ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ ሁለንተናዊ ልማት ለማካሄድ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖችን ፈርማለች፡፡ በአገር ውስጥም አካል ጉዳተኛውን ያካተተ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት እንዲኖር አዋጅና ፖሊሲ ወጥቷል፤ መመርያም ተዘጋጅቷል፡፡ አካል ጉዳተኛው በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችሉ ጠቃሚና ወሳኝ ጉዳዮችም በወረቀት ሠፍረዋል፡፡ ምን ያህሉ መሬት ወርደዋል ሲባል ግን፣ ብዙ ችግሮች እንዳሉ በተለይ በመድረክ ተገኝተው ስለአካል ጉዳተኛው ጉዳይ ለመናገር ዕድል ያገኙ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም በእነሱ ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት ጥቂት መሻሻሎች ቢኖሩም የአካል ጉዳተኛው ጉዳይ በተግዳሮቶች የተተበተበ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዜሮ ተሳትፎ ወደ አንድ ያደገ ቢሆንም፣ አካል ጉዳተኛው በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን የተቀመጡ ደንቦች፣ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና መመርያዎች ታች ወርደው በቅጡ እንደማይተገበሩ ይናገራሉ፡፡
አካል ጉዳተኛውን በማካተት ጉዳይ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ችግሮች እንዳሉ ቢነገርም፣ እርምት ተደርጎባቸው የሚታዩ ዘርፎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41፣ የሥራ አዋጁ 377/2003 እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ 515/2007 እና በ2030 ሊሳኩ ይገባሉ በሚባሉት ስምንት ዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የተካተተውን አካል ጉዳተኞችን በሁሉም ዘርፎች የማሳተፍ ግብ ለመተግበርም፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው በጠነከረ መልኩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በየዘርፉ ተካቶ እንዲተገበር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
አካል ጉዳተኞችን በልማቱ ተሳታፊ ለማድረግም ኢትዮጵያ በወረቀት የሠፈሩ በርካታ መልካም ጎኖች አሏት፡፡ ትልቁ ችግር ያለው እነዚህ በወረቀት የሠፈሩ መብቶችን ወደ ተግባር መለወጡ ላይ ነው፡፡
የአካል ጉዳተኞችን ማካተት የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም፣ ኢትዮጵያ በ2030 ሊሳኩ ይገባቸዋል በተባሉ ግቦች ዙሪያ ያጠናቀራችውን ሪፖርት በሐምሌ አጋማሽ በኒውዮርክ በተደረገው የከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ፎረም (High – Level Political Forum (HLPF)) ላይ አቅርባለች፡፡ 43 አገሮች በበጎ ፈቃደኝነት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት መድረክ ኢትዮጵያ ሪፖርቷን ስታቀርብ፣ በላይት ፎር ዘ ወርልድ የአካል ጉዳተኝነት አካቶ ልማት ከፍተኛ አማካሪ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤም ተገኝተው ነበር፡፡
ይህንን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር ለመወያየት ላይት ፎር ዘ ወርልድ ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ የተገኙት ወ/ሮ የትነበርሽ፣ ኢትዮጵያ የተሻለ ለውጥ ያሳየችው በምግብ ዋስትና ረገድና በጤና ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአካል ጉዳተኞች አካቶን በተመለከተ ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም የሚቀር ነገር መኖሩንም አክለዋል፡፡ እንደተግዳሮትና የመረጃ አያያዝ ክፍተትና የአየር ንብረት ጉዳይ ተነስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በበጎ ፈቃደኝነት የ2030ውን ዘላቂ የልማት ግብ ዕውን ለማድረግ ከዚህ ቀደም የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ በፈቃደኝነት ሪፖርት ማቅረቧ፣ የአካል ጉዳተኛው ጉዳይ መነሳቱም መልካም መሆኑንና የለውጥ አመላካች እንደሆነ በመግለጽም፣ መንግሥትና በተለይ አገር ውስጥ በአካል ጉዳተኛ ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት ማኅበረሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ታች ወርደው ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
ድህነትና አካል ጉዳተኝነት አይለያዩም፡፡ በዓለም ከሚገኙ ከአንድ በላይ ቢሊዮን አካል ጉዳተኞችም 80 በመቶ ያህሉ ድሆች ናቸው፡፡ በዘላቂ የልማት ግቦችም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ አካል ጉዳተኞችን ለመድረስ በሁሉም ግቦች ውስጥ ተካቷል፡፡ ግቦቹ በአጠቃላይ ያለሙትም ሁሉንም ሰው ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ታሳቢ በማድረግ እየሠራች መሆኑ ለውጥ ቢሆንም፣ ኒውዮርክ ላይ የቀረበው ሪፖርት በቂ አልነበረም፡፡ ወ/ሮ የትነበርሽም፣ በመርህ ደረጃ አካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሲጠየቅ ተቀባይነት መኖሩን፣ ነገር ግን ተፈጻሚነቱን የሚከታተል ጠንካራ አካል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
መኪና የሚይዝ ጋዜጠኛ በሌሎች ዘርፎችም የሚሳተፍ አካል ጉዳተኛ መኖሩን ሆኖም ያለው ለውጥ በቂ እንዳልሆነ፣ ስለአካል ጉዳተኞች መድረክ ላይ የሚመራው መሬት ወርዶ ካልተተገበረ ዳቦ ሆኖ እንደማያጠግብ፣ የሚወራው ፖሊሲ ለሰዎች ዳቦ እንዲሆን መንግሥት ተጠያቂ፣ ሕዝብ ጠያቂ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
አሁን ያለው አሠራር መካከለኛ ድሃውን እንጂ የድሃ ድሃውን እየደረሰ እንዳልሆነ በመጥቀስ ‹‹ትንሽ ቦታ የያዝን ሰዎች ዋጋ መክፈል ያለብን ይመስኛል፤›› የሚሉት ወ/ሮ የትነበርሽ፣ አካል ጉዳተኞች መብታቸውን እንዲጠይቁ፣ መንግሥት በአዋጅ፣ በፖሊሲ፣ በደንብና በመመርያ ያስቀመጣቸውን ሕጎች የሚያስፈጽሙ አካላት ካልተገበሩት የሕግ ተጠያቂ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ከተሳተፉ የሚዲያ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር፡፡ በአገሪቱ አካል ጉዳተኛውን በሁሉም ዘርፍ አሳታፊ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች ቢኖሩም የጎላ ለውጥ አላመጡም፡፡ ይህ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚለው አንዱ ነበር፡፡ ወ/ሮ የትነበርሽ እንዳሉት፣ ለዚህ ዋና ምክንያቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ በትልልቅ የፖሊሲ መድረኮች የአካል ጉዳተኛው ችግር በበቂ አይነሳም፡፡ ይህም ከሥር ጀምሮ ያሉ ችግሮች መፍትሔ እንዳያገኙ አድርጓል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበሩ መድረኮች የኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ የንግድ ማዕከላት፣ መንገዶች ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለአካል ጉዳተኛው ምቹ እንዳልሆኑ ተነስቷል፡፡ ሆኖም ችግሩ አዲስ በሚሠሩ ግንባታዎች ላይ ሲቀረፍ አይታይም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኛ መወጣጫ ቢኖራቸውም፣ ከፍታ ያላቸው በመሆኑ ለዊልቸር ተጠቃሚዎች አመቺ አይደሉም፡፡ ሊፍቶችም ቢሆኑ ብዙ ቦታ አንድ ዘሎ አንድ ናቸው፡፡ የማይሠሩም አሉ፡፡ የሕንፃ አዋጁ ሕንፃዎች ሲገነቡ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉ ዲዛይን እንዲኖቸው ቢያስቀምጥም፣ ይህ ብዙም ሲተገበር አይታይም፡፡
በየመንገዱ የተቆፈሩ ጉድጓዶችና ሌሎችም ተምሮና ወጣ ብሎ ራሱን ለመቻል የሚለፋውን አካል ጉዳተኛ እየፈተኑት ነው፡፡ በመንግሥት የሚገነቡ ሕንፃዎችም አካል ጉዳተኛውን በቅጡ ያገናዘቡ አይደሉም፡፡ ወ/ሮ የትነበርሽ ይህንን ‹‹የሕንፃ አዋጁን በመጀመርያ የጣሰው መንግሥት ነው፤›› ይሉታል፡፡ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚሄድ አካል ጉዳተኛ ተደራሽ የሆነ ግንባታ ባለመኖሩ እንደሚቸገር በመግለጽም፣ ይህንን ለምን? የሚል ማኅበረሰብ መፈጠር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመጥቀስም ባለዕድሉ አካል ጉዳተኛው ከሆነ የወለል ክፍል አንደሚሰጥ፣ ሆኖም እናት/አባት ባለዕድለኛ ቢሆንና አካል ጉዳተኛው ልጁ ቢሆን፣ የወለል ክፍል እንደማያገኝ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ እናቶች ተከራይተው ለመኖር መገደዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ግልጽ እንዳልሆነ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በ2007 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ ከሕዝቡ 1.17 በመቶ ማለትም 1.17 ሚሊዮን አካል ጉዳተኛ አለ የሚል ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ዓለም ባንክ በ2011 ያወጡት ሪፖርት 17.6 በመቶ ወይም 17.6 ሚሊዮን ይላል፡፡ ይህንን በተመለከተ በመጪው ዓመት የሚካሄደው ሕዝብ ቆጠራ ግልጽ መረጃ እንደሚሰጥ ተስፋ እንዳላቸው፣ አካል ጉዳተኞች በቅጡ ካልተቆጠሩ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ናሽናል ዲስኤቢሊቲ አክሽን ኔትወርክ በተዘጋጀ መድረክም በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛው ቁጥር በግልጽ እንደማይታወቅ ተነግሯል፡፡ አካል ጉዳተኞች የተሻለ ትምህርት ያለማግኘታቸው፣ የሥራ ማስታወቂያዎች ተደራሽ አለመሆን፣ በቀጣሪ በኩል አዎንታዊ ምልከታ እንደሌለም ተገልጿል፡፡
ትምህርቱ ለአካል ጉዳተኛ በበቂ ተደራሽ ባለመሆኑ ቤት የቀሩ፣ ከድህነታቸው ብዛት በየእምነት ተቋማቱ ምፅዋት የሚጠይቁ አካል ጉዳተኞችም በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አገሪቷ አጀብ የተባሉ ፖሊሲዎች ቢኖሯትም አፈጻጸማቸው ላይ ያለው ክፍተት በየመድረኩ የሚነሳ አጀንዳ ነው፡፡