Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበልሁ አባ ቆሮ - ከጥቋቁር የሙዚቃ ፈርጦች አንዱ

በልሁ አባ ቆሮ – ከጥቋቁር የሙዚቃ ፈርጦች አንዱ

ቀን:

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ መከሰት አንዱ አጋጣሚ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ይባሉ በነበረበት በግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን (1909-1922)፣ በ1916 ዓ.ም. አውሮፓና እስራኤልን መጎብኘታቸው እንደሆነ ይወሳል፡፡

ከዘጠኝ አሠርታት በፊት ከኢየሩሳሌም የመጡት አርባ የአርመን ልጆች ከሙዚቃ ጋር ትውውቅ ስለነበራቸው ኢትዮጵያውያን ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር ለመተዋወቅ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ የአርመን ሙዚቀኞች መምጣት ተከትሎ በአዲስ አበባ ወጣቶች በሙዚቃ ትምህርት እንዲሠለጠኑ ሲደረግ ዕድሉን ካገኙት መካከል አብዛኞቹ ከምዕራብ ኢትዮጵያ ከጋምቤላና ከቤኒሻንጉል አካባቢ የተገኙ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡

ንግሥት ዘውዲቱ አርፈው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን በ1923 ዓ.ም. ጥቅምት 23 ሲነግሡ የዘውድ በዓሉን ያደመቁት ኢትዮጵያውያኑ ሙዚቀኞች በተለይም የማርሽ ባንድ እንደነበረ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡

የማርሽ ባንዱን ከሁለት ሜትር በላይ ቁመት ያለው በልሁ አባ ቆሮ ይመራው እንደነበረ በለጠ ገብሬ በጻፉት ‹‹በዕድሜ ጎዳና ላይ የጉዞ ትዝታ›› ድርሳናቸው ገልጸውታል፡፡

በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከማንነቱ ይልቅ ምስሉ የሚታወቀው የመጀመርያው የማርሽ ባንድ አሽከርካሪ፣ አንዳንዶችም ‹‹ትራፊክ›› ለሚሉት በልሁ አባ ቆሮ ማንነት የተወሰነ መረጃ የሚገኘው የዓይን ምስክር ከሆኑት አቶ በለጠ ገብሬ ነው፡፡

ከመንግሥት ሹመኝነት ባሻገር በኪነ ጥበቡ መስክ በተለይ በተዋናይነት የሚታወቁት አቶ በለጠ፣ በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በተደረሰው አፋጀሺኝ ቴአትር እንደ አፋጀሺኝ ሆነው የሴት ገጸ ባሕሪን የተጫወቱ ናቸው፡፡ እሳቸው በልሁን እንዲህ ይገልጹታል፡-

‹‹የበልሁ አባ ቆሮን ስም ከሙዚቀኝነት ሙያው ይልቅ በዝናማነት ያሳወቀው ከሁለት ሜትር በላይ የሆነው መለሎ ቁመቱ ነበር፡፡ ታዲያ ከመቶ የሚበልጡት ወገኖቹ ሙዚቀኞች የሙዚቃ መሣሪያቸው በሙሉ ፍፁም ዘመናዊና በፈረንጅ ኖታ (የዜማ ምልክት) የሚቃኝ የአውሮፓ ኦርኬስትራ ሆኖ ሳለ፣ እነዚያ የሐበሻን ፊደል ቀርቶ አማርኛ ቋንቋ እንኳ አጠናቀው የማይናገሩ መሐይማን ባላገሮች የሙዚቃውን ኖታ አበጥረው አውቀው፣ ዜማውን በልዩ ልዩ መሣሪያዎቻቸው ለመቃኘትና እያቀላጠፉ ለማቀንቀን መቻላቸው እጅግ ያስገርም ነበር፡፡

‹‹ለመሆኑ በየትምህርት ቤቱ ቋንቋ ከሚማሩት ወጣቶች መካከል ተመርጠው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ለተወሰነ ሰዓት የሙዚቃ ፕሮግራም በጣልቃ ገብ ከሚከታተሉ ተማሪዎች ለዚሁ አገልግሎት የሚሆኑትን ከማሠልጠን ፋንታ፣ በተለይ ጋምቤላዎቹ በጣም ሩቅ ከሆነው ጠረፍ አገራቸው ከጋምቤላ አካባቢ መልምሎ ማምጣት ያስፈለገበት ምክንያት እንቆቅልሽ ቢሆንም፣ ምናልባት ከጥንት ጀምሮ በግልም ሆነ በማኅበራዊ ሥነ በዓል ላይ እንቢልታ መለከት መንፋት፣ አዋጅ በሚነገርበትና በጦርነት ጊዜ ባህላዊ ነጋሪት መምታትና የመሳሰለውን ተግባር መፈጸም የነሱ ዓይነት ሰዎች ሙያ በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡

‹‹ይህንንም የሚያሰኘው በቆየው ባህላችን የጨዋ ልጅ ሲባል፣ ከበገና በቀር የዜማ መሣሪያዎችን መቃኘት ተምሮ ሊጫወት ይቅርና ተፈጥሮ ለሰው ልጅ ከለገሰቻቸው ረቂቅ ሥነ ጥበባት አንዱ መሆኑ ታውቆ በሌሎቹ ዓለማት እጅግ የሚደነቀው የዘፈን ተሰጥኦ በእኛይቱም አገር የቁም ነገር ደረጃ ሊያገኝ እስከቻለበት ቅርብ ዘመን ድረስ፣ ድምፃውያን ዘፋኞችን በጾታ ስያሜ ወንዶቹን ‹‹አዝማሪ››፣ ሴቶቹን ‹‹አረሀ›› እያሉ በመጥራት ዝቅ አድርጎ መመልከት ለምዶ መኖሩ ስለታወቀ ነው፡፡

አቶ በለጠ ‹‹ጥቋቁር የሙዚቃ ፈርጦች›› እያሉ የሚጠሯቸውን ቀዳሚዎቹ ሙዚቀኞች በወቅቱ ያሳደሩባቸውን ያድናቆት ትዝታ በመጽሐፋቸው አውስተውታል፡፡ በተለይም የማርሽ ባንዱን መሪ አሽከርካሪ በልሁ አባ ቆሮን፡፡

‹‹ይኸውም ያን ጊዜ ታላላቅ ወታደራዊ ሠልፍ በሚደረግበት ክብረ በዓል ላይና በአዘቦቱም ቀናት ልምምድ ለማድረግ ሙዚቀኞቹ ሲወጡ፣ መንገደኛው ሁሉ በታምቡሩ ጉርምርምታና በጥሩምባው ቱማታ እየተመሰጠ ከየአቅጣጫው ተሰብስቦ ያጅባቸውና አብረቅራቂ መሣሪያዎቻቸውን፣ የተሸተረ አለባበሳቸውን፣ ያማረ ትጥቃቸውንና የኅብረት ዕርምጃቸውን በማድነቅ ይከተላቸው ስለነበረ ነው፡፡

‹‹በተለይም በልሁ አባ ቀሮ ጥቂት ነጠል ብሎ ከፊት እየመራ ባለወርቅ ጫማ በትረ ሙዚቃውን ወደ አየር አጉኖ መልሶ በመቅለብ፣ ወደ ፊት ወደ ጎን ሰንዝሮ በመስበቅ፣ ከዚያም በቁንጥር አያያዝ እየተመረኮዘ ሸብ እረብ በማለት፣ በዚያ በቁመቱ ሲሰግር ሲረገረግ አይቶት ያልፈዘዘ ሰው ይኖራል ማለት በእውነት ያስቸግራል፡፡ ይህ ሁሉ ሁኔታ ለእኔ ሁልጊዜ አዲስ ከመሆኑ የተነሳ፣ አንድ ቀን በራስ መኰንን ድልድይ አካባቢ ድንገት አጋጥመውኝ ፈዝዤ እየተከተልኩ በማጀብ ላይ ሳለሁ፣ አካሄዳቸው ወደ ጃን ሜዳ ሠፈራቸው ለመመለስ ኖሮ አርመን ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሲደርሱ ወደ ግራ ታጥፈው የአርባ ደረጃን አቀበት በዝግታ ዕርምጃ ተያያዙት፡፡ እኔ ግን እዛው ቆሜ በዓይኔ ሸኘኋቸው፡፡ የሠልፍ መሪያቸው የበልሁ ሰውነት፣ ከዳሌው አንስቶ ወደ ላይ ያለው አካሉ ከተከተሉት ሙዚቀኞች አናት በላይ ዘልቆ ስለታየኝ፣ በዚህ ግምት ቁመተ አጣራ የሚባሉትን ዓይነት ሁለት ሰዎች ሊያህል ምን ቀረው? የሚል ስሜት አሳድሮብኝ ነበር፡፡››

የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን (1928-1933) ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የመከራና የፍዳ ዘመን ነበር፡፡ ቅድመ ወረራ ሠልጥነው የነበሩት ሙዚቀኞች በመከራው ጊዜ የገፈቱ ቀማሽ የነበሩ ሲሆን፣ ግማሾቹ ሲገደሉ የቀሩም መበታተናቸውን ‹‹ሙዚቃ በኢትዮጵያ›› የሚለው ድርሳን ያስረዳል፡፡ ፋሺስቶች አዲስ አበባ ሲገቡ የነበረው ሹማቸው ባዶሊዮ ተሽሮ ማርሻል ሮዶልፎ ግራሲያኒ ሲሾም፣ በአገሪቱ ላይ በተለይ ከግንቦት 1928 እስከ የካቲት 1929 ዓ.ም. ያወረደው መከራ የፈጸመው ፍጅት በታሪክ ይወሳል፡፡ አቶ በለጠ ገብሬ ያን ዘመን ያን ዓመተ ፍዳ ያስታውሱታል፡፡ በነበረው የጅምላ አፈሳ ሰለባ ከነበሩት መካከል አንዱ የክብር ዘበኛ ሙዚቀኞች ሰልፍ መሪ የነበረው በልሁ አባ ቆሮ ነበር፡፡ ደራሲው እንዲህ አሉ፡-

‹‹የከተማው ሰው ዳር እስከ ዳር ከመበርገጉ የተነሳ አንዳንዱ የደበቀውን መሣሪያ እያወጣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደ ሚገኙት አርበኞች የጦር አለቆች ሲሄድ፣ የሚበዛው በየቤቱ መዋል ማደሩን ትቶ በዛፍ ውስጥና አልባሌ በሆነ ቦታ እየተሰወረ ፍጻሜውን ይጠባበቅ ጀመር፡፡ የሆነ ሆኖ አፈሳው ቶሎ መቆም ብቻ ሳይሆን የታሰሩትም ሰዎች ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተለቀቁ፣ በብስጭት እንፋሎት የታመቀው የሕዝቡ ስሜት ረገብ ብሎ እንደገና የሰላም አየር የሚተነፍስ መሰለ፡፡ የታሰሩበትም ቦታ ‹‹ዓለም በቃኝ›› የተባለው ታላቁ ወህኒ ቤት እንደነበረ ከተፈቱ በኋላ ሊቄ ገብረ ክርስቶስ ወልደ ዮሐንስ አስረድተው፣ ከእስረኞቹ መካከል አንዳንዶቹ ገና በዚያው መገኘታቸውንና ከነሱ ውስጥ የሚያውቁት በልሁ አባ ቆሮ የተባለውን የክብር ዘበኛ ሙዚቀኛ ሠልፍ መሪ ብቻ መሆኑን ገልጠውልናል፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...