Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምበትራምፕና በፑቲን ግንኙነት ላይ የተጋረጠው የሕግ ረቂቅ

  በትራምፕና በፑቲን ግንኙነት ላይ የተጋረጠው የሕግ ረቂቅ

  ቀን:

  በየአገሮቹ የሚታየውና የኢንተርኔት ግንኙነቶችን የሚያመሰቃቅለው የሳይበር ጠለፋ፣ በተለይም በኢኮኖሚ ላደጉትና በቴክኖሎጂ ለመጠቁት አገሮች ፈተና ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኃያላን አገሮች እርስ በርሳቸው የመረጃ መረብ ግንኙነታቸውን ሲመነታተፉ፣ መልሰው ሲወነጃጀሉም ይስተዋላል፡፡ አሜሪካ የጀርመንና እንግሊዝን የመረጃ መረብ ሰብራ ትበረብር እንደነበር፣ ሩሲያና አሜሪካም እርስ በርሳቸው በዚሁ የሳይበር ጠለፋ ስለመመሰጣቸው፣ ኳታርን ከወዳጆቿ የነጠላት የሳይበር ሸፍጥና ከጥቂት ወራት በፊትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግንኙነቶችን ያቋረጠው የመረጃ መረብ ጠለፋ፣ በቴክኖሎጂው የበለፀጉት አገሮችን በስፋት ይጉዳ እንጂ፣ ደሃ አገሮችም ቢሆኑ ከችግሩ አላመለጡም፡፡

  ከሩሲያ ጋር መልካም ግንኙት መፍጠር እንደሚፈልጉ ሥልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞ ሲናገሩ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ለአገራቸው ትልቅ ሥጋት የሆነውን የሳይበር ጠለፋ ለመግታት ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

  ትራምፕ በቅርቡ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተገናኙ በኋላ በሳይበር ጉዳይ ላይ ስምምነት ለማድረግ ሥራ ቢጀምሩም፣ ሩሲያና ምዕራባውያን ስምምነቶችንና ድርድሮችን የሚያዩበት መነጽር ፍፁም የተለያየ መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡ በተለይም በታላቋ ሶቭየት ኅብረት ዘመንም ሆነ በሩሲያ ስምምነቶች የራሳቸው ተደጋጋሚ ባህሪ አላቸው፡፡

  እንደ ዘገባው፣ ሩሲያ ማንኛውም ዓይነት ስምምነት የጉዳዩ መቋጫ ነው ብላ አታምንም፡፡ መልካም ግንኙነት ለመፍጠር መንገድ ነውም አትልም፡፡ በዲፕሎማሲ ላይ እ.ኤ.አ. በ2014 መጽሐፍ ያሳተሙት የሩሲያ ዲፕሎማቲክ አካዳሚ ባለሙያዋ ኢርና ቫስሊንኮም፣ የስምምነት ሌላ ገጽታ ጦርነት ነው ይሉታል፡፡

  ድርድር ተስማሚ ወገኖቹን ተጠቃሚ የሚያደርግና የራስን ሐሳብ ለማስተላለፍም ሆነ በተደራዳሪው ወገን በኩል የሚነሱ ሐሳቦች ላይ ጫና ለመፍጠርም ጠቃሚ ዘዴ ነው፡፡ ሆኖም ሩሲያ በስምምነቶች ላይ ወግ አጥባቂ ስትሆን፣ በራሷ ጥረት ብቻ ልታመጣው የማትችለው ጉዳይ ላይ ካልሆነ በስተቀር ወይም ከተደራዳሪው ወገን አቻ ለአቻ ካልሆነች ለጉዳዩ ተቀባይነት አትሰጥም ይባላል፡፡

  ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በብዙዎቹ ድርድሮች አዎንታዊ ምላሽ ስለምትሰጥም፣ ከሩሲያ በተሻለ ከሌሎች አገሮች ተቀባይነትን ከማግኘት በተጨማሪ ጥምረት ለመፍጠርም መቻሉም ይነገራል፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ ሪፐብሊካኖች ከሩሲያ ጋር መነጋገርንና መደራደርን ከሒትለር እንደ መደራደር ይቆጥሩታል፡፡ ይህም ማለት ሩሲያ የምዕራባውያኑን መደራደሪያ ነጥብ የጋራ ችግር ይፈታል ብላ ከመቀበል ይልቅ ከሽንገላ ትቆጥረዋለች፡፡ በዚህም ምዕራባውያኑና በተለይም አሜሪካና ሩሲያ በድርድር ዙሪያ ላይ ያላቸው አቋም የተለያየ እንደሚሆን ነው የሚታሰበው፡፡

  ሆኖም ትራምፕ ከፑቲን ጋር በሳይበር ዙሪያ ስምምነት ለማድረግ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይህ በሒደት ላይ ባለበት ወቅት ደግሞ የአሜሪካ ሴኔት በሩሲያ፣ በኢራንና በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል የሕግ ረቂቅ ላይ ምርጫ ለማድረግ ስብሰባ ተቀምጧል፡፡

  ይህን ረቂቅ ሪፐብሊካኖች በሚመሩት ሴኔት ድጋፍ ካገኘ ፕሬዚዳንት ትራምፕ  ከመፈረም ወይም በምርጫ ከመሳተፍ አንዱን መምረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጉን አልቀበልም ብለው ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ቢጠቀሙም፣ ሪፐብሊካኑ በቂ ድጋፍ ካገኙ በሕግ አውጪዎች ሊሻር ይችላል፡፡

  ትራምፕ ሩሲያን በተመለከተ ካላቸው ለዘብተኛ አቋም በመነሳት በሩሲያ ላይ ሊያሳልፉ የሚችሉትን አዎንታዊ ውሳኔ ይገድባል፣ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ትራምፕ የጀመሩትን ሥራ ያወሳስባል የተባለው አዲሱ ረቂቅ፣ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓ ኅብረትም ሥጋት ሆኗል፡፡

  ትራምፕ ከሩሲያ ጋር የጀመሩትን መልካም ግንኙነት ያወሳስባል የተባለው ቢል፣ ኢራንና ሰሜን ኮሪያንም የሚነካ ሲሆን፣ ሴኔቱ በረቂቁ ላይ ለመወሰን የተቀመጠውም፣ ሩሲያ እ.ኤ.አ. በ2014 ክራይሚያን ከዩክሬን ነፃ ማውጣቷንና ወደ ራሷ መቀላቀሏን፣ እንዲሁም በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ደግሞ ጣልቃ በመግባቷ ተከትሎ ለመቅጣት ነው ተብሏል፡፡ ሆኖም የሪፐብሊካኑ ሴናተርና የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ቦብ ኮርከር ረቂቅ ሕጉ ያለቀለት አይደለም፣ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይም መነጋገር ያለብን የተለያዩ ጉዳዮች አሉ ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ረቂቁ ከፀደቀ የትራምፕ አስተዳደር በሞስኮ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማላላት ሲፈልግ ከኮንግረሱ ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

  ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ላለፉት ስደስት ወራት የሩሲያና የትራምፕ ግንኙነት መነጋገሪያና የሚዲያውንም ቀልብ የሳበ ሆኗል፡፡ ሩሲያ እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ አልገባሁም ብትልም፣ ሩሲያ በምርጫው ላይ የመረጃ ጠለፋ በማካሄድ ትራምፕ የሚያሸንፉበትን መንገድ ስለማመቻቸቷ ምርመራ እየተደረገም ነው፡፡ የትራምፕ ልጅ ባለቤት ጄርድ ኩሽነርም፣ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ስለተገናኘበት ጉዳይ ለሁለተኛ ጊዜ የተጠየቀው፣ ሴኔቱ በቢሉ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ በተቀመጠበት ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

  የአውሮፓ ኅብረት ግን አሜሪካ በሩሲያ ላይ ለመጣል ባሰበችው አዲስ ማዕቀብ ላይ የመከፋፈል ሥጋት ተጋርጦበታል፡፡ አሜሪካ በሩሲያ ላይ የምትጥለው ማዕቀብም ለአውሮፓ ኩባንያዎች ፈተና ነው፡፡ ትራምፕ ረቂቁን ሊፈርሙ ይችላሉ ተብሎ በዋይት ሐውስ መነገሩም ለአውሮፓ አልተመቸም፡፡ በመሆኑም የአውሮፓ ኮሚሽን አሜሪካ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያቀረበችውን አዲስ ሐሳብ ለመቃወም በዝግጅት ላይ ነው፡፡ በተዘዋዋሪ የአውሮፓ ኩባንያዎችን ይጎዳል የተባለው አዲስ የሕግ ረቂቅ፣ በኅብረቱ ውስጥ ክፍፍል ሊፈጥር እንደሚችልም ሮይተርስ አሥፍሯል፡፡

  የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2014 ክራይሚያ ከዩክሬን ነፃ ወጥታ ወደ ሩሲያ በመቀላቀሏ በሩሲያ የገንዘብ ተቋማት፣ የመከላከያና የኃይል ዘርፍ ላይ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን፣ በሩሲያ ጋዝ ላይ የተመረኮዙት በተለይ ሰሜናዊ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ተጎድተዋል፡፡

  በአውሮፓ ኅብረት የቢዝነስ አውሮፓ ዳይሬክተር ማርኮስ ቤይረር አሜሪካ በግሏ የምትወስደው ዕርምጃ የአውሮፓ ኅብረትን፣ ዜጎችንና ኩባንያዎቻቸውን እንዳይጎዱ ጠይቀዋል፡፡ የአውሮፓ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ረቡዕ ሐምሌ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚመክር ሲሆን፣ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው የኃይል ኩባንያዎች ላይ በምትጥለው አዲስ ማዕቀብ፣ የአውሮፓ ኅብረትን እንዳታካትትና በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችን የሚነካ ውሳኔ እንዳታሳልፍ እንደሚጠይቁም ታውቋል፡፡

  ቀድሞውንም የሩሲያን የነዳጅ ኢንዱስትሪን ለማንኮታኮት ተብሎ በተጣለው ማዕቀብ ሩሲያን ብቻ ሳይሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ኩባንያዎችንም የጎዳ በመሆኑ፣ በአዲሱ ማዕቀብ የአውሮፓ ኅብረት አቋም ከአሜሪካ ሊለይ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img