በየመን አድርገው ወደ ሌሎች አገሮች ለመሄድ ሲያደርጉት በነበረው ጉዞ፣ ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. 160 ኢትዮጵያዊያን በየመን ባህረ ሰላጤ ተወርውረው መገደላቸው ተገለጸ፡፡ ከአንድ ቀን በፊትም 50 ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ድርጊት ሕይወታቸው ማለፉ ተጠቁሟል፡፡
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ዓርብ ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፣ የየመን ግዛት በሆነችውና ሻብዋ ተብላ በምትጠራው አካባቢ 160 ኢትዮጵያውያን በጀልባ ሲጓዙ የባህር ላይ ወንበዴዎች ወደ ባህሩ ወርውረዋቸው ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ድርጊት ከመከሰቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተመሳሳይ 50 ኢትዮጵያዊያንና ሶማሊያዊያን ስደተኞች፣ በዚህ ሁኔታ ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቋል፡፡ አሥራ ሦስት ኢትዮጵያውያን የደረሱበት አልታወቀም ብሏል፡፡
አይኦኤም እስካሁን ባደረገው ፍለጋ በሁለት ቀናት ውስጥ ወደ ባህሩ ተወርውረው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ከተደረጉት 160 ዜጎች መካከል፣ የሁለት ወንዶችንና የአራት ሴቶችን አስከሬን ብቻ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ድርጅት እንዳስታወቀው፣ በዓመት በሺሕ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች በዚህ አካባቢ አቋርጠው ሲሄዱ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ የየመን ባህረ ሰላጤ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ስደተኞች አቋርጠው ሲሄዱ፣ የከፋ ጉዳት እንደሚደርሰባቸው ድርጀቱ አስታውቋል፡፡
በየመን በኩል የሚደረገው የስደተኞች ጉዞ እጅግ ከባድና ለስቃይ የሚዳርግ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በዚህ አካባቢ ተቋሙ የሥነ ልቦና አማካሪዎችን በማሰማራት፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን መከራና እንግልት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አትቷል፡፡ እንደ አይኦኤም ሪፖርት እ.ኤ.አ በ2017 ብቻ በየመን በኩል በሚደረገው ስደት 144 ስደተኞች ከጀልባ በግድ ወደ ባህር ተወርውረው እንዲሞቱ መደረጉን ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚህ አሰቃቂ ጉዞ በሕይወት የተረፉ ስደተኞች በባህር ላይ ዘራፊዎችና ወንበዴዎች ከፍተኛ የሆነ ስቃይ እንደሚደርስባቸው መናገራቸውን አይኦኤም ገልጿል፡፡ በዚህ አካባቢ የሚደረገው የስደተኞች ጉዞ ስቃይ የበዛበት ከመሆኑ በላይ፣ ወንበዴዎች በጣም የተደራጁና በሚስጥር የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን አክሏል፡፡ በጉዟቸው ወቅት ከሚጠየቁት ተጨማሪ ክፍያ ባሻገር ሌሎች ጉዳቶችም እንደሚያደርስባቸው ጠቁሟል፡፡
ወደ ባህር ከተወረወሩ 160 ኢትዮጵያን መካከል በሕይወት የተገኘ እንደሌለ አይኦኤም አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡ ዓርብ ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የተደራጀ መረጃ እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡