Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናከቻይናዊው ባለሀብት አምስት ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉ ዓቃቢያነ ሕግ ክስ ተመሠረተባቸው

  ከቻይናዊው ባለሀብት አምስት ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉ ዓቃቢያነ ሕግ ክስ ተመሠረተባቸው

  ቀን:

  ንብረትነቱ የቻይናዊ ባለሀብት የሆነው ሲሲኤስ ኮም ሰርቪስ ሶሉዩሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሠራተኞች የተመሠረተባቸውን የግብርና ታክስ ክስ ለማቋረጥ በመስማማት፣ የአምስት ሚሊዮን ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሁለት ዓቃቢያነ ሕግና ሦስት ግለሰቦች ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

  ተከሳሾቹ ዓቃቢያነ ሕግ አቶ አበበ ብርሃኔና አቶ ጌታ ሰው ተሰማ የሚባሉ ሲሆኑ፣ ጉቦውን ለማቀባበልና ስምምነት ላይ ለማድረስ ተባብረዋል የተባሉት ደግሞ አቶ በላይነህ ፈንታ፣ አቶ አክሊለ ብርሃን አባቡና አቶ አብዮት ተስፋዬ ናቸው፡፡

  የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ዓቃቢያነ ሕጉ የኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ ናቸው፡፡ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸውን ሲሲኤስ ኮም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሠራተኞች የክስ መዝገብ ምርመራ ከመምራት ጀምሮ ክትትል ሲያደርጉ ነበር፡፡

  ክስ የተመሠረተበትን የተጠቀሰውን የቻይና ኩባንያና ሠራተኞች በዋስ እንዲወጡ፣ ክሱን ለማቅለልና በነፃ እንዲለቀቁ ለማድረግ ከሦስቱ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር የድርጅቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ው ዣንግን ጉቦ መጠየቃቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

  ዓቃቢያነ ሕጉን ለማገናኘት አቶ በላይነህና አቶ አክሊለ ብርሃን የድርጅቱን ኃላፊዎች ሚስተር ው ዣንግንና ሚስተር ዱዩን በተለያዩ ካፌዎች በተለያዩ ጊዜያት በማግኘትና በማግባባት፣ ተከሳሾች ጓደኞቻቸው እንደሆኑና ሊረዷቸው እንደሚችሉ በመግለጽ እንዳግባቡዋቸው ክሱ ያስረዳል፡፡ ለሁለቱ ተከሳሾች ሦስት ሚሊዮን ብር፣ እነሱ ለሚያገናኙበት ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ብር በድምሩ 4.5 ሚሊዮን ብር እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውንም አክሏል፡፡ ገንዘቡንም በቼክ ሳይሆን በጥሬ ገንዘብ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውንና ማግባባታቸውንም አክሏል፡፡

  በመጨረሻም ግብረ አበሮች ናቸው የተባሉ ተከሳሾች አቶ በላይነህና አቶ አክሊለ ብርሃን፣ ቻይናውያኑን ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በማግኘት እንዳስተዋወቋቸውና አምስት ሚሊዮን ብር ከከፈሉ ክሱ እንደሚቋረጥላቸው በድጋሚ በመንገር ማደራደራቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ሚስተር ዱዩ የተባሉ ቻይናዊ ገንዘቡን ለመስጠት እንደተስማሙ ገልጾ፣ ገንዘቡን ሲሰጡ ግን ሁለቱም ዓቃቢያነ ሕግ እንዲገኙ መስማማታቸውንም አክሏል፡፡ በስምምነታቸው መሠረት ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ሲሆን፣ ቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ አካባቢ በተከሳሽ አቶ አብዮት መኪና ውስጥ ከተገናኙ በኋላ፣ 50,000 ብር ጥሬ ገንዘብና 4,950,000 ብር በቼክ በተከሳሽ አቶ በላይነህ አማካይነት ሲቀበሉ፣ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀናለ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 10(3)ን ተላልፈው በመገኘታቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ጉቦ የመቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

  ለተከሳሾቹ ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ክሱ ተነቦላቸው የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው ተጠይቀው እንዳላቸው በመግለጻቸው፣ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ ማረሚያ ቤት ተልከዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img