Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቤጂንጉ የኪነጥበብ ማዕከል

የቤጂንጉ የኪነጥበብ ማዕከል

ቀን:

ወደ ቻይና መዲና ቤጂንግ ሲያቀኑ መጎብኘት ይገባዎታል ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ ሰቨን ናይን ኤይት (798) አርት ዞን የተሰኘው የኪነጥበብ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ የበርካታ ጠቢባን መዳረሻ በመሆኑ ጎብኚዎች ዘወትር ወደ ሥፍራው ይጎርፋሉ፡፡ በተለምዶ ዳሸንዚ አርት ዲስትሪክት በመባል የሚታወቀው የኪነጥበብ ማዕከል ውስጥ ጋለሪዎች፣ የባህላዊ ቁሳቁስ መሸጫ ሱቆች፣ ሲኒማ ቤቶችና ሌሎችም ጥበባዊ ክንዋኔዎች የሚያስተናግዱባቸው ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

የኪነጥበብ ማዕከሉ ቀድሞ የአገሪቱ ወታደራዊ ቁሳቁሶች የሚመረቱበትና የሚከማቹበት ነበር፡፡ ሰቨን ናይን ኤይት የሚለውን ስያሜውን ያገኘውም ወታደራዊ ማዕከል በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ማዕከሉ ዛሬ ቻይናውያን ፊልም ሠሪዎች፣ ሠዓሊዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ቀራፂዎች፣ ፎቶ አንሺዎችና ሌሎችም ኪነጠቢባን መገኛ ነው፡፡ የትኛውንም ዓይነት ጥበባዊ ሥራ ለማዘጋጀት እንዲሁም ለሕዝብ ለማድረስ በቂ ቦታ ያለው ማዕከሉ፣ በአንድ ቀን ጉብኝት የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡

ከ60 ሔክታር በላይ በሆነው ማዕከሉ፣ ከቻይናውያን አርቲስቶች በተጨማሪ ከሌሎች አገሮች ሥራዎቻቸውን ለማሳየት ወደ ቻይና የሚጓዙም ይስተናገዳሉ፡፡ የቻይና ኮንቴምፖራሪ አርት መጎምራት ሲጀምር አርቲስቶቹ ለሥራቸው ምቹ ሆኖ ያገኙት ሰመር ፓላስ የተባለውን ጥንታዊ የቻይና ቤተ መንግሥት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1984 እስከ 1995 አብዛኞቹ የኪነጥበብ ሥራዎች በቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ ይከናወኑም ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ1995 የቤጂንግ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ሴንትራል አካዴሚ ኦፍ ፋይን አርትስ፣ አርቲስቶች በሰቨን ናይን ኤይትን እንደ ማዕከል እንዲገለገሉበት ዕድሉን አመቻቸ፡፡ የትምህርት ቤቱ የቅርፃ ቅርፅ ትምህርት ክፍል ዲን ስቱዲዮውን በማዕከሉ ካዞረ በኋላም በርካታ አርቲስቶች አርአያውን ይከተሉ ጀመር፡፡

በመቀጠል ቻይናውያንና የሌሎች አገሮች ባለሙያዎችም ማዕከሉን መቀላቀሉን ተያያዙት፡፡ ማተሚያ ቤቶች፣ የመጻሕፍት መደብሮችና የልብስ ዲዛይን ማሳያ ክፍሎች በማዕከሉ ሲከፈቱ የጎብኚዎች ቁጥርም እየናረ ሄደ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2002 ‹‹ቤጂንግ አፍሎት›› የተሰኘ ዐውደ ርእይ ሲከፈት ከ1ሺሕ በላይ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡

በማዕከሉ ዓለም አቀፍ የሥዕልና ፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዮች፣ የፊልም ፌስቲቫሎች፣ የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ፡፡ ማዕከሉን በጎበኘንበት ወቅት ቋሚ ዐውደ ርእይ ያላቸው ጋለሪዎች ተመልክተናል፡፡ ስቱዲዮዋቸው ውስጥ ሆነው በተመስጦ የሚሥሉ አርቲስቶች መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ የማዕከሉ ጥግ በብረት፣ በፕላስቲክና ሌሎችም ቁሳቁሶች የተሠሩ ቅርፆች ይታያሉ፡፡ የተለያየ ይዘት ያላቸው ሥዕሎች በየጋለሪዎቹ መግቢያ ግርግዳዎች ይገኛሉ፡፡ የልጆችና የአዋቂዎች ሲኒማ ቤቶች በፊልም ተመልካቾች ተጨናንቀውም አስተውለናል፡፡ በማዕከሉ ከተለያዩ አገሮች በተውጣጡ ሼፎች የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ ሬስቶራንቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ተመጋቢዎች ያዘዙት ምግብ እስከሚደርስ የሚዝናኑበት አማራጭም አላቸው፡፡

የንቅሳትና የሒና አርቲስቶች የማዕከሉ ሌላኛው ገጽታ ሲሆኑ፣ ቤተ መቅደሶችና የቤት ቁሳቁስ መሸጫ መደብሮችም ይገኛሉ፡፡ ከተቀረው ዓለም ገለል ባለ መልኩ በራሳቸው ዓለም የሚኖሩት ቻይናውያን፣ በማዕከሉ በመጠኑም ቢሆን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለመተሳሰር ሲጣጣሩ ይስተዋላል፡፡ በማዕከሉ ያገኘናቸው ሰዎች ሰቨን ናይን ኤይት ነፃ ቦታ እንደሆነና ማንኛውም ዓይነት አመለካከት ያለው ያሰው ሐሳቡን እንደሚገልጽበት አስረድተውናል፡፡

ጥበባዊ ሥራዎቹ የማኅበረሰቡን ነባራዊ ሕይወት መሠረት ያደረጉ ሲሆን፣ የአገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ገጽታ የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ በከተማ ቀመስና ገጠራማ የቻይና ከተሞች ያለውን ሕይወት በፎቶግራፍ፣ በቅርጻ ቅርጽና በቪዲዮ የሚያሳዩ አርቲስቶችም ገጥመውናል፡፡ ከነዚህ መካከል የሩዝ እርሻን እንደመነሻ የወሰደው አርቲስት ይጠቀሳል፡፡ ሰፊ የሩዝ ማሳን የሚወክል ቅርጽ እንዲሁም አርሶ አደሮችን የሚያሳዩ ሥዕሎች በስብስቡ ተካተዋል፡፡ ማዕከሉ በቻይና ሥነ ጥበብ ስመጥር ከሆኑ አርቲስቶች አንዱ የሆነው አይ ዌዌን የመሰሉ ባለሙያዎችና አማተሮችንም ያቅፋል፡፡ የጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ታዳጊዎች ሙያቸውን የሚያዳብሩበት ቦታም የማዕከሉ አካል ነው፡፡

በማዕከሉ ለሽያጭ ቀርበው የተመለከትናቸው ባህላዊ ቁሳቁሶች ከቻይና ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አገሮችም የተውጣጡ ናቸው፡፡ ቻይና የቱሪስቶች መዳረሻ ከሆኑ አገሮች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እንደመሆኗ የየአገራቸውን ባህላዊ ቁሳቁሶች ለማስተዋወቅና ለመሸጥም ተመራጭ ቦታ በመሆኑ ማዕከሉን እንደመረጡት የገለጹልን ሻጮች ነበሩ፡፡ ከዓመታት በፊት መንግሥት ማዕከሉን አፍርሶ ዘመነኛ ገጽታ የማላበስ እቅድ እንዳለው ቢያሳውቅም ቦታው የጥንታዊ ቻይና ኪነ ሕንፃ አሻራ በመሆኑ መፍረስ እንደማይገባው የሚያምኑ አርክቴክቶች እንደተቃወሙም ገልጸውልናል፡፡

በማዕከሉ ውስጥ የሚሠሩ አርቲስቶችና አብዛኞቹ ጎብኚዎችም በሳይክል ይንቀሳቀሳሉ፡፣ ከሰቨን ናይን ኤይት መግቢያ በር አንስቶ በማዕከሉ የሚገኙ ቦታዎችን በቀላሉ ለመጎብኘት ምቹ የሆነው የትራንስፖርት አማራጭ ሳይክል ሲሆን፣ በማዕከሉ ሳይክል ተቆልፎ የሚቆምባቸው የፓርኪንግ ቦታዎችም ይገኛሉ፡፡

በማዕከሉ ስንዘዋወር ካስተዋልናቸው ጋለሪዎች መካከል የጃፓንና የታይዋን ጋለሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በማዕከሉ ወደ 400 የሚደርሱ የባህል ተቋሞች መኖራቸውንም በጋለሪዎቹ ያገኘናቸው ባለሙያዎች ገልጸውልናል፡፡ የፈረንሣይ፣ ጣልያን፣ እንግሊዝ፣ ቤልጄየም፣ ጀርመንና አውስትራሊያ ተቋሞች ተጠቅሽ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ በየዓመቱ የጥበብ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ የማዕከሉን እውቅና እንደጨመረም ባለሙያዎቹ ያምናሉ፡፡

እንደ ቻይና ካሉ አገሮች በተቃራኒው የታዳጊ አገሮች የኪነጥበብ ዘርፍ ከሚፈተንባቸው ነገሮች ቀዳሚው በቂ ቦታ አለማግኘት ነው፡፡  ኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ባለሙያዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑበት፣ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር የሚገናኙበትና ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበት መድረክ እምብዛም አይደለም፡፡ እንደ ሰቨን ናይን ኤይት ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች የሚያስተሳስር ማዕከል ማግኘት ደግሞ ከምንም በላይ ከባድ ነው፡፡ የቤጂንጉ የኪነጥበብ ማዕከል፣ ለአርቲስቶች ጥያቄ ምላሽ ከመስጠቱም በላይ፣ ሙያዊ ነጻነታቸው ተከብሮ ሐሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት ዕድል ተመቻቶላቸዋል፡፡

በማዕከሉ ሲዘዋወሩ በአንድ ግርግዳ ጥግ በተለያዩ ቀለማት የተጻፉ ቀና መልዕክቶች እንዲሁም ጥበባዊ ነፃነትን የሚወክሉ ምልክቶች  ያስተውላሉ፡፡ የሚታዩት ጥበባዊ ሥራዎች በአሠራርና በይዘትም ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው፡፡ ከማዕከሉ ጎዳናዎች በአንዱ በብረት አጥር ውስጥ የሚገኙ ሦስት ግዙፍ ድራጎኖች አንዳቸው በሌላቸው ተደራርበው ይታያሉ፡፡ በሌላው ጎዳና የወደፊት ሕይወቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠይቅ ታዳጊ የአባቱን መጻፍ ይዞ ይስተዋላል፡፡

ማዕከሉ ከጠዋት ጀምሮ አስከ ምሽት ክፍት ስለሆነ ብዙዎች ማልደው ሔደው ቀኑን ሙሉ ማሳለፍ ይመርጣሉ፡፡ በሚታዩት ሥራዎች በየጊዜው አዲስ ነገር ስለሚታከል የቤጂንግ ነዋሪዎች ከሌሎች አገር ዜጋዎች ባልተናነሰ ማዕከሉን ያዘወትራሉ፡፡ እንደ ትሪፕ አድቫይዘርና ሎንሊ ፕላኔት ባሉ ዓለም አቀፍ የጉብኝት ድረ ገጾች ስለ ማዕከሉ ዝና ብዙ ተጽፏል፡፡ የቻይናውን ትራቭል ቻይና ጋይድ ጨምሮ ሌሎችም መገናኛ ብዙኃንም ቦታውን አወድሰዋል፡፡

በሰቨን ናይን ኤይት ዕውቅ ከሆኑ ጋለሪዎች መካከል ዩሲሲኤ ተጠቃሽ ሲሆን፣ ከቻይናዊው አይ ዌዌ በተጨማሪ እንደ ሉሺያን ፍሮውድና አንዲ ዋሮል ያሉ ዓለም አቀፍ አርቲስቶችም ሥራቸውን አቅርበውበታል፡፡ ልብስ ዲዛይን የሚደረግባቸው እንዲሁም የፋሽን ትርኢት የሚቀርብባቸው አዳራሾችም በብዙዎች ይወደዳሉ፡፡ በማንደሪን እንዲሁም በሌሎች ቋንቋዎችም የተጻፉ መጻሕፍት የሚሸጡባቸው መደብሮችም ይገኛሉ፡፡

በኪነጥበብ ማዕከሉ ከቤት ውጪ (አውትዶር) የሚጎበኙት ቅርፃ ቅርፆች የብዙዎችን ትኩት ይስባሉ፡፡ አብዛኞቹ ቅርፆች ግዙፍ ሲሆኑ፣ የምሥራቁ ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች ምሥል ይገኝበታል፡፡ በማዕከሉ የሚገኘው ዲ ፓርክ የተሰኘ ፓርክ ለእግረኞች ምቹ ተደርጎ የተሠራ ነው፡፡ ፓርኩን ለመጎብኘት ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውና ከመምህራኖቻቸው ጋር የተገኙ ታዳጊዎች ተመልክተናል፡፡ ወጣት ጥንዶችና በማዕከሉ የሚሠሩ አርቲስቶችም መንፈሳቸውን ለማደስ ወደ ዲ ፓርክ ያቀናሉ፡፡

ማዕከሉ በርካታ ጥበባዊ መዳረሻዎችን በአንድ አቅፎ መገኘቱ በዓለም ላይ መጎብኘት ካለባቸው 22 ቦታዎች አንዱ አድርጎታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 ታይም መጋዚን ‹‹ዋን ኦፍ ዘ ቶፕ 22 ሞስት ፌመስ ላንድማርክስ ስሩ አውት ዘ ወርልድ›› በሚል ማዕከሉ በዓለም ካሉ 22 ድንቅ ሥፍራዎች አንዱ መሆኑን አትቷል፡፡

በማዕከሉ የኢንተርየር ዲዛይን ባለሙያዎች የቤት ውስጥ ዲዛይን ሞዴል የሚያሳዩበት ክፍል ይገኛል፡፡ በቅርብ ርቀት የወጣት ድምፃውያን ስቱዲዮዎች ያሉ ሲሆን፣ በተለይም በቻይና ዘመናዊ ሙዚቃ  ተፅዕኖ እየተፈጠሩ ያሉ ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸው ለሕዝብ ጆሮ ከመድረሳቸው በፊት የሚያቀናብሩበት ቦታ ነው፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ጊዜ አልፎበታል ተብሎ የሚነሳ ወይም የሚጣል ነገር የለም፡፡

ከዓመታት በፊት ለእይታ የበቁ ጥበባዊ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በየጊዜው አዳዲስ ሥራዎች ይካተታሉ፡፡ ማዕከሉን የሚጎበኝ ሰው በቀድሞ ዘመንና በአሁኑ መካከል የሚመላለስ ሊመስለውም ይችላል፡፡ ማዕከሉ ከጥበባዊ ሥራዎች በተጨማሪ በጊዜ ልዩነት መካከልም ድልድይ ዘርግቷል ማለት ይቻላል፡፡ በማዕከሉ ልዩ ልዩ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ባጠቃላይ አማራጭ ቀርቧል፡፡ በአንድ የማዕከሉ ማዕዘን የምሽት ክለቦች በሌላው ደግሞ የዮጋ ሴንተር ይገኛል፡፡ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች በእጃቸው የሠሯቸው ጌጣ ጌጦችና መገልገያዎችም የማዕከሉ ሌላ ገጽታ ናቸው፡፡    

 በኪነጥበብ ማዕከሉ ተቀራራቢ ዝንባሌ ያላቸው አርቲስቶች በኅብረት የሚሠሩባቸው ቦታዎች ጎብኝተናል፡፡  ኋይት ቦክስ አርት ሴንተር፣ ማጂሽያን ስፔስ እና ታቡላ ራሳ ይገኙበታል፡፡ በኪነጥበቡ፣ በሙዚቃውና በፋሽኑም ተመሳሳይ ዘዬ የሚከተሉት ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን የሚሳዩባቸው ናቸው፡፡ በማዕከሉ ከቻይና ጥንታዊ ኪነጥበብ እስከ ዘመናዊው ከመገኘቱ ባሻገር በማዕከሉ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ለማስጎብኘት ጓጉተው ይጠብቃሉ፡፡

      ወደ አንድ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ  የጋበዘችን ወጣት፣ ቻይናውያን በተወሰነ ደረጃ ወግ አጥባቂ ከመሆናቸው የተነሳ በአደባባይ ሊናገሯቸው የማይደፍሯቸው ማህበረሰባዊ እውነታዎችን በፎቶግራፍ ማሳየት እንምትሻ ትገልጻለች፡፡ ያስጎበኘችን የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ሴትነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እርቃናቸውን የቆሙ ሴቶች ምስልን ያካተተ ነበር፡፡

      ማዕከሉን የጎበኙ ሰዎች በሰጡት አሰተያየት መሠረት በሰቨን ናይን ኤይት በብዛት ከሚጎበኙ ቦታዎች መሀከል ‹‹ፌንግ ሊንግ ፋሽን አርት ዲዛይን››፣ ማለትም ፌንግ ሊንግ በተባለች ዲዛይነር የተመሠረተው ቡቲክ ይጠቀሳል፡፡ የቻይናን ባህላዊ አልባሳት ከምዕራባውያን ዘመን አመጣሽ ፋሽን ጋር ያጣመሩ ልብሶች ይሸጡበታል፡፡ ሌላው በብዛት የሚጎበኘው ሼንጂ ካይ ጎዋን በተባለ ቻይናዊ ሼፍ የተመሠረተው ሼንጂ ሬስቶራንት ነው፡፡ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ኦልድ ፋክተሪ ሬስቶራንት፣ የቀድሞውን የወታደራዊ ገፅታ እንደጠበቀ የሚገኝ ነው፡፡ ጥንታዊ የእንጨት ቁሳቁሶችና መሣሪያዎች እንደ መመገቢያ ጠረጴዛና ወንበር ያገለግላሉ፡፡

  

  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...