Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  የትንሳዔ መንገድ ለአክሲዮን ማኅበራት

  ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል፤›› እንደሚባለው ሁሉ ሞኝ የሚያስመስሉን ተግባራት አይጠፉም፡፡ እንደ አገር ልንሠራቸው እየተገባን ያላከናወናቸው በርካታ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል፣ ክፍተታችንን በመገንዘብ ሠርተን ለመለወጥ ተነሳሽነታችን ዝቅተኛ መሆኑ የሌሎችን ሥፍር አልባ ሸቀጥ ተቀባይ ለመሆን አብቅቶናል፡፡

  አገሪቱ በተፈጥሮ ሀብት ስለመታደሏ የምንዘምርላትን ያህል የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ በየዓመቱ ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከምናወጣባቸው የውጭ ሸቀጦች ውስጥ ገሚሱን እዚሁ አገራችን ውስጥ አምርተን መጠቀም የምንችልባቸው ዕደሎች ቢኖሩም፣ ይህንን ለመለወጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ደካማ ሆኖ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ የጥርስ መጎርጎሪያ ስንጥር (ስቴኪኒ) በብዙ ሺሕ ዶላር እየገዛን ከውጭ ከማስገባታችን ምክንያቱ እዚሁ ለማምረት የምንችልበት አቅም ሳይሆን ትኩረት በማጣታችን የተነሳ ነው፡፡

  በተፈጥሮ ሀብታችን ልክ መጠቀም አለመቻላችን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ብልጽግና ሊመሩን የሚችሉ ቁም ነገሮች ላይ የምናፈሰው ጉልበትና ሀብት አናሳ በመሆኑም ከድህነት የመውጣት ጉዟችንን እያዳከመው ይመስላል፡፡ በቁሳዊ አካል ብቻም ሳይሆን፣ የሰው ኃይላችንን በአግባቡ ባለመጠቀም ሳቢያም የሚታይ ሰንኮፍ ነው፡፡ አገር ያፈራቻቸው ባለሙያዎች ዕውቀታቸው በሚፈቅደው ልክ ወደ ተግባር ለመመንዘር አለመቻላቸው ሲታይ ለምን? ያሰኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ሊሠሩት የሚችሉትን ሥራ የውጭ ዜጎች ሲሰማሩበት ማየት የሚያስቆጫቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ከቁዘማ የዘለለ መፍትሔ ግን ሲሰጥበት አይታይም፡፡

  ዕውቀታችንን ከገንዘባችንና ከጉልበታችን አቀናጅነት በጋራ የመሥራት ልማዳችን የላሸቀ ነው፡፡ ገንዘብ ከሕዝብ በማሰባሰብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚቋቋሙ ኩባንያዎች በየጊዜው ብቅ ቢሉም፣ በሒደት የሚታዩ ችግሮች ሕዝቡ በአክሲዮን ተደራጅቶ መሥራት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ሰበብ ሆነዋል፡፡ የሕዝብ እምነት በማጉደል አንጡራ ሀብቱን የውኃ ሽታ ያደረጉም አልታጡም፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ በአገራችን ካለው ድህነት አኳያ ሲታይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በተናጠል ለመገንባት የሚያስችል አቅም ባለመኖሩ፣ ከዚህም ከዚያም አጠረቃቅሞ በአክሲዮን ተደራጅቶ ትልቅ ካፒታል መፍጠር የብልሆች ዘዴ የመሆኑን ያህል አልተገፋበትም፡፡ በእርግጥ ጤናማ አደራጆችና አስተባባሪዎች ሲኖሩ በአክሲዮን አማካይነት የሚፈጠር ኢንቨስትመንት ለባለአክሲዮኑም ለአገርም መጥቀሙ አያጠያይቅም፡፡

  በቅርቡ በሪፖርተር ጋዜጣ እንደተነበበው ዘመናዊ ሆስፒታል ለማቋቋም የተጀመረውን ጥረት ስንመለከት፣ ስለአክሲዮን ኩባንያዎች ዳግመኛ እንድናስብ ይገፋፋናል፡፡ በአክሲዮን በሚዋጣ ገንዘብ ሊገነባ የታሰበው ሆስፒታል፣ ለአገራችን ታካሚዎች ብቻም ሳይሆን፣ በሕክምና ቱሪዝም በኩል ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እንድትታወቅ ብሎም፣ በከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት መስክ የሚታየውን ችግር ለመቀነስ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሲነገር ቆይቷል፡፡ የጋዜጣው ዘገባም ይህንኑ ያሳያል፡፡ በህንድ ወይም በታይላንድ ወይም በደቡብ አፍሪካ የጤና ምርመራ ለማድረግ 600 ዶላር ይከፈላል፡፡ ለከፍተኛ የሕክምና ክትትል የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሲሰላም፣ ለሕክምና የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ መጠን የትየለሌ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

  ከአክሲዮን ኩባንያው መሥራቾች የተደመጠውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የውጭ አገር የሕክምና ጉዞ በማስቀረት እዚሁ ለመታከም የሚያስችለው ተቋም በእርግጥም ዕውን ከተደረገ፣ ጠቀሜታው ወደ ውጭ የሚፈልሰውን ታካሚ መታደግ ብቻም ሳይሆን ከውጭ የሚመጡትንም በማከም የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡

  ይህንን ዘርፍ በጥንቃቄ አጥንቶ ለመፍትሔ መነሳሳቱ ትልቅ ቁም ነገር ነው፡፡ በሌላ አንፃር ሲታይ የአክሲዮን ኩባንያዎች ምሥረታ በተቀዛቀዘበት ወቅት፣ እንዲህ ያለ ፕሮጀክት ይዘው ብቅ ያሉት አደራጆች መንገዳችሁን ሳትስቱ ግፉበት እንድንላቸው የሚገፋፋ ነው፡፡

  የተባለው ፕሮጀክት በተባለው መሠረት ሥራ ላይ እንደሚውል መመኘቱ ተገቢ ቢሆንም፣ ቁም ነገሩ ግን ቃላቸውን በተግባር መዋላቸው ላይ የሚታይ ነው፡፡ አደራጆቹ ለዚህ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አካሄዳቸው እንደተንኮታኮቱት የአክሲዮን ኩባንያዎች እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ ለሕዝብ ሀብትና ጥሪት ታማኝ ከመሆን አልፈው ለአገሪቱን አዲስ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የእነሱ ስኬት ለሌሎች ኩባንያዎች ዳግመኛ ማቆጥቆጥ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ያሉትን የሚሠሩ መሆናቸው ትልቅ ዋጋ አለው፡፡

  መንግሥትም እንዲህ ያሉ የቢዝነስ ውጥኖችን መርምሮ አዋጭነታቸው መሆኑን በማረጋገጥና በመቆጣጠር አገሪቱም ሕዝቧም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የአክሰሲዮን ኩባንያዎች የታጣውን እምነት ለመመለስ የአክሲዮን ኩባያዎች የሚመሩበትን ሕግ መሥራቱ የሚመሰገን በመሆኑ፣ በረቂቅ ደረጃ የሚንቀራፈፈውን አዋጅ በቶሎ አጽድቆ ሥራ ላይ ማዋሉ ላይ ትኩረት ቢደረግበት ይበጃል፡፡

  አዋጁ እስካሁን የታዩትንና ወደፊትም የሚመጡትን ችግሮች ለመቅረፍ፣ ዜጎችም በአቅማቸው መጠን ካፒታል አሰባስበው ጠቃሚ ነገር ሠርተው እንዲጠቀሙ ማድረግም ከደጃችን የሚገኝ ብልህነት ነው፡፡ ለአክሲዮን ኩባንያዎች ትንሳዔ እንዲመጣ የሚያደርጉ አሠራሮች ይበራቱ፤ ይበራከቱ፡፡  

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት