‹‹የታታሪዎች ዕንቁ የሆኑትን እኚህን አገር ወዳድና የአገር አገልጋይ ሃይማኖተኛ ሰው፣ [ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ] በዚህ በተቀደሰ ቦታ ተገኝተን ለመጨረሻ ጊዜ ስንሰናበታቸው መልካም ሥራቸውና ሰብዕናቸው እየታሰበን ነው፡፡››
ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት ተብለው በሚታወቁት አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲፈጸም ዐውደ ምሕረት ላይ የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሥራች፣ የአሥራ ሦስት ወራት ፀጋ (13 Months of Sunshine) በሚል መጠሪያ ቱሪዝሙን ለዘመናት ሲያስተዋውቅ የኖረውን መለያ (ብራንድ) የፈጠሩና በዘርፉ በርካታ ሥራዎችና የራሳቸውን የዕደ ጥበብ ውጤት ጨምሮ ያስተዋወቁት አቶ ሀብተ ሥላሴ በ90 ዓመታቸው ያረፉት ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡