Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በቅንነት እየሠራ እንዳልሆነ ፍርድ ቤት ተቸ

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በቅንነት እየሠራ እንዳልሆነ ፍርድ ቤት ተቸ

ቀን:

  • ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምርመራውን እንዲከታተል ታዘዘ
  • በቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ተጠናቀቀ

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት በስኳር ኮርፖሬሽን የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ በእነ አቶ ዘነበ ይማም ላይ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተፈቀደለት ጊዜ የፈጸመው የምርመራ ሥራ ‹‹ፍርድ ቤቱን የማይመጥን፤›› እና ቅንነት የጎደለው መሆኑን ዳኞች ተናገሩ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች እንዳሉት፣ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ ተፈቅዶለት በነበረው ጊዜ የፈጸመው ተግባር ‹‹ፍርድ ቤቱን የማይመጥን›› ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህንን የተናገረው ለአራተኛ ጊዜ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡት የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ አምስት ተጠርጣሪ ሠራተኞች ላይ፣ መርማሪ ቡድኑ ተፈቅዶለት በነበረው የምርመራ ጊዜያት የሠራውን ካስረዳ በኋላ ነበር፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት ጊዜ የአራት ምስክሮች ቃል መቀበሉን የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ገልጾ፣ የኦዲት የምርመራ ግኝት እንደሚቀረው በመናገር ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

- Advertisement -

የምርመራ መዝገቡን ተቀብሎ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፣ መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት ጊዜ የሠራው ነገር እንደሌለና መዝገቡ የሚያሳየው ቀደም ብሎ የተሠሩ የምርመራ ግኝቶችን እንደሆነ ገልጿል፡፡ በተፈቀደለት 14 ቀናት ውስጥ የአራት ሰዎችን የምስክርነት ቃል ብቻ መቀበል ተገቢ እንዳልሆነ የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ መርማሪ ቡድኑ በቅንነት እየሠራ እንዳልሆነ ጠቁሟል፡፡ መርማሪዎች በሥርዓት መሥራት ሲገባቸው ምርመራውን በጣም እያጓተቱ መሆኑን ገልጿል፡፡

ቀደም ባለው ችሎት በተመሳሳይ ተቋም ውስጥ የተጠረጠሩ ኃላፊዎችና ግለሰቦች በአንድ መዝገብ ተጠቃለው እንዲቀርቡ ተብሎ የተሰጠውን ትዕዛዝ አለመፈጸማቸውም ሥራ እንዳልተሠራ ማሳያ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በተፈቀደው ጊዜም የተሠራውም ሆነ መርማሪ ቡድኑ ይቀረኛል ያለው የምርመራ ሒደት አግባብነት እንደሌለው ከተገለጸ በኋላ፣ ለሥራው ትኩረት አለመስጠት እንጂ ልምድ ያላቸው መርማሪዎች መኖራቸውን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በበኩሉ የተጠርጣሪዎቹን የሥራ መዘርዝር ለማምጣት በክልል የሚገኙ የስኳር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶች የሄደ ቢሆንም፣ ሊያገኝ አለመቻሉን ተናግሯል፡፡ ምርመራውን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻለውም ተጠርጣሪዎች ማስረጃዎችን በማሸሽ ችግር ስለፈጠሩበትም እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ዋስትና ቢፈቀድላቸውም የበለጠ ማሸሽና መደበቅ ስለሚችሉ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ፣ የተጠርጣሪዎች የሥራ መዘርዝር በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ቢጠፋ በዋና መሥሪያ ቤት ዓቃቤ ሕግ በመመደብ እንደሚገኝ አስረድቶ፣ ዜጎች ያለተጨባጭ ነገር ታስረው መቆየት እንደሌለባቸውና ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ መሥራት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ የምርመራ ሒደቱ የጥራትና የመጓተት ችግር እንዳለበት በመጠቆም፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የመርማሪ ቡድኑን አሠራር እንዲከታተል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ሥራውን አጠናቆ እንዲያቀርብ ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ለጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የኮሚሽን ሠራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ ከኦሞ ኩራዝ አምስት 15 ሚሊዮን ብር በመቀበል የተጠረጠሩት ክስተት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት መሆናቸው የተገለጸ አቶ ሳልሳዊ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉ ተጠርጣሪ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ተጠርጣሪው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ምርመራ መዝገብ ለነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተቀጠሩ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ያሉ በመሆናቸው፣ እሳቸውም አብረው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በእነ ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ የምርመራ መዝገብ፣ የጀመረውን መጨረሱንና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም በዕለቱ የቀረቡትን ዓቃቤ ሕግ መቼ እንደተረከቡ ጠይቆ ‹‹ዛሬ ተቀብለናል›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ክስ ለመመሥረት በሕጉ መሠረት 15 ቀናት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከተጠየቀው 10 ቀናትን በመፍቀድ፣ ለመስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ክስ ያልተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ባሉበት በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...