Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ታካሚዎች በኢትዮጵያ ሐኪሞች ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል››

ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአጥንት ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊና ተባባሪ ፕሮፌሰር

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ ናቸው፡፡ በሆስፒታሉ ስፔሻሊስት ሐኪም ከመሆናቸው ባሻገር የአጥንት ሕክምናም አማካሪ ናቸው፡፡ ስለ አጥንት ሕክምና እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአጥንት ሕመም እንዴት ይከሰታል?

ዶ/ር ብሩክ፡- የአጥንት ሕመም በስፋት የሚከሰተው በአደጋ ጊዜ ነው፡፡ አሁን በአገሪቷ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ ደግሞ የበለጠ ቁጥሩን እየጨመረ አንዲመጣ አድርጎታል፡፡ በዚህም መሠረት የእኛ ባለሙያዎች ያለ ዕረፍት ዕርዳታቸውን እያደረጉ ነው፡፡ ሌላኛው የአጥንት በሽታ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የሚከሰት  ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ውጭ አገር አምርተው የአጥንት ሕክምና እንዲደርጉ ውሳኔያችሁን ያገኙ ታካሚዎች ባገር ውስጥ መፍትሔ ያላገኙበት አጋጣሚ ምን ነበር?

ዶ/ር ብሩክ፡- ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲታከሙ ጉዳያቸው የታየላቸው ታካሚዎች አሉ፡፡ በሽታው በጣም ውስብስብ ሲሆንና ሕክምናው በአገር ውስጥ የማይሰጥ ሲሆን ብቻ ወደ ውጭ ይጻፍላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የታካሚዎች ፍላጎትን በማከል መልኩ ይከናወናል፡፡ ግን ቀደም ብለን ክትትል ስናደርግላቸው የሚሄድ የማይሄደውን እንለያለን፡፡ እሱም ደግሞ በባለሙያዎች ከፍተኛ ድጋፍ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ እምብዛም ከሌላው ዓለም ያነሰ ሕክምና እያደረግን ነው ማለት አያስደፍርም፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ሕክምናውን የሚከታተል የአጥንት ሕመም ታካሚ ውጭ አገር ሄዶ እንዲታከም ውሳኔ የሚሰጠው በምን ዓይነት መንገድ ነው?

ዶ/ር ብሩክ፡- ውጭ ሄዶ እንዲታከም ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት የታካሚው ሁኔታ በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ ታካሚው የሚያስፈልገው ሕክምና ለማግኘት ያጋጠመው ሕመም ከተፈጥሮ ነው ወይስ በሒደት የመጣ? ወይንም ደግሞ በአደጋ የሚለው ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ከዛም በኋላ በሽታው በአገር ውስጥ ሕክምና የማይቻል መሆኑና አገር ውስጥ ካለው የሕክምና  አቅም በላይ ከሆነ ወደ ውጭ ሄዶ እንዲታከም ይወሰናል፡፡ የውሳኔው ሒደት አምስት አባላት ያሉበት ኮሚቴ አለው፡፡ ባለሙያዎቹ ጉዳዩን ከተከታተሉትና ከተወያዩበት በኋላ ውሳኔ ላይ ደርሰው ታካሚው ወደ ውጭ ሄዶ ሕክምና እንዲያደርግ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞ ከነበረው የአጥንት ሕክምና ባለሙያ አንፃር አሁን ላይ ያለው ምን ዓይነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ብሩክ፡- አሁን ላይ ያሉት የአጥንት ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል፡፡ በቅርቡ ራሱ ከ100 በላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከ13 በላይ ንዑስ ስፔሻላይዝድ ክፍሎች አሉ፡፡ እንዲሁም የሕፃናት የአጥንት ሕክምና ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ከአገራቸውም ተርፈው ወደ ተለያዩ አገሮች በማምራት ግልጋሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማፍራት እየቻልን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹም ብቃት ያላቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉ ባለሙያዎች እያፈሩ ነው፡፡ አንዳንዴ ተማሪዎቹ ካላቸው አቅምና የትምህርት ውጤት አንዱን ከአንዱ ለማስቀረት ራሱ አዳጋች የሚሆንበት ወቅት አለ፡፡ ካሉን የአጥንት ባለሙያዎች አንፃር ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ መሆን እየቻልን ነው፡፡ ስለዚህ ብቁ የሆኑና ቁጥራቸው ወደፊት የበለጠ የሚጨምር ባለሙያዎች ይኖሩናል ማለት ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ታካሚዎች አስፈላጊውን  ሕክምና እና ዕርዳታ ከመስጠት አንፃር እንቅስቃሴያችሁ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ብሩክ፡- እውነት ለመናገር ባለሙያዎች ታካሚዎችን ለመርዳት በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው በአገሪቷ በየቀኑ የሚያጋጥመው የተሽከርካሪ አደጋና ባለሙያዎቹ ምን ዓይነት ዕርዳታ እንደሚሰጡ አንድ ቀን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አድሮ መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ በአጠቃላይ ከ2,500 በላይ ከፍተኛ ቀዶ ሕክምናዎችን ማከናወን ችለናል፡፡ በቀን ከዘጠኝ በላይ ኦፕራሲዮን እናደርጋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡-  የአጥንት ሕክምና ቀድሞ ከነበረው አንፃር ሲታይ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ብሩክ፡- በአጠቃላይ ሕክምና ሲባል በማንኛውም አጋጣሚ የታመመ ሰውን የማዳን ሥራ ነው፡፡ ሁሉም ሰው በተለያዩ በሽታዎች ሕይወቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የሁሉም ሰው በሽታ ተመሳሳይ ነው ማለት አይቻልም፤ የእያንዳንዱ ሰው በሽታ የራሱ የሆነ ባህሪ አለው፡፡ ስለዚህ በባለሙያዎች አስፈላጊው ክትትል ከተደረገለት በኋላና ጉዳዩ በጥልቀት ከታየ በኋላ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ቀደም ብሎ በአጥንት ሕክምና ዙሪያ ባለው የባለሙያ ዕጥረትና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ዕቃ ያለመኖር የተወሰኑ ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲታከሙ ተደርገዋል፡፡ ግን ቀድሞ ከነበረው አሁን ላይ ቁጥሩ በጣም ቀንሷል፡፡ በፊት በዓመት እስከ 115 ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር አምርተው እንዲታከሙ ተደርጓል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የዘንድሮውን ቁጥር ብንመለከት 56 ታካሚ ብቻ ነው የተላከው፡፡ ለዚህም በግማሽ የመቀነሱ ምክንያት  በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረው የአጥንት ሕክምና በሁሉም መሰጠት ስለተጀመረ ነው፡፡ በተጨማሪም ዓለም የደረሰበትን የሕክምና መሣሪያ በአገራችን ማስገባት ስለቻልን እንዲሁም የባለሙያዎች ቁጥር መጨመር ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ እንዲያውም የውጭ አገር ዜጎች በእኛ አገር ሕክምናው እያገኙ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ አገር ሄደው ሕክምና የሚያደርጉ ታካሚዎችን መሉ በሙሉ እናስቀራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ታካሚዎች በኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ስላለው የሕክምና ማሻሻያ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ብሩክ፡- በቅርቡ መንግሥት የሕክምና መሣሪያ አስገብቶልናል፡፡ በፊት አንድ ታካሚ ለአጥንት መገጣጠሚያ እስከ 150 ሺሕ ብር ያወጣ ነበር፡፡ አሁን ግን 67 በመቶ በነፃ እንዲታከም አስችሎታል፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የሕክምና ጣቢያዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ እየታየ ያለው የአጥንት ሕክምና ዕድገት ችግሮችን በአገር ውስጥ በቀላሉ ለመፍታት ያስችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ላይ ታካሚዎች ከሚያጋጥማቸው ድንገተኛ በሽታ አኳያ የገንዘብ ዕጥረት እያጋጠማቸው በየመንገዱ ሕዝቡን ሲማጸኑ ይታያል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ብሩክ፡- ማንኛውም ሰው እንዴትና መቼ በሽታ እንደሚያጋጥመው እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ ችግሩ ሲያጋጥመው ደግሞ ቅድሚያ ሕክምና ማግኘት ይኖርበታል፡፡ አሁን ግን በበሽታው መጎዳቱ ሳይቀር የሚታከምበት ገንዘብ ፍለጋ የሰው ፊት ለመመልከት ይገደዳል፡፡ ስለዚህ በእኛ አገር የጤና ዋስትና መስፋፋት ይኖርበታል፡፡ ከሚገኘው የቀን ገቢ ለጤና ዋስትናው የመቆጠብ ባህልን መልመድ ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች የጤና ዋስትና አላቸው፡፡ በደህና ጊዜ ገንዘብ የመቆጠብ ዘዴ መለመድ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት በሁለቱ አገሮች የተያዘውን...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

‹‹የእኛ ብሔርተኝነት የበሰለና ዴሞክራሲያዊ ነው›› አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...