቤቱታ ሲያቀርብ የሚያዳምጠው አይኖርም፡፡ ሌላው ቀርቶ የሕዝብ አቤቱታና ቅሬታ ማስተናገድ የሚገባው ተቋምና ተሿሚ ጭራሽ በእሱ ብሶ የበለጠ ቅሬታ ሲፈጥር ይታያል፡፡ አገልግሎት በሚሰጡ መንግሥታዊ ተቋማት ተቆጣጣሪ የሌለ እስኪመስል ድረስ በአደባባይ ምልጃ ሲጠየቅና አገልግሎት ሲነፈግ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ‹ጉዳይ ገዳይ› የሚባሉ ወንበዴዎች ተፈልፍለዋል፡፡ ተቋማቱ በአስመሳዮች ስለሚመሩ ትክክለኛ አሠራር ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህ መሀል ግን ግብር ከፋዩ ሕዝብ አሳሩን ያያል፡፡ ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ እየበዛ ነው፡፡ የአገር መውደድ ስሜት እየቀዘቀዘ ግለኝነት ተንሠራፍቷል፡፡ ነገን አሸጋግሮ ከማየት ይልቅ ዛሬ ላይ መቆዘም በርትቷል፡፡ ራዕይ አልባዎች አገርን ጃርት የበላው ዱላ እያስመሰሉ ነው፡፡

ተቋማት በፅኑ መሠረት ላይ ተገንብተው ለዕድገት የሚያግዙ ውጤታማ ዜጎች ካልተሰማሩባቸው፣ አሁን ባለው ደመነፍሳዊና ልማዳዊ አሠራር መቀጠል አይቻልም፡፡ በትምህርት፣ በልምድና በሥነ ምግባር የተኮተኮቱ ዜጎች ተቋማትን እንዲያጠናክሩና የተሻሻሉ አሠራሮችን እንዲዘረጉ ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህ ዘመን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ግስጋሴ የታደለ በመሆኑ፣ በደመነፍስ የሚመሩ ተቋማት ነፍስ እንዲዘሩ መደረግ አለበት፡፡ ከዘመኑ ጋር በማይመጥን ኋላቀር አስተሳሰብ የተተበተበው ቢሮክራሲ ትንሳዔ ሊያገኝ ይገባል፡፡ አገር በመፈክርና በንድፈ ሐሳባዊ ትንተናዎች ብቻ የትም አትደርስም፡፡ ከዕቅድ አወጣጥ ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ድረስ ሳይንሳዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለተሻሉ ሐሳቦችና አሠራሮች ዕድሉን መስጠት የግድ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት የተገኘባቸው ልምዶች ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር እንዲጣጣሙ ተደርጎ ተግባራዊ እንዲደረጉ፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር በብዛት እንዲደረግ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች በብዛት እንዲኖሩና አገሪቱ በተፈጥሮ የታደለቻቸውን ፀጋና በረከቶች እንድትጠቀምባቸው ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ይህ ብርቱ ምኞት ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ የግድ ይላል፡፡ ከአስመሳይነትና ከአድርባይነት የፀዳ ለውጥ፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ አገር ናት፡፡ ሕዝቧ ዓለም የመሰከረለት ጀግንነት ባለቤትና በተምሳሌትነቱም ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ይህ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚወደው አገሩን ነው፡፡ ለዚህች የተከበረች አገር ደግሞ ሕይወቱን ለመሰዋት አያንገራግርም፡፡ በዚህ መሀል ግን ከራሳቸውና ከመሰሎቻቸው ጥቅም በላይ አርቀው የማያዩ አስመሳዮች አሉ፡፡ እነዚህ አስመሳዮች ደግሞ ከመንግሥት መዋቅር ጀምሮ በየሥፍራው ተቀፍቅፈዋል፡፡ በአገር ፍቅር ጭምብል ውስጥ ሆነው አገር የሚያጠፉ አስመሳዮችም አብረዋቸው አሉ፡፡ እነዚህን ሥፍራ ማሳጣት ተገቢ ነው፡፡ መሠረታዊ ለውጡ መጀመር ያለበትም ከዚህ ነው፡፡ በመጀመርያ ሕግ መከበር አለበት፡፡ አስመሳይነት በሕገወጥነት ውስጥ የተደበቀ እኩይ ጠላት ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት እንዳይፈጠር፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲጣሱ፣ የአገር አንጡራ ሀብት በወረበሎች እንዲዘረፍ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የሚረዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት እንዳያብቡ፣ ዜጎች በነፃነት የመሰላቸውን እንዳይናገሩ፣ ወዘተ. በማድረግ አገሪቱን ሲኦል ያደርጋታል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ይህ እኩይ ድርጊት ለዚህች የተከበረች አገርና ለዚህ ኩሩ ሕዝብ አይመጥንም፡፡ በፍጥነት አሽቀንጥሮ መጣል ያስፈልጋል፡፡

ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን መሆን የሚችሉት ማኅበራዊ ፍትሕ ሲኖር ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚሰፍነው ደግሞ በሕግ የበላይነት ብቻ ነው፡፡ በዜጎች መካከል ያለው ግንኙንት በእኩልነት ላይ ሲመሠረትና ማኅበራዊ መስተጋብሩ ጤነኛ ሲሆን ግን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥርጊያው ይመቻቻል፡፡ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል የመጫወቻ ሕግና ሜዳ ላይ ሲወዳደሩ፣ ሁሉም መሠረታዊ መብቶች ሲከበሩ፣ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ነፃነት ሲሰማቸውና ከፍርኃት ቆፈን ውስጥ ሲወጡ ሰላማዊው ድባብ ይፈካል፡፡ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሙስና ቦታ አይኖራቸውም፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ወሳኝ ሲሆንና የፈለገውን ሲሾምና ሲሽር፣ የፖለቲካው ዓውድ ሰላማዊ ይሆናል፡፡ ግጭትና መቆራቆስ ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያለው ግን ብሔርን፣ ቋንቋን፣ እምነትን፣ ባህልን፣ የፖለቲካ አቋምንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን አንድ ላይ በመጠርነፍ አገርን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡ ወይም እነዚህን ልዩነቶች በማባባስ ትርምስ መፍጠር ነው፡፡ ብዝኃነት በአስተሳሰብ ጭምር በመሆኑ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ግን በአስመሳይነት የተተበተበው አሠራር ፈር ሊይዝ ይገባል፡፡ አስመሳዮች በተሰባሰቡበት ዴሞክራሲን ማለም አይቻልም፡፡ እኩልነትን መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ በአጠቃላይ አስመሳዮች በተሰባሰቡበት ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ይበዛል! ይህ ደግሞ ለአገር በፍፁም አይጠቅምም!

  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...