Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱ ተገለጸ

  በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱ ተገለጸ

  ቀን:

  የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በመጠቀም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የልማት ፋይናንስ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተጠቅማ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንደምትሠራ ተናግረዋል፡፡

  በበጀት ዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 84 ግዙፍ ኩባንያዎች በአገሪቱ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተከናወነው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡

  በዚህ ዓመት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው አማካይነት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ለውጭ ምርቶች ገበያ በማፈላለግ፣ በቱሪስት ፍሰት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የቴክኒክና ሙያ ድጋፍ በማድረግ የተገኘው ውጤት ስኬታማ እንደነበር ተገልጿል፡፡

  ‹‹በአገሮች መካከል የሚደረግ ግንኙነት የፖለቲካ ዲፕሎማሲ አንዱ መገለጫ ቢሆንም፣ የላቀ ግንኙነት ማሳያው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኤምባሲዎች የሙሉ ጊዜ ሥራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስኬት መለኪያ ዲፕሎማሲው የአገሪቱን የልማት ፍላጎት ምን ያህል አግዟል የሚል መሆኑንም ቃል አቀባዩ አውስተዋል፡፡

  ስለሆነም ዲፕሎማሲው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ የአገሪቱን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ ለኤክስፖርት ምርቶች ሰፊና አስተማማኝ ገበያ ማስገኘት፣ የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ለገቢ ምርቶች የተሻለ ዋጋና አስተማማኝ አቅራቢ ማፈላለግ፣ እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳደግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሚሲዮኖች ባደረጉት ጥረት 144 ኩባንያዎች የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ 984 አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና የኢንቨስትመንት አዋጭነት ጥናት እንዲያካሄዱ መደረጉንም አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡

  ይኼንን ለማሳካት ሲባልም የቢዝነስ ፎረም፣ የንግድ ትርዒቶችና የቱሪዝም ኤግዚቢሽንና ፕሮሞሽኖች እንደተካሄዱ አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ከቱርክ፣ ከጃፓን፣ ከሞሮኮ፣ ከብራዚልና ከሌሎች አገሮች ጋር ከ31 በላይ የቢዝነስ ፎረሞች መካሄዳቸውን አውስተዋል፡፡ 672 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የቢዝነስ ትስስር መፍጠራቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ ባለሀብቶች አብላጫውን ቁጥር የያዙት፣ ከእስያና ከኦሽኒያ ክፍላተ አኅጉር የሚመጡ ባለሀብቶች ናቸው ብለዋል፡፡

  ባለሀብቶች በአብዛኛው መሰማራት የሚፈልጉባቸው መስኮችም የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የብረታ ብረትና ኤሌክትሮኒክስ፣ ግብርናና አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ታዳሽ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን፣ የመጠጥ ውኃ፣ ፋርማሲዩቲካልና ኬሚካል ኢንቨስትመንትና ማሽነሪዎች ማምረት እንደሆነ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

  ‹‹በኢንጂነሪንግና የመሠረት ልማት ቴክኖሎጂ ሽግግር መስክም 60 የቴክኖሎጂ ሽግግርና 236 የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዕድሎች ጥቅም ላይ ውለዋል፤›› ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱም 122 የገበያ ዕድሎች ለማመቻቸት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ከ490 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

  አቶ መለስ በመግለጫቸው ወቅት እንደተናገሩት፣ አገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳቷ ሌሎች የውጭ አገር ባለሀብቶች ደስተኛ መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በዚህም ወደፊት አገሪቱ ከዚህ የተሻለ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደምትሆን ገልጸዋል፡፡

  በኬኒያ በተካሄደው ምርጫ እየተገለጸ ያለውን ውጤት ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው ሥጋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደማይደርስ፣ ችግሩንም ኬንያውያን የሚፈቱት በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሥጋት እንደማይፈጥር አስረድተዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...