Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ለአሜሪካ የወረደው ሲሳይ

ትኩስ ፅሁፎች

መሰንበቻውን ለንደን ለአሥር ቀናት ባስተናገደችው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተፈጠሩት አስገራሚ ክስተቶች አንዱ በ3000 ሜትር መሠናክል የሴቶች ውድድር ላይ ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. የታየው ነበር፡፡ በ3000 ሜትር መሠናክል በውጤት ገናና የሆኑት ኬንያውያቱ በዘንድሮው ውድድር ከሦስተኛነት አላለፉም፡፡ የአማሪካውያቱ የቅርብ ተፎካካሪ የነበረችው ሂይቪን ጄፕኬሞይ ነሐሱን አጥልቃለች፡፡ ለወርቅ ትጠበቅ የነበረችው ቢትራይስ ጄፕኮኤች ውድድሩን እየመራች ስትሄድ ኩሬ ያለበትን መሠናክል መዝለሉን ዘንግታ ሩጫዋን በመቀጠሏና መሳሳቷን ተረድታ ለመመለስ ብትሞክርም አልፈዋት ከሄዱት ቀዳሚዎቹ ላይ መድረስ አልቻለችም፡፡ በአራተኛነት አጠናቃለች፡፡ ሲሳይ የወረደላቸው አሜሪካውያቱ ኢማ ኮበርንና ኮርኔይ ፍሪችስ ወርቅና ብሩን አጥልቀዋል፡፡

ደራሲ ማን ነው?

አንተ ባለቅኔ! አንተ ልብ-ወለድ ወላጅ

ሥነጽሑፍን ከሕዝብ ገንጥሎ ተራማጅ፡፡

       ከመካከል ቁመህ ደረትህን አትንፋ

       ወይ እሳቱን አንድድ ወይ እሳቱን አጥፋ…

ወይ ነፋሱን አግድ ወይ ነፋሱን ግፋ

ወይ ደመናን ጥረግ ወይ ደመናን አስፋ

ወይ ትንፋሽህን ዋጥ ወይም ትንፋሽ ትፋ፡፡

      ወይ ዐይንህን ግለጥ ወይ ዐይንህን ዝጋ

      ወይ ጀሮህን ድፈን ወይ ጀሮህን አትጋ፡፡

ወይ ታጠቅ ተፈሪ ወይም ታጠቅ ቁምጣ

ወይም ፀሐይ አግባ ወይም ፀሐይ አውጣ፡፡

      አልሚ-አጥፊ ተብለህ አብጅ ዘመድ ጓድ

      ሁለት የወደደ አያገኝም አንድ፡፡

  ነፋስ አንከባሎም ወደ አንዱ አይጎልትህ

   መጥፎና መልካሙን ሳይመርጥ ጭንቅላትህ፡፡

ሥነጽሑፍ የሕዝብ ናት የሰፊው ሕዝብ ምርጫ

የላትም ጉራንጉር የግል መሸጎጫ

የልፍኝ ቤት መግቢያ… የጓሮ በር መውጫ፡፡

     እና! የምንለው የደራሲው ብዕሩ

     ወይም ከሕዝብ ሆኖ ቀይ ይሁን መስመሩ፡፡

ከሕዝቡ ደም ነክሮ ይጻፍ የሕዝብ ዋይታ

ወይም ከውሃው ጠቅሶ በውሃው ግጥም ይምታ፡፡

    ከሁለቱ መርጦ ባንደኛው ካልጣፈ

    ለደሙም ለውሃውም ጠላት ነው የጦፈ፡፡

ግን ከመኸል ቁሞ መንገዱን ከዘጋ

ኸንጥ ይግባ ተገፍቶ ምን አለው ከእኛ

  • አያልነህ ሙላቱ ‹‹ወይ አንቺ አገር›› (2004)

 

***

የ76 ዓመቱ ብራዚላዊ የቁንጅና ውድድር አሸነፉ

በጉብዝናቸው ወቅት የኮንስትራክሽን ባለሙያ ነበሩ፡፡ አያት ከሚለው የክብር ስም ውጪ ሌላ ማዕረግ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ግን የ2017 መልከ መልካሙ  አዛውንት ተብለዋል፡፡ የ76 ዓመቱ ሆዜ ዶሳንቶስ ከ24 መልከ መልካም አዛውንቶች ጋር ተወዳድረው አንደኛ የወጡት ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በሳኦፖል ተዘጋጅቶ በነበረው የቁንጅና ውድድር ነው፡፡ ውድድሩ የአዛውንቶቹን በራስ የመተማመን ስሜት ከፍ እንደሚያደርግ የውድድሩ አዘጋጅ ኒልተን ዳሲልቫ ገልጿል፡፡ ውድድሩ የተዘጋጀው በሳኦፖል ስቴት ሄልዝ ዲፓርትመንት ነበር፡፡

ከ62 እስከ 96 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አዛውንቶች በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡ ‹‹በውድድሩ መሳተፍና ተሸላሚ መሆን ለኔ ትልቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም የኔ ዕድሜ ላይ መድረስ ትልቅ ስኬት ነው፤›› ብለዋል አሸናፊው ሆዜ፡፡ ዜናውን የዘገበው ሀፍ ፖስት ነው፡፡

***

የትራፊክ መጨናነቅን በዋና የሚያልፈው ጀርመናዊ

ቤንጃሚን ዴቪድ የተባለው ጀርመናዊ ወደ ሥራ ለመሄድ ብስክሌት ወይም ባስ ይጠቀም ነበር፡፡ ይሁንና በሙኒክ ጎዳናዎች ላይ የሚፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ የሥራ ገበታው ላይ በጊዜ ከመገኘት ሲያግደው ቆይቷል፡፡ ለዚህም አንድ መፍትሔ ዘየደ፡፡ ላፕቶፑንና የሥራ ልብሶቹን ውኃ በማያስገባ ቦርሳ በመያዝ በአቅራቢያው የሚገኘውን ኢዛር የተባለ ወንዝ በዋና አቋርጦ መሄድ፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው ዋናው 12 ደቂቃ ነው የሚፈጀው፡፡ ‹‹በጣም ቆንጆና ስሜት የሚያድስ ነው፡፡ በተጨማሪም ፈጣኑ መንገድ ነው፤›› በማለት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ያህል መሆኑን ቤንጃሚን ተናግሯል፡፡

***

 

በ101 ዓመታቸው የፓራሹት ዝላይ ያደረጉ ግለሰብ አዲስ ሪከርድ አስመዝግበዋል

ቬርደን ሄይስ የተባሉት የ101 ዓመት አዛውንት፣ ከ15,000 ጫማ ከፍታ ላይ በፓራሹት በመዝለል በዓለም በዕድሜ ትልቁ ‹ስካይ ዳይቨር› ሆነዋል፡፡ ‹‹በጣም ደስ ይላል፡፡ በእውነት ይኼንን ነገም አደርገዋለሁ፡፡ የሚወደድ ነገር ነው፤›› ሲሉ ስሜታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡ እንግሊዛዊው ቬርደን ከተወለዱ 101 ዓመት ከ37 ቀናት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የ101 ዓመት ከሦስት ቀን ዕድሜ ያላቸው አንድ ካናዳዊ ከ10,000 ጫማ ከፍታ ላይ ስካይ ዳይቭ በማድረግ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግበው ነበር፡፡

ቬርደን በስካይ ዳይቭ ስፖርት ለመሳተፍ ማሰብ የጀመሩት የ90 ዓመት አዛውንት ሳሉ ነበር፡፡ ይሁንና ባለቤታቸው ሊፈቅዱላቸው ባለመቻላቸው ምኞታቸው ዕውን ሳይሆን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን የተሳካላቸው ግን ባለቤታቸው ሐሳባቸውን ቀይረው ስለፈቀዱላቸው ሳይሆን በሞት ስለተለዩዋቸው ነው፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች