Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ድርጅቶች ሳይጨመሩ የአገሪቱ ብድር 23 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተበደሩት ሳይደመር የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ብቻ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 30.4 ቢሊዮን ብር ተበድሯል፡፡ ሚኒስቴሩ እስካሁን የተበደረው 23 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተመልክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በአጠቃላይ በ2009 ዓ.ም. ከብድር 68.268 ቢሊዮን ብር (3.04 ቢሊዮን ዶላር)፣ ከዕርዳታ 30.384 ቢሊዮን ብር (1.35 ቢሊዮን ዶላር)፣ በድምሩ 98.876 ቢሊዮን ብር (4.41 ቢሊዮን ዶላር) የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የአገሪቱ ብድር የመክፈል አቅም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከውጭ ለተበደርነው ብድር 0.7 ቢሊዮን ብር፣ ከአገር ውስጥ ለተበደርነው 5.1 ቢሊዮን ብር ክፍያ ፈጽመናል፤›› በማለት አቶ ሐጂ ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥለው 2010 በጀት ዓመት ደግሞ ሚኒስቴሩ ከውጭና ከአገር ውስጥ አገሪቱ ያለባትን ብድር ለመመለስ 16 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ቢሄድም አገሪቱ ከኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ በታሰበው ልክ ባለመሄዱ በብድር አከፋፈል ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡

ይህም በመሆኑ በተለይ ከፍተኛ ወለድ ያላቸው ኮሜርሻል ብድሮች ለጊዜው እንዲቆሙ መደረጉን አቶ ሐጂ ገልጸው፣ መንግሥት ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በሙሉ አቅሙ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ የምትበደረውን ብድር ለመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የውጭ ምንዛሪ ለሚያመነጩ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደምታውል ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ብድሩን ለመመለስ በዋነኛነት ግምት ውስጥ የሚገባው የኤክስፖርት ገቢ መጠን ነው፡፡ ከመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጀምሮ፣ የኤክስፖርት ገቢ በዕቅዱ መሠረት መጓዝ ባለመቻሉ የአገሪቱን የመበደር ፍላጎት እንዲገታ ተመልክቷል፡፡

በተጠናቀቀው 2009 በጀት ዓመት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት 6.7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ይህንን ዕቅድ ከልሶ ወደ 4.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ማሳካት የተቻለው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ይህ የኤክስፖርት መጠን ለአገርና ለውጭ ግዢዎች ጭምር የሚውልም በመሆኑ ተፅዕኖ መፍጠሩን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

በተለይ ለመሠረተ ልማት ተቋማትና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ ብድር እየተበደሩ በመሆኑ፣ መንግሥት በ2010 በጀት ዓመት ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከኤክስፖርት በማግኘት ችግሩን መስበር እንደሚፈልግ ተገልጿል፡፡

በ2009 በጀት ዓመት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ የተገኘና የፈሰሰ የውጭ ሀብት

ኢትዮጵያ የውጭ ብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ከሁለት ምንጮች ሲሆን እነዚህም፣

 • የመልቲላተራልና የመንግሥታት ትብብር (ባይላተራል) ናቸው፡፡

1. ግኝት (Commitment)  

 • ከመልቲላተራል ምንጮች በ2009 በጀት ዓመት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ
  • በብድር ብር 24.850 ቢሊዮን
  • በዕርዳታ ብር 15.164 ቢሊዮን
  • በአጠቃላይ ብር 40.014 ቢሊዮን አዲስ ብድርና ዕርዳታ ተገኝቷል፡፡
 • በተመሳሳይ ወቅት

ከመንግሥታት ትብብር (ባይላተራል) ምንጮች በ2009 በጀት ዓመት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ ደግሞ

 • በብድር ብር 43.642 ቢሊዮን
 • በዕርዳታ ብር 15.220 ቢሊዮን
 • በአጠቃላይ ብር 58.862 ቢሊዮን አዲስ ዕርዳታና ብድር ተገኝቷል፡፡
 • በአጠቃላይ በ2009 በጀት ዓመት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ

ከሁለቱ ምንጮች

 • በብድር ብር 68.268 ቢሊዮን
 • በዕርዳታ ብር 30.384 ቢሊዮን
 • በአጠቃላይ ብር 98.876 ቢሊዮን አዲስ ዕርዳታና ብድር ተገኝቷል፡፡

2. ፍሰት (Disbursement)

 • በ2009 በጀት ዓመት አሥራ ሁለት ወራት ውስጥ ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ

ከመልቲላተራል ምንጮች

 • ከብድር ብር 30.330 ቢሊዮን
 • ከዕርዳታ ብር 13.401 ቢሊዮን
 • በአጠቃላይ ብር 43.731 ቢሊዮን የውጭ ሀብት ፍሰት ተገኝቷል፡፡
 • በሌላ በኩል ከመንግሥታት (ባይላተራል) ምንጮች
  • ከብድር ብር 20.541 ቢሊዮን
  • ከዕርዳታ ብር 14.560 ቢሊዮን
  • በአጠቃላይ ብር 35.101 ቢሊዮን የውጭ ሀብት ፍሰት ተመዝግቧል፡፡
 • በአጠቃላይ ከሁለቱም ማለትም ከመልቲላተራልና ባይላተራል ምንጮች
  • ከብድር ብር 50.871 ቢሊዮን
  • ከዕርዳታ ብር 27.961 ቢሊዮን
  • በአጠቃላይ ብር 78.832 የብድርና ዕርዳታ ፍሰት ተገኝቷል፡፡

የ2009 በጀት ዓመት የግኝትም ሆነ ፍሰት አፈጻጻም የተሰላው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ከጁላይ 8 ቀን 2016 እስከ ጁላይ 7 ቀን 2017 ባለው አማካይ የምንዛሪ ተመን 1 ዶላር = 22.436 ብር ተባዝቶ ነው፡፡

ምንጭ፡- የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች