Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመኢአድና ሰማያዊ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ተቸግረናል አሉ

መኢአድና ሰማያዊ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ተቸግረናል አሉ

ቀን:

በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር እሑድ ነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በመብራት ኃይል አዳራሽ ውይይት ለማድረግ ያስገቡትን የዕውቅና ጥያቄ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ዕቅዳቸውን መሰረዛቸውን አስታወቁ፡፡

ፓርቲዎቹ ይህን ያስታወቁት ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ዋና ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የመኢአድ ፕሬዚዳንት በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር)፣ የሰማያዊ ፕሬዚዳንት አቶ የሺዋስ አሰፋና የመኢአድ ዋና ጸሐፊና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ናቸው፡፡

‹‹ሕዝባዊ ሰብሰባ እንደምናደርግ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ደብዳቤ ብናሳውቅም፣ ‹ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ስብሰባ ለማካሄድ በአንድ ደብዳቤ መጠየቅ አይችሉም› የሚል አሳማኝ ያልሆነ መልስ ተሰጥቶናል፡፡ ምንም እንኳን የተሰጠንን መልስ ባናምንበትም ለፕሮግራማችን መሳካት ሲባል አስተዳደሩ ባሳሰበው መሠረት፣ በየፓርቲዎቹ ፕሬዚዳንት ፊርማ በተናጠል በድጋሚ በጽሑፍ ጠይቀናል፡፡ ሆኖም  ጥያቄያችንን ተቀብሎ የሚያስናግድ አካል ባለመኖሩ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ውይይት ማካሄድ አልቻልንም፤›› በማለት የፓርቲዎቹ መግለጫ ያትታል፡፡

- Advertisement -

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ክፍል በበኩሉ ከፓርቲዎቹ ደብዳቤ እንደደረሰው ያረጋገጠ ሲሆን፣ ነገር ግን ኃላፊነት የሚወስድ አካል ከፓርቲዎቹ ባለመቅረቡ ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ አለመቻሉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ኃላፊ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹ፓርቲዎቹ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡ ነገር ግን ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አላሟሉም፡፡ ደብዳቤውን ብቻ ጥለው ነው የሄዱት፡፡ ከዚህ አንፃር ኃላፊነት የሚወስድ አካል በሌለበት ሁኔታ ምን ማድረግ እንችላለን?›› በማለት የፓርቲዎቹን ስሞታ በጥያቄ ሞግተዋል፡፡

ምንም እንኳን አስተዳደሩ ይህን ቢልም፣ ‹‹በጋራ የሚለውን ቃል ከደብዳቤው እንድናወጣ፣ ካልሆነ ፎርም እንደማያስሞሉን ገልጸውልናል፡፡ ነገር ግን ይህን የሚገልጽ ደብዳቤ ስጡን ስንል ደብዳቤ የመስጠት ግዴታ የለብንም የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ስለዚህ ይህ ሆን ተብሎ ሰብሰባውን የማደናቀፍ ተግባር ነው፤›› በማለት አቶ የሺዋስ የአስተዳደሩን ምላሽ ተችተዋል፡፡

የሕዝባዊ ስብሰባው ዋነኛ ዓላማ ከሕዝቡ ጋር በወቅታዊና በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እንደነበር አቶ የሺዋስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የስብሰባው ዋነኛ ዓላማ የነበረው ለአሥር ወራትና ከዚያም በፊት ለዓመታት ተዘግቶ የነበረውን በፓርቲዎችና በሕዝብ መካከል የነበረውን ግንኙነት መክፈት ነበር፡፡ ከሕዝቡ ጋር እንነጋገራለን የሚለውንም እንሰማለን የሚል ዓላማ ነበረው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህንን ዕድል ነው የዘጋብን፤›› በማለት አክለው አስረድተዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቷል ተብሎ ወደ መደበኛው የሕግ ሥርዓት ተመልሰናል ቢባልም፣ እየሆነ ያለው ነገር ግን ከዚያ የባሰ ነው፤›› ሲሉ አቶ የሺዋስ በምሬት ገልጸዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ፖለቲካ መሥራት ይቻላል? ሕዝቡንና አገሪቷንስ እንዴት ወደ ሰላም ማምጣት ይቻላል?›› ሲሉ አቶ የሺዋስ ይሞግታሉ፡፡

‹‹ገዢው ፓርቲ ፍርኃት ውስጥ ነው፡፡ ፍርኃት ውስጥ ሆኖ ደግሞ ምንም አማራጭ ለሕዝብ እንዳናቀርብ እያደረገን ነው፡፡ ያ ደግሞ አገሪቱን የባሰ ችግር ውስጥ የሚጥል በመሆኑ መንግሥት ለሕዝብ ማሰብ አለበት፡፡ የፓርቲዎችን ሥራ ማክበርና ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት መፍጠር የለበትም፤›› ሲሉ አቶ የሺዋስ አስረድተዋል፡፡

የመኢአድ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የእንደዚህ ዓይነት ስብሰባዎች ውጤት የሚጠቅመው መንግሥትን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹እሑድ ዕለት በመብራት ኃይል አዳራሽ ለማካሄድ አቅደነው የነበረው ስብሰባ ዋናው ቁም ነገር የነጋዴው ኅብረተሰብ አባላት አለብን የሚሉት ችግር ላይ ለመወያየት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ውይይት ደግሞ የሚጠቅመው ለራሱ ለመንግሥት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር በዛብህ መንግሥት ስብሰባ እንዳይካሄዱ የሚፈራበት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለም ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ ድብቅ አጀንዳ የለንም፡፡ በግልጽ ነው የምንታገለውና የመንግሥትን ድክመት ለማጋለጥ የምንሞክረው፡፡ ይህ ደግሞ ሥራችንም ነው፡፡ ለዚሁ ነው ተመዝግበን የምንታገለው፡፡ እንደዚሁ ለጨዋታ ወይም የምናገኘው ፍርፋሪ ስላለ አይደለም፡፡ በራሳችን ነው የምንታገለው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለቱ ፓርቲዎች ለጠየቁት ጥያቄ አፋጣኝና በጎ ምላሽ መስጠት ሲገባው፣ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሁለቱን ፓርቲዎች ሕገ መንግሥታዊ መብት መጋፋቱን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...