Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአራተኛው የሥነ ሕዝብና ጤና ሪፖርት የሕፃናት ሞት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል አለ

አራተኛው የሥነ ሕዝብና ጤና ሪፖርት የሕፃናት ሞት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል አለ

ቀን:

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ የተደረገው አራተኛው የሥነ ሕዝብና ጤና ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የሕፃናት ሞት የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃኔና የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ኃላፊዎች በተገኙበት ይፋ የተደረገው ጥናት፣ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚያካትት ነው፡፡ በሥነ ሕዝብና በጤና ዘርፍ የተለያዩ ግኝቶችን ይዟል፡፡

ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሆኑ 15,783 ሴቶች፣ 12,688 ወንዶች፣ እንዲሁም 16,650 አባዎራዎችን እንደ ናሙና በመውሰድ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የፌዴራል ከተሞች ላይ ጥናቱ መከናወኑም ተጠቁሟል፡፡

ጥናቱ የሕፃናት ሞት ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው አኃዝ ቅናሽ እንዳሳየ አመልክቷል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ 1,000 ሕፃናት 88 የሚሆኑት የአምስተኛ የልደት በዓላቸውን ከማክበራቸው በፊት ይሞቱ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በወጣው ሪፖርት ይህ ቁጥር ወደ 67 ቀንሷል፡፡ ይህ ማለት ዕድሜያቸው በተጠቀሰው ክልል ውስጥ ከሚገኙ 15 ሕፃናት አንዱ ዕድሜው አምስት ከመሙላቱ በፈት ይሞታል ማለት ነው፡፡ ይህ አኃዝ ከክልል ክልል ይለያያል፡፡ በአፋር ክልል ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት 1,000 ሕፃናት ውስጥ 125 ይሞታሉ፡፡ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቁ ነው፡፡ በተቃራኒው አዲስ አበባ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 39 ሕፃናትን በማጣት የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል፡፡

ሌላው በሪፖርቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የተባለው በሕፃናት ላይ እየታየ ያለው የቀይ ደም ሕዋሳት እጥረት መጨመር ነው፡፡ ሪፖርቱ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ወር ከሆኑ ሕፃናት ውስጥ ወደ 57 በመቶ የሚሆኑት እጥረት አለባቸው ብሏል፡፡ ይህ አኃዝ ከአምስት ዓመት በፊት 44 በመቶ ብቻ ነበር፡፡

‹‹ይህ የጥናት ሪፖርት ትኩረት የሚያስፈልገውና በጥልቅ መታየት ያለበት ነው፤›› ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህም ጥናት ውጤት ተነስተን በሕፃናት ላይ የተለያዩ ሥራዎች እናከናውናለን፡፡ ለምሳሌ የትምህርት ቤት ውስጥ የምገባ ሥርዓት ማጠናከር፣ ለቀይ ደም ሕዋሳት እጥረት መፍትሔ የሚሆኑ መድኃኒቶች በቤቶችና በትምህርት ቤቶች ማሠራጨት ይከናወናል፤›› ብለዋል፡፡

ከሴቶች ግርዛት ጋር ያሉ አኃዞች መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ካሉ ሴቶች ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት የተገረዙ ሲሆን፣ ይህም በ1997 ዓ.ም. ከነበረው 77 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

አኃዙ በክልል ሲታይ በሶማሌ 99 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ክልሉን በአንደኝነት አስቀምጦታል፡፡ በተቃራኒው ትግራይ ክልል 24 በመቶ በመያዝ መጨረሻ ደረጃን ይዟል፡፡ አዲስ አበባ 54 በመቶ በመያዝ 33 በመቶ የያዘውን ጋምቤላ ክልልን በመከተል በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡

ሌላው በጥናቱ ላይ የተመለከተው የወሊድ መጠን ሲሆን፣ ከ16 ዓመት በፊት ከነበረው 5.5 ልጆች በአንድ ሴት አማካይ ቁጥር የ0.9 ልጆች ቅናሽ በማሳየት በአገር አቀፍ ደረጃ 4.6 ልጆች በአንድ ሴት ደርሷል፡፡

ይህ አኃዝ በክልል ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው ደረጃ ሲታይ በአፋር፣ በሐረሪ፣ በአዲስ አበባና በትግራይ ክልሎች የሚገኙ ሴቶች የወሊድ መጠን ጨምሯል፡፡ በተቃራኒው እንደ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ ክልል፣ ጋምቤላ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ቅናሽ አሳይተዋል፡፡

በክልሎች ያለውን የወሊድ መጠን ሲታይ ሶማሌ 7.2፣ አፋር 5.5፣ እንዲሁም ኦሮሚያ 5.5 ልጆች በአማካይ በአንድ ሴት በመሆን ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በሌላ በኩል አዲስ አበባ 1.8 ልጆች በመሆን የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል፡፡

‹‹ከወሊድና ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ከሚሆኑ ሴቶች 13 በመቶ የሚሆኑት የመጀመርያ ልጃቸውን ያረገዙ ወይም የወለዱ ናቸው፤›› ሲል ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ ከጋብቻ ጋርም በተያያዘ ወደ 11 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሚሆኑ ሴቶችና አምስት በመቶ የሚሆኑት በተመሳሳይ ዕድሜ ያሉ ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስት ወይም ባል አላቸው ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ያገቡ ሴቶች መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ዘመናዊ የወሊድ መከላከያ እንደሚጠቀሙ ተመልክቷል፡፡ በተመሳሳይ በክልል ደረጃ ሶማሌ ክልል ውስጥ ካገቡ ሴቶች ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆኑት ብቻ ዘመናዊ የወሊድ መከላከያ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ይህም ክልሉን በአገር አቀፍ ደረጃ መጨረሻ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡ በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚኖሩ ያገቡ ሴቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ የመከላከያው ተጠቃሚ በመሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 23 ወራት ለሆኑ ሕፃናት ከሚሰጠው ክትባት ጋር በተያያዘ በአገር አቀፍ ደረጃ 39 በመቶ የሚሆኑት ስምንቱንም ክትባቶች እንደተከታተሉ ተመልክቷል፡፡ በክልል ደረጃ አዲስ አበባ 89 በመቶ፣ ትግራይ 67 በመቶ፣ እንዲሁም ቤኒሻንጉል ጉምዝ 37 በመቶ በመያዝ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ይህ ለአራተኛ ጊዜ የወጣው ሪፖርት ከተለያዩ ለጋሽ ድርጀቶች ጋር በመተባበር የተሠራ ሲሆን፣ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...