Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን እሰጥ አገባ

የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግ ኡን እሰጥ አገባ

ቀን:

በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ውዝግብ በጉልህ ጫፍ የነካው ባለፈው

ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያም የሚሳይል ሙከራዎቿን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተደጋጋሚ የሞከረችውና ለዓለም ሥጋት መሆኗን ያሳየችው እ.ኤ.አ. 2017 ከገባ ወዲህ ነው፡፡ ከየካቲት 2017 ወዲህ ብቻ 18 ሚሳይሎችንም አስወንጭፋለች፡፡ የመጨረሻውን አኅጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ያስወነጨፈችው በሐምሌ በመጀመሪያ ላይ ሲሆን፣ ሰሜን ኮሪያም ሚሳይሉ በዓለም የትኛውም ሥፍራ መድረስ ይችላል ብላ ማሳወቋን ሲኤንቢሲ ዘግቧል፡፡

ይህ ሰሜን ኮሪያ የምታካሂደው የሚሳይል ሙከራ በተለይ ኃያላኑን አገሮች ይልቁንም አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ አስገብቷል፡፡ ከሰሜን ኮሪያና ከሩሲያ ጋር ችግሮችን በሰላም ለመፍታት እጥራለሁ ሲሉ የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ከሰሜን ኮሪያው ኪም ጆን ኡን ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ጣቶቻቸውን ከትዊተር የማይለዩት ትራምፕ፣ በአገራቸው በሪፐብሊካኑ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ሰሜን ኮሪያ አርፋ ካልተቀመጠች ቃታ እንስባለን ብለዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያን ከሚሳይል ሙከራ ይገታታል የተባለ ተጨማሪ ማዕቀብ የቻይና ድጋፍ ታክሎበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢያጸድቅም፣ ይህም ሌላ መዘዝ ሊያመጣ ይችላል ተበሏል፡፡ ሰሜን ኮሪያ በማዕቀብ ምክንያት በሚያጋጥማት ችግር የተነሳ ሚሳይሎቿን ልትጠቀም፣ በቀጣናውም ጦርነት ልትከፍት ትችላለች የሚል ሥጋትም እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ሰሞኑን ድርጅቱ ማዕቀቡን ሲያፀድቅ በድርጅቱ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ ያሉትም፣ ማዕቀቡ ተጣለ ተብሎ ራስን ማሞኘት እንደማይገባ ነው፡፡ ችግሩ እንዳልተቀረፈና እንዳልተዘጋ ማሰብ እንደሚገባ፣ የሰሜን ኮሪያ ሥጋትነት እንዳለና በፍጥነትም በአደገኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ተመድ በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቡን አፅድቆ ሳምንት እንኳን ሳያቆይ ሰሜን ኮሪያ ሁለት ዋና ዋና የአሜሪካ ወታደራዊ ቤዞች በሚገኝበት ጉአም አራት ሚሳይል ለማስወንጨፍ ያላትን ዕቅድ ከልሳ መጨረሷን አስታውቃለች፡፡ ትራምፕ በበኩላቸው ፒዩንግያንግ አርፋ የማትቀመጥ ከሆነና ለአሜሪካና ወዳጆቿ ሥጋት ከሆነች፣ የአሜሪካ የኑክሌር አረሮች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንካራ ጥቃት ይሰነዝሩባታል ብለዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በጉአም ማንኛውም ጥቃት ለማድረስ ዕቅድዋን የጨረሰች ቢሆንም፣ ቢቢሲ ማክሰኞች ይዞት በወጣው ዘገባ ኪም ጆን ኡን ለጊዜው ዕቅዳቸውን ማዘግየታቸውን አሳውቀዋል፡፡

ኪም የጉአም ዕቅዳቸውን ያስታወቁት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ግዛት ሚሳይል ከተኮሰች የጦርነት ጨዋታው ተጀመረ ብሎ ካስታወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጀምስ ማቲስ በፔንታጎን ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የሚከተለውን ምላሽ ለመሸከም ካልፈለግህ በስተቀር በሰዎች ላይ አትተኩስም፤›› ሲሉም ሰሜን ኮሪያ ለምትሰነዝረው ጥቃት ወታደራዊ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ደቡብ ኮሪያ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ እሰነዝረዋለሁ በምትለው ጥቃት አትስማማም፡፡ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሙን ጂኢን የመከላከያ ሚኒስትሩን ንግግር በማጣጣል፣ አሜሪካ ማንኛውንም ዕርምጃ በሰሜን ኮሪያ ላይ ከመውሰዷ በፊት ከደቡብ ኮሪያ ይሁንታን ማግኘት አለባት ብለዋል፡፡

‹‹በኮሪያ ልሳነ ምድር የሚወሰድ ማንኛውም ወታደራዊ ዕርምጃ በደቡብ ኮሪያ ብቻ የሚወሰንና ማንኛውም አካል ከደቡብ ኮሪያ ዕውቅና ውጪ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ አይችልም፤›› ሲሉም ጂኢን ተናግረዋል፡፡ መንግሥታቸው ሁሉን ነገር መስመር በማስያዝ የጦርነት አማራጮችን በሙሉ እንደሚዘጋም አክለዋል፡፡

ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ጦርነት ጦርነት በሚሸቱ ንግግሮች የተጠመዱት አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ፣ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ተጨማሪ ውጥረትን አንግሠዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ መብረራቸውና ትራምፕም ሰሜን ኮሪያ ላይ መዛታቸው፣ ለቀጣናው አገሮች በተለይም ለደቡብ ኮሪያ አልተመቸም፡፡

ሰሜን ኮሪያ ቀድሞውንም የሚሳይል ሙከራ የምታደርገው አሜሪካ የአገሪቱን መንግሥት ለመጣል የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት እንደሆነ ኪም ሲገልጹ፣ ትራምፕ ደግሞ ኃላፊነት የማይሰማው መንግሥት የኑክሌር ባለቤት ከሆነ ለዓለም ሥጋት ነው በማለት ሰሜን ኮሪያን ያጣጥላሉ፡፡

የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ግን አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ የመንግሥት ለውጥ የማድረግና ለረዥም ጊዜያት በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ሰሜን ኮሪያውያን ላይም ምንም ጉዳት የማድረስ ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል፡፡

ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር በስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ሰሜን ኮሪያ በማንኛውም ሁኔታ ሚሳይል ማስወንጨፍ አንደሌለባት ተስማምተናል፤›› ብለዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ሁለት ታላላቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ቤዞችና ዘመን አመጣሽ የጦር መሣሪያዎች ያሉበት ጉአምን በሚሳይል እመታለሁ ብላ ማስፈራራቷ የመነጨው፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር የበረሩት የአሜሪካ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከጉአም አንደርሰን አየር ኃይል ጦር ሠፈር በመነሳታቸው ነው፡፡ በጉአም ደሴት አምስት ሺሕ ያህል የአሜሪካ ወታደሮች ሲኖሩ፣ በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ ከሚገኙት የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፖች በተለይ ለሰሜን ኮሪያ ቅርብ ናቸው፡፡

ይህ በህልውናዋ ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑን የምትገልጸው ሰሜን ኮሪያ አሜሪካ ለምታደርስባት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ስትገልጽ፣ ትራምፕ ደግሞ ሰሜን ኮሪያ አሜሪካን ማስፈራራቷን እስካላቆመች ከዚህ ቀደም ዓለም አይታው የማታውቀው እሳትና ኃይል ይወርድባታል ብለዋል፡፡

የትራምፕ አስተያየት የማይረባ ንግግር ጋጋታ ነው የሚሉት ኪም፣ በጉአም አካባቢ እሳት ሊያወርድ የሚችል አካሄድን ሊቀይሱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ግን ሰሜን ኮሪያ ጉአምን ጨምሮ በአሜሪካ ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት እንደማትሆን አምናለሁ ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰሜን ኮሪያ ምክንያት ለመከላከያ የሚውለውን ወጪ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ቃል ገብተዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የእሳትና የኃይል ውርጅብኝ ይወርድባታል ያሉትም በቂ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ላይ እሰነዝራለሁ የሚሉትን ጦርነት ባትደግፍም፣ በፓስፊክ ደሴት የአሜሪካ ገዢ ትራምፕን በመደገፍ፣ ‹‹አንዳንዴ በጥባጭን ለማስቆም አፍንጫው ላይ ጡጫ ያስፈልገዋል፤›› ብለዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ግን የፈለገው የቃላት ጦርነት ቢበዛ በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ መካከል የነገሠው እሰጥ አገባ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ትላለች፡፡ አሜሪካ በእርጋታ፣ ኃላፊነት በተሞላበት አካሄድና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እልባት እንድታደርግ፣ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሙን ጂኢን ጠይቀዋል፡፡

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...