Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢኮኖሚው ዕድገት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፌዝ አቢዮዱን የተባሉ ናይጄሪያዊ ጸሐፊ፣ ከሰሞኑ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሚነሱበትን ጥያቄዎች የተመለከተ ትንታኔ አስነብበዋል፡፡ ፊውቸር አፍሪካ የተባለውን ተቋም በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት አቢዮዱን፣ ከቀናት በፊት ያስነበቡት ጽሑፍ በአብዛኛው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ስለ ኢትዮጵያ ባቀረበው ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት በኢኮኖሚ ዕድገታቸው በዓለም ፈጣን ከሚባሉ 12 አገሮች ተርታ ትመደብ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት ከግንባር ቀደሞቹ አንዷ በመሆን የፊተኛው መስመር ላይ እንደምትገኝ በጽሑፋቸው በመግቢያው አስፍረዋል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ አሥር አገሮች ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡

ኡዝቤኪስታን፣ ኔፓል፣ ህንድ፣ ታንዛኒያ፣ ጂቡቲ፣ ላኦስ፣ ካምቦዲያ፣ ማይናማር እንዲሁም ፊሊፒንስ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ7.6 እስከ 6.9 በመቶ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ እየተጓዙ የሚገኙና በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አሥሩ አገሮች ተብለው ሲቀመጡ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ቡድን በቀዳሚነት እየመራች የምትገኘው በ8.3 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት መሆኑን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም አትቷል፡፡

የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት 2.7 በመቶ በሆነበት ወቅት ለኢትዮጵያ የተቀመጠው የዕድገት ትንበያ 8.3 በመቶ በመሆኑ፣ አገሪቱ የዓለምን አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በ5.6 በመቶ ብልጫ እየተራመደች መጓዝ መቻሏም ኢትዮጵያን ከዓለም ፈጣኗ በዕድገት የምትመነደግ አገር አሰኝቷታል፡፡ ይህንኑ እውነታ የአገሮችን ብድር የመመለስ ግምት በማስላት ደረጃ የሚያወጡ ትልልቅ ተቋማት ትንታኔም እያረጋገጠው ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ ሙዲስ የተባለው ኩባንያ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ኢትዮጵያ በዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ሥሌት የስምንት በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ እንደምትጓዝ አትቷል፡፡ ይህም ለአገሪቱ የብድር የመመለስ አቅም ምዘና ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ይገመታል፡፡

ሰሞኑን በቻይናው ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ (ሲጂቲኤን) ባቀረበው የውውይት መድረክም በአሜሪካ ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባል ለመሆን የምረጡኝ ቅሰቀሳ የጀመሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ቴድ ዓለማየሁን ጨምሮ፣ የቀድሞው የኧርነስት ኤንድ ያንግ ሜኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱና ሌሎችም የውጭ አገር ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ተወያይተዋል፡፡ አገሪቱ ስለምትከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና፣ ሞዴል በምታደርጋቸው የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ስለተቃኘው የልማት ስትራቴጂዋ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡  

ወደ ናይጄሪዊው ጸሐፊ ስንመለስ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግስጋሴ ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካ ተምሳሌትነት እንዳለው ይዘክራሉ፡፡ በተለምዶ የአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚለካበትና ዓለም አቀፍ የመለኪያ ቀመር በመሆኑ ስምምነት የተደረሰበት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ግሮስ ዶሜስቲክ ፕሮጀክት- ጂዲፒ) ባሻገር እውነተኛውን የአንድ አገር ግስጋሴ ይለካል ተብሎ በሚታመንበት፣ የሰዎችን የአኗኗር ሁኔታና ለውጥ የሚመዝነው ‹‹ሒውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ›› መለኪያም ቢሆን ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን ለውጥ ከሚያሳዩ አገሮች ተርታ አሠልፏታል፡፡ የጠቋሚ መለኪያ ዘዴው የትምህርት ሥርጭትን፣ የዕድሜ ጣሪያን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢን በማስላት የሰብዓዊ ልማት ለውጦችን ይመዝናል፡፡ ሆኖም አንዳንድ አገሮች ግን ከዚህም ያልፉና የሕዝባቸውን የደስተኛነት ደረጃ ጭምር እንደ መመዘኛ ሲጠቀሙበትም ይታያሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የታየው የሰብዓዊ ልማት በዓለም ሁለተኛዋ ፈጣን የለውጥ አገር ለመባል አስችሏታል፡፡ ከድህነት ወለል በታች ይኖር ከነበረው 55 በመቶ ሕዝቧ፣ አሁን ላይ ከ25 በመቶ በታች ዝቅ ማለቱም የዓለም ባንክ ያረጋገጠው እምርታ እንደሆነ ሲነገር ቢያንስ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በመሠረተ ልማቱ በተለይ በመንገድ ግንባታ እ.ኤ.አ. በ2000 የነበረው አገር አቀፍ 28,000 ኪሎ ሜትር የመንገድ ኔትወርክ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በነበረ አኃዝ ወደ 110,000 ኪሎ ሜትር ተስፋፍቷል፡፡ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከሁለት ዓመት በፊት 40 ሚሊዮን ገደማ መድረሱ ሲጠቀስ፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ወደ አሥር ሚሊዮን ማሻቀቡ በውጭ ተንታኞች ዕይታ ከለውጦች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ 

በሰው ለውጥ ላይ የሚለካው ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ በተለይ የእናቶች ሞትን እስከ 70 በመቶ መቀነስ መቻል እንዲሁም የውልደት መጠን እየቀነሰ መምጣት ሁሉ ለአገሪቱ በዜጎች የዕድሜ ጣሪያ ወይም ረዥም ጊዜ የመኖር ዕድልን በመጨመርም ኢኮኖሚው የሚጨበጥ ለውጥ ማሳየቱ እየተነገረለት መጥቷል፡፡ መንግሥታቸው የአርማታና ብሎኬት መደርደር ሥራን በማከናወን ብቻ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዳላመጣ ለማስረዳት ይመስላል፣ የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነትና ክትትል ድጋፍ ዘርፍ ሚኒስትር ኃላፊው አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ከወትሮው በተለየ አገላለጻቸው እንዲህ ያሉትን የሰብዓዊ ልማት መለኪያ ለውጦች በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹ መደመጥ የጀመሩት፡፡

ይህም ሁሉ ተብሎ ግን አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከዓለም አሥር ደሃ አገሮች ውስጥ አንዷ ከመሆን እንዳላዳናት የጠቀሱት አቢዮዱን፣ መንግሥት ግን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች መደዳ ኢትዮጵያን የማስቀመጥ ትልም እንዳለውና ከዚህ ምድብ አገሪቱን ነፃ የማውጣት ዕቅዱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፎቹን አገሮች ማለትም ደቡብ አፍሪካንና ናይጄሪያን ሳይቀር የመቅደም ተስፋ እንዳላት መተንበያቸውም ይታወሳል፡፡ ይህም ምናልባት ከሦስት አሥርታት በኋላ ዕውን ሊሆን እንደሚችል ሎፔዝ ይገምታሉ፡፡ ይህ ግን ሊሆን የሚችለው በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በዚሁ መቀጠል ከቻለ ነው፡፡ አቢዮዱን ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምን የተለየ ነገር ሠርታለች?›› በማለት ላነሱት ጥያቄ ራሳቸው ያሰፈሩት ምላሽ አጭር ነው፡፡ ከባድ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት፡፡ ይኸው ነው፡፡

በየብስና በአየር የተካሄዱ የመሠረተ ልማት መስፋፋቶች (የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚውና ትልቁ እንዲሆን ማድረግን ጨምሮ) በባቡር መሠረተ ልማት ድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር መገንባቱ ለአገሪቱ እሰየው ከሚያስበሉ የለውጥ ምሳሌዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ የተዘረጋው የ750 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር መዘርጋቱ፣ የኢንዱትሪ ፓርኮች መትከሉና ሌሎችም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመሠረተ ልማት አውታሮች ያልመለሷቸው ወሳኝ ጥያቄዎች ብቅ እያሉ ነው፡፡

አንደኛው እንግዲህ መንግሥት በየዓመቱ የሚመድበው የመሠረተ ልማት በጀት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት በዚህ ዓመት የመደበው በጀት ከ320 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተመድቧል፡፡ በተለመደው አካሄድ ከቀጠለ፣ መንግሥት ለመሠረተ ልማት አውታሮች እስከ 60 በመቶ ከዋለም፣ ከ190 ቢሊዮን ብር በላይ ለዚሁ ተግባር እንደሚውል ይጠበቃል፡፡ ይህንን የበጀት ፍላጎት ለማሟላት ከአገር ውስጥ ፋይናንስ በተጓዳኝ ዓይነተኛው መንገድ ብድር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ የሚጓዘው የባቡር ግንባታ ከ70 በመቶ በላይ ወጪው የተሸፈነው በቻይና መንግሥት ብድር ነው፡፡ በመሆኑም የቁጥጥር ሥራ የሚሠሩ፣ ቴክኒሻኖች፣ የባቡር ጣቢያ ኃላፊዎችና ሌሎችም ለአምስት ዓመት ያህል ኢትዮጵያውያን እስኪሠለጥኑና ቦታውን እስኪረከቡ ድረስ የባቡር ትራንስፖርት ሥርዓቱን በመምራት ይቀጥላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የሌሎችንም በራፍ ማንኳኳት ግድ ሆኗል፡፡ በዚህ ሳቢያ አገሪቱ የኢኮኖሚዋን ዕድገት በማቀላጠፍ ለመጓዝ በምታደርገው መፍጨርጨር የብድር ዕዳ እየተቆለለባት መሄዱ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለልማት እየተባለ የሚመጣው ብድር ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ እንደደረሰ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ የሚያመላክተውም አገሪቱ አብዛኛውን ብሔራዊ ገቢዋን የብድር ዕዳ ለመክፈል እንደምታውለው መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየተነተኑ ነው፡፡ የብድር ዕዳ ክፍያው የሚከናወነውም ከወለድ ጭምር ያውም በአሁኑ ጊዜ እየተበራከተ ከመጣው የአጭር ጊዜ ብድር ጋር አብሮ በመሆኑ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ግስጋሴ ሥጋት ላይ ጥሎታል፡፡ ጸሐፊው አቢዮዱን በብድር ዕዳ ክምችት ላይ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ያወጣውን ሪፖርትም ያጣቅሳሉ፡፡

ምንም እንኳ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአገሪቱ የብድር ዕዳ ክምችት አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ሲናገሩ ቢደመጡም፣ የብድር ዕዳው መልኩን እየቀየረ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ የቻይና መንግሥት ከፍተኛ አበዳሪ በመሆኑና እስካሁንም ያልተከፈለው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ከኢትዮጵያ እንዲከፈለው እየተጠባበቀ በሚገኝበት ወቅት፣ ካቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የባለቤትነት ድርሻ መጋራት እንደሆነ እየታየ ነው፡፡

ለአብነት የሚጠቀሰው ደግሞ በቅርቡ የ40 በመቶ ድርሻው እንዲሰጠው የጠየቀው የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ይገኝበታል፡፡ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሚተዳደረው ይህ ተቋም በአፍሪካ ስመ ገናና በመሆን ከንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አስተዳደር የዘለቀበት መንገድ፣ በዚህ ዘመን ቀስ በቀስ እያከተመ የመጣ ይመስላል፡፡ የብድር አመላለስ ጉዳይን በተመለከተ የመንግሥት ምላሽ ቁጥብነት ላይ የተመረኮዘ ሆኗል፡፡ ካለበት የዕዳ ጫና አኳያ በየዓመቱ ተመላሽ የሚደረገው መጠን አነስተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር መከፈሉ ሲታወስ፣ ዘንድሮ የዚህን እጥፍ ማለትም 16 ቢሊዮን ብር ለብድር ዕዳ እንደሚከፈል ይፋ ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳ የገንዘቡ መጠን አገሪቱ ካለባት ዕዳ አኳያ ዝቅተኛ ቢመስልም፣ በአንድ ዓመት ውስጥ በእጥፍ መጨመሩ ግን የብድር ዕዳ ክፍያ ጥያቄዎች እየተበራከቱ ለመምጣታቸው አስረጅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በአገሪቱ የኢኮኖሚ ግስጋሴ ውስጥ ምላሽ አጥተዋል የሚባልላቸው ጉልህ ጥያቄዎች ግን ከዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ጋር የሚያያዙም ናቸው፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም እንደተወሳው ኢትዮጵያ በምታራምደው የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ውስጥ የዕድገቷን ያህል የማይዘመርለት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ መሆኑ ተወስቷል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) እንዳረጋገጡት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም አንዱ ትችትም ይኼው ነው፡፡ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ፖሊቲካዊ አንድምታው በፕሬስና በመሰብሰብ ነፃነት ላይ ጥላውን እንዳጠላበት፣ በኢንተርኔት ከባድ ቁጥጥርና በመሳሰሉት ሳቢያ የአገሪቱም የውጭ ዜጎችም በአስተዳደሩ ከባድ ተፅዕኖ ሥር በመውደቅ በፍራቻ እንዲኖሩ ማስገደዱን ናይጄሪያዊው ጸሐፊ ይጠቅሳሉ፡፡

እንዲህ ያሉትን ክሶች የሚያጠናክረው ደግሞ ከሰሞኑ ከወደ አሜሪካ የተደመጠው ዜና ነው፡፡ ለአሜሪካ ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ዕይታ የተመራው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተው የኢትዮጵያን ጉዳይ ምክር ቤቱ ከዕረፍት ሲመለስ እንዲመለከተው የሚቀርብለት አጀንዳ መሆኑ የተሰጠውን ትኩረት አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ያስመዘገበችው ውጤት ላይ ጥላ እንደሚያጠላበት ከወዲሁ ቢነገርም መንግሥት ወዲያወኑ እንዳስተባበለው አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች