Sunday, June 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕገወጥ ዝውውርን አደብ ማስገዛት የሚቻለው ሕጉን ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ነው

በበላይ ታምሩ

ሰሞኑን መንግሥት ከረጅሙ የተሃድሶ ግምገማ፣ በቅርቡም ከተከታታዩ የአመራር ሥልጠና በኋላ የዕርምጃ በትር ያነሳ መስሏል፡፡ ለዓመታት ሕዝቡ፣ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ዋና ኦዲተርና መሰል አካላት ‹‹ኧረ ምንድነው ነገሩ?››  ሲሉባቸው የቆዩ መሥሪያ ቤቶችና የሥራ ኃላፊዎችን በሙስና ወንጀል መመርመር ጀምሯል፡፡ ጥልቀት ያለውና ቁርጠኝነት የታከለበት ከሆነ ደግሞ ይበል፣ ይጠናከር የሚባል ጅምር ይሆናል፡፡ ይህን ጉዳይ በደንብ ሲብላላና የክስ መዝገቡም ፍርድ ቤት መቅረብ ሲጀምር የምመለስበት ሆኖ፣ ለዛሬው ግን ተሃድሶውም ሆነ መገማገሙ ብዙም

የዳሰሰው ስላልመሰለኝ አንድ አንገብጋቢ ችግር ላወጋችሁ ወደድኩ፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የታዳጊው ዓለም ዋነኛ ችግር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የስደቱ መነሻ የኢኮኖሚ ፍላጎት ማደግ፣ የዓለም ወደ አንድ መንደርነት መቀየርና የትም አገር ገብቶ የመሥራት ፍላጎት መጨመር፣ ወይም የፖለቲካ ነፃነት ማጣትም ይባል መገፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆኖ በአገራችን በሕጋዊ መንገድ ከአገር ወጥቶ ለመሥራት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ በሕገወጥ መንገድ በተገኘው አጋጣሚ የሚፈረጥጠው ዜጋ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሷል፡፡ የተዳፈነ ቢመስልም ሲያገረሽ ታይቷል፡፡ ይህንኑ ፈተና ለመግታት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ የችግሩ ፈቺ ግብረ ኃይል ቢቋቋምም፣ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ስለመምጣቱ ማረጋጋጫ አልተገኘም፡፡

እንዲያውም በአሁኑ ወቅት በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ እየሆነ ያለውን ለሚመረምር ሥር እየሰደዱ ዜጐችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና እንግልት እየዳረጉ ከሚገኙ ወንጀሎች አንዱና ዋናው፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መሆኑን  በቀላሉ ለመገንዝብ አያዳግተውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን፣ በኬንያና  ከእኛም በማይሻሉ አገሮች በርካታ ኢትዮጵዊያን በሕገወጥ መንገድ ስለመኖራቸው ብዙም ሲነገር አይሰማም፡፡ በእኛ አገር ያሉ የጎረቤት አገሮች ስደተኞችን ብዛትና ስብጥር ያህል ማለቴ ነው፡፡

በእርግጥ ሁሉም አገሮች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ነው ብለው ከደመደሙ ከራርመዋል፡፡ ወንጀሉም በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ዝውውርን እጅግ የከፋ የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ያለውና ተያያዥ የሆነው ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል እንደሆነም ታምኖበታል፡፡ ነገር ግን ስደተኞችን በየአገሩ ለማቆየት የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር የተደረገው በቂ ጥረት የለም፡፡ በእኛም አገር ቢሆን በየጊዜው እየሆነ ያለውን (የግብር መጫንና በአገር ውስጥ ሕዝቡ ከአነስተኛ ንግድ እንዲወጣ ማድረግ፣ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳዳር ዕጦት፣ የሙስና መባባስ፣ የፖለቲካው ሁሉን አሳታፊ አለመሆን፣ አለመተማማን …) ለታዘበ ስደትን የሚያስቀር ዕርምጃ ተወስዷል ለማለት አያስደፍርም፡፡

በአገር ደረጃ የሕገወጥ ስደት ከጥቅሙ ይልቅ አስከፊነቱን ደጋግመን ታዝበናል፡፡ ከዜጎች እንግልትና ሞት እስከ አሸባሪ ካራ ድረስ አርፎብናል፡፡ በሴቶችና በሕፃናት ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ በማሻገር ወንጀልም፣ ቁጥራቸው በጣም ብዙ የሚባሉ ዜጐች ተጎድተዋል፡፡ ይህን ወንጀል ለመከላከል ከተለያዩ አገሮች ጋር ተባብሮ  ኃላፊነትን መወጣት የሚያስፈልገውም የችግሩ ዋነኛ ሰለባ ኢትዮጵያ በመሆኗ ነው፡፡ ለወንጀሉ ተጐጂዎች ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ፣ ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸውን፣ ፆታቸውንና ልዩ ፍላጐታቸውን ያገናዘበ የተለየ ጥበቃ እንክብካቤና ድጋፍ ማድረግም ወሳኙ የመንግሥት ኃላፊትነት ሊሆን ይገባል፡፡

ይሁንና በዚህ ረገድ ከተግባር በላይ ወሬው እየጮኸ ብዙ ትዝብት ላይ እየጣለን ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ከሳዑዲ ዓረቢያ ከ135 ሺሕ በላይ ዜጎች በግፍ ተፈናቅለው ወደ አገር ቤት ተመለሱ፡፡ ተቀባይ ኮሚቴ ተቋቋመ፣ የተለያዩ ተቋማት ባለሥልጣናት ተገኙ፣ በየአካባቢው ተደራጁ ተባለ፣… ነገር ግን ከአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ያለፈ ሥራ ባለመሠራቱ፣ አብዛኛዎቹ ተመልሰው ከመሰደድ አልፈው በአገር ቤት የተውተረተሩ ቢኖሩም እምብዛም የተሳካላቸው አልነበሩም፡፡ ከዚሁ ሐሜት ሳይወጣም ይኼው በምንገኝበት ጊዜ ሌሎች በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕገወጥ ስደተኞች፣ ከዚያው አገር በግዳጅ እየተመለሱ ነው፡፡ ግን ለዘለቄታው ምን እየተሠራ ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡  

 የዚህ ጽሑፍ ዓለማ ይበልጡኑ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የወጣው የሕግ አተጋባበርና አስገዳጅነት ላይ ማተኮር ነው፡፡ በመሠረቱ ስደትን ለማስታገስም እንደ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ከሚደረጉ ጥረቶች ባሻገር፣ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችን በቁርጠኝነት ለማስታገስም በወንጀል ሕጉም ሆነ በሌሎች ሕጎች የተቀመጡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ በመሆኑም ከወቅቱና ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ ምላሽ የማይሰጡና ወንጀለኞችን ለጥፋታቸው ተገቢና ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ለመጣል የማያስችሉ ሆነው ሲገኙም በየጊዜው እየታዩ መሻሻል አለባቸው፡፡

ከሁሉ በላይ ግን  ከገጠር ቀበሌዎች እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ ከተሞች የተዘረጋው ሰንሰለትና አንዳንዴም የመንግሥት አካላት ጭምር የሚሳተፉበት አደገኛው መስመር የሚበጠስበት ሕጋዊ ዕርምጃ ሊጠናከር ግድ ይለዋል፡፡ ከቀበሌ መታወቂያ ሰጪው አንስቶ በየኤምባሲና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለሕገወጥ ድለላ ወኪል እስከ ሆነው ጥቅመኛ ድረስ ሊጋለጥ የሚችለው፣ በዚሁ የሕግ ማስፈጸም ጥንካሬ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ አሁን እንደሚታየው ‹ሲሞቅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ› ዓይነት አካሄድ ግን ከአረንቋው ሊያወጣን የሚችል አይደለም፡፡

‹‹ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አለ›› ሲባል ይህንኑ የማዘዋወር ተግባር የሚፈጽም ሕገወጥ አዘዋዋሪ፣ ወይም ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር አሻጋሪ ወንጀለኛ አለ ለማለት  ነው፡፡ ‹‹ሕገወጥ አዘዋዋሪ›› ወይም ‹‹ድንበር አሻጋሪ›› የሚባለው ወንጀለኛ ደግሞ በማንኛውም መንገድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕግን በመጣስ፣ ወይም በራሱ ፈቃድ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የፈጸመ ወይም ለመፈጸም የሞከረ ሰው ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ወንጀል ደግሞ ያለጥርጥር የመንግሥት አካላት ወሳኝ ድጋፍ ሳይኖርበት ሊፈጸም አይችልም፡፡ እውነት ለመናገር በአንዳንድ አገሮች የሚገኙ ቀንደኛ ደላሎች እኮ እስከ ኤምባሲዎች የሚደርስ ኔትወርክ እንዳላቸውም ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደተኞችን ድንበር የማሻገር የወንጀል ድርጊት ላይ በአባሪነት የተሳተፈ ሰው እኩል ወንጀለኛ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች በወንጀል ድርጊቱ እንዲሳተፉ ያደራጀ ወይም በተደራጀ የወንጀል ቡድን ውስጥ አመራር የሰጠ እሱም ወንጀለኛ ነው ከተባለ፣ በድርጊቱ ውስጥ ተሳትፈው የተገኙ አካላት በግምገማ ብቻ ሊታለፉ ባልተገባ ነበር፡፡ በተለይ አሁን መንግሥት በጥልቀት በመታደስ ላይ እገኛለሁ እያለ ባለፉት ጊዜያት እንደ ሥርዓት የፈተኑትን አጀንዳዎች እየመረመረ ባላበት ጊዜ፣ ነገሩ በቸልታ ሊታለፍ አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡

ሰዎችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጀምሮ የተስፋ ቃል በመስጠት ልክ ዶላር እንደ ቅጠል የሚሸመጠጥና እንደ አሸዋ የሚታፈስ እያስመሰለ በሐሰት ወሬ እያነሳሳ ለወንጀል ድርጊቱ ወይም ለስደተኝነት የዳረገ ሰው ወንጀለኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ በማንኛውም መንገድ የወንጀል ድርጊቱ እንዲስፋፋ ያደረገ፣ ወይም የተደራጀ ቡድን ወንጀል ለመፈጸም ማሰቡን እያወቀ ለጋራ ዓላማ በቡድን ለተሰባሰቡ ሰዎች አስተዋጽኦ ያደረገ፣ ሕገወጥ አዘዋዋሪ ወይም ድንበር አሻጋሪ በሚለው ሥር ተፈርጆ በወንጀሉ ተጠያቂ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ ጥቂት ደላሎችን፣ አጓጓዦችንና ደባቂዎችን በመቅጣት ብቻ ሊቆም አይገባውም፡፡ ይልቁንም በመንግሥት መዋቅርም ውስጥ የፌደራልና የክልል ፖሊስ፣ የድንበር ጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ፣ እንደ ኢሚግሬሽንና መሰል ሥፍራዎች ላይ በመሆን ወንጀሉን የሚያሳልጡ ተባባሪዎች ሊመነጠሩ ግድና አስፈላጊ ነው፡፡

እዚህም አገር ያለው አቀባይ እዚያም አገር ያለው ተቀባይ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ እየተቀባበሉ ለብዝበዛ በመዳረጋቸው ከሕግ ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ ‹‹ሰዎችን ለብዝበዛ መዳረግ›› በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ሥር የሚጠቃለሉ በርካታ መገለጫዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሌሎች ሰዎች ዝሙት አዳሪነት መጠቀም ወይም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ወይም የጉልበት ብዝበዛ፣ ወይም የግዳጅ ሥራ ወይም የአገልጋይነት ብዝበዛ አለ፡፡ ባርነት ወይም ባርነት መሰል ተግባር፣ የወሲብ አገልጋይነቱን ጨምሮ ሰውን የማይገባ አገልጋይ ማድረግ፣ ሰውን በመያዣነት መያዝ ወይም አሳልፎ ለሌላ መስጠት፣ ወይም/እና የሰው ልጅን አካል ማውጣት ወይም መውሰድ (Body Parts)፣ ወይም አስገድዶ በልመና ማሰማራት… ሁሉም በሰብዓዊነት ላይ የሚሠሩ የሕገወጥ ዝውውርና የሕገወጥ ድንበር አሻጋሪነት ተግባር አስከፊ የብዝበዛ ውጤቶች ናቸው፡፡

ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ ለብዝበዛ ዓላማ ሲባል በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት፣ ወይም ለሥራ ወይም ለልምምድ ወደ ውጭ አገር በመላክ ሽፋን፣ ወይም የጉዲፈቻ ስምምነት በማድረግና ይህም በዚሁ ሽፋን የተደረገ ከሆነ ወንጀል ነው፡፡ በሌላ በማንኛውም ዓይነት ዓላማ ዛቻን፣ ኃይልን፣ ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም በማገት፣ በመጥለፍ፣ በተንኮል በማታለል ወይም የተስፋ ቃል በመስጠት ከተጠቀመ ወንጀል ነው፡፡

ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት፣ ወይም በመቀበል ሰዎችን የመለመለ፣ ያጓጓዘ፣ ያዘዋወረ፣ ያስጠለለ ወይም የተቀበለ ሰው ወንጀለኛ ነው፡፡ ቅጣቱም ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ250 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጫ እንደሚቀጣ በሕጉ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወንጀል ተጠርጥሮና በመረጃ ተረጋግጦ በሕግ የተጠየቀ ሰው ስለመኖሩ ፍንጭ የለም፡፡ ወይም ወሬ ነጋሪዎች እንኳን ትንፍሽ ብለው አልሰማንም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕገወጥ ስደተኛ በሚናኝበት አገር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሕግና ተግባር ታቅፈን የት ልንደርስ እንችል ይሆን?

በተለይ ደግሞ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው በሕፃናት፣ በሴቶች ወይም በአዕምሮ ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፣ ተጐጂው ለአካላዊ ወይም አዕምሯዊ ጉዳት ከተዳረገ፣ አደንዣዥ ዕፅ ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም ከሆነ፣ በመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ሠራተኛ ከሆነና ወንጀሉን የፈጸመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ከሆነ ወይም በተጐጂው ወላጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ አሳዳጊ ወይም በተጐጂው ላይ ሥልጣን ባለው ሰው ከሆነ ቅጣቱ ከባድ እንደሆነም የሚታወቅ  ነው፡፡ ከ250 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብርና ከ25 ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራት ወይም ዕድሜ ልክ እስራት መቀጮ እንደሚጣልበት ሕጉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በተግባርስ የምንመለከታቸው ብዙ የዜጎች ጉዳቶች በእንዴት ያለ የሕግ ማከሚያ እንዲሽሩ ተደርጎ ነው ቀዳሚው ጥያቄ ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም! ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መደገፍና ማመቻቸት ራሱን የቻለ ከባድ ወንጀል ነው፡፡ ማንኛውም ሰው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የራሱንም ሆነ በይዞታው ሥር ያለን ቤት ሕንፃ ወይም ግቢ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዓላማ ያከራየ ወይም እንዲጠቀሙበት የፈቀደ ሰው ወንጀለኛ ነው፡፡ ሕገወጥ ዝውውርን ለማስፋፋት የተለያዩ የኅትመት ውጤቶችን ያባዛ፣ ያጠራቀመ፣ ያሰራጨ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጭ ያስወጣ ሰው ጥፋተኛ ነው፡፡ ግን በመዲናችንም ሆነ በአንዳንድ የክልል ከተሞች በዚህ አሳፋሪ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሕገወጦች እነማን እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማበረታታት በማሰብ የሥራ ቅጥር ተቋም በማደራጀት ያስተዳደረ፣ የመራ ወይም በገንዘብ የደገፈ፣ እያወቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ያመቻቸ ወይም ተጐጂዎችን በአየር፣ በምድር ወይም በባህር ያጓጓዘ ወይም አገልግሎቱን ያመቻቸ ሰው በሠራው ጥፋት በወንጀል ተጠያቂ ነው፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማመቻቸት ሌላውን ሰው የተጭበረበረ፣ ሐሰተኛ ወይም በሕገወጥ መንገድ መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ እንዲያገኝ የረዳ፣ እንዲዘጋጅ ያደረገ፣ ያቀረበ፣ ይዞ የተገኘ ወይም እነዚህን ሰነዶች ወደ ሐሰት የለወጠ ሰው ወንጀለኛ ነው፡፡ ይህንኑ ዝውውር ለማመቻቸት የሌላውን ሰው የመንቀሳቀስ ነፃነቱን እንዳይጠቀም፣ ወይም ሕዝባዊ አገልግሎቶች እንዳያገኝ ለማድረግ የተጐጂዎችን መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ መያዣ ያደረገ፣ በኃይል የነጠቀ፣ የሰወረ ያጠፋ ወይም እንዲጠፋ ያደረገ ከሆነ ከ15 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራትና ከ250 ሺሕ እስከ 300 ሺሕ ብር በሚደርስ ገንዘብ እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

ሕገወጥ ስደተኞችን የሚመለከት ሕግም አለ፡፡ ለምሳሌ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቆይ ወይም እንዲኖር ለማድረግ የመኖሪያ ፈቃድ፣ መታወቂያ ካርድና ሌሎች የጉዞ ሰነዶች የሚያስፈልግ መሆኑን እያወቀ፣ ወይም ማወቅ ሲገባው ሕገወጥ ስደተኛ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሻገር ድጋፍ የሰጠ፣ ወይም በሕገወጥ መንገድ ድንበር የተሻገረ ስደተኛ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዲቆይ የረዳ ማንኛውም ሰው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ያገኘዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ማለትም ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድኖች የአገሮችን ሰላም ለማናጋት እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ፣ ሕገወጥ የውጭ አገር ሰዎችን መቀበልና መኖሪያ መስጠትና ማስጠለል፣ ያለሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድና መታወቂያ ወረቀት እንዲንቀሳቀሱ ሽፋን መስጠት አደጋው የከፋ መሆኑን ከወዲሁ አውቀን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ለማይረባ ጥቅም አገርን አሳልፎ የመስጠት ያህል በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለንን ግንዛቤ ማጠናከር አለብን፡፡ የማይታወቅ የውጭ አገር ሰው ሲያጋጥመን ወዲያውኑ ለፖሊስ ማሳወቅም ተቀዳሚ ኃላፊነታችን ነው፡፡

 የወንጀል ድርጊቶችን አለማሳወቅ በራሱ ጥፋት ነው፡፡ በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረን ሰው ወይም ወንጀል ሊፈጽም የተዘጋጀን ሰው ለመያዝ፣ ለመክሰስ ወይም ለማስቀጣት የሚያስችል መረጃ ወይም ማስረጃ እያለው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወይም አሳማኝ በሆነ ምክንያት መረጃውን/ማስረጃውን ለፖሊስ ወይም ለሌላ አግባብነት ያለው አካል ወዲያውኑ ያልገለጸ፣ ወይም ሐሰተኛ ማስረጃ የሰጠ ሰው ከአምስት ዓመት የማያንስና ከአሥር አመት የማይበልጥ እስራትና ከአሥር ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡ ይህም ስለሕገወጥ ስደተኞች በወጣው የአዋጅ ድንጋጌዎች በግልጽ ሠፍሮ ይገኛል፡፡

ማንኛውም ሰው ሕገወጥ ዝውውርንና ሕገወጥ የድንበር ማሻገርን ወንጀል በተመለከተ መረጃ ወይም ማስረጃ የማቅረብ ግዴታውን ላለመወጣት ሲል ልዩ መብትን በምክንያትነት መጠቀም አይችልም፡፡ ግዴታውን ባለመወጣቱ ምክንያት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይህ ኃላፊነት በእያንዳንዳችን ላይ አለ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የመንግሥትና የመንግሥት አካላት ዋነኛ ኃላፊነት ነው፡፡

በአጠቃላይ ከዚህ በላይ እንዳየነው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በአሁኑ ጊዜ ከበፊቱ በጣም የተሻለ የሕግ ማዕቀፍ አለን፡፡ ፈተናው ግን ከመተግበሩ ላይ ነው፡፡ በመሠረቱ ጥሩ አዋጅ ማውጣቱ ብቻ ዘላቂ መፍትሔም አይደለም፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀቱ በራሱ ታላቅ ሥራ መሆኑ ባይካድም፡፡ ዋናው ነገር ግን ይህን  የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ ወደ መሬት ሲወርድ የሚያስገኘው የአፈጻጸም ውጤት ነው፡፡      

ሕጉ ምን ውጤት አስገኘ? ብለን አዋጁን ለማስፈጸም ሥልጣን የተሰጣቸውን ተቋማት መጠየቅ መብታችን ነው፡፡ እነሱም ቢሆን በአዋጁ መሠረት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ምን ያህል እንደተንቀሳቀሱ ራሳቸውን መገምገም አለባቸው፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ሕጉ ምን ያህል ጉልበት ሆናቸው? ስንት የነበረው ሕገወጥ ዝውውር አሁን ስንት ደረሰ? አዋጁን በመፈጸም ረገድ ጥንካሬና ድክመታችን ምን ላይ ነበር? ወደፊት ያሉት መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ከእስካሁኑ አሠራር ምን ትምህርት ተገኘ?… ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለብን፡፡

በእርግጥ አዋጁ ገና አዲስ ቢሆንም ሕገወጥ ስደተኛው እየበዛ ሲገፈተር በምን እንመልሰው ብሎ ከመጨነቅ መታሰብ ያለበት ሕገወጥ መጓጓዙ በሕግ እንዴት ይገታ የሚለው ነውና በአጽንኦት መታየት አለበት፡፡ ሕዝብን ከመከራ አገርንም ከውርደት ማዳን የሚቻለው በዚሁ መንገድ ማሰብ ሲቻል ነውና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles