እባብን መዝገበ ቃላቱ እግር አልባ መሬተ በል፣ በምድር የሚሳብ የሚጐተት የሚሰልክ በደረቱ የሚሄድ፣ የሚዘል የሚወረወር መርዘኛ አውሬ የሰው ጥንተ ጠላት ሲል ይፈታዋል፡፡ በተረትና ምሳሌ ውስጥ በየዐውዱ ይጠቀሳል፡፡ እባብን ልቡን አይቶ እግር ነሣው፣ እባብ ግደል ከነበትሩ ገደል፣ እባብ ያየ ልጥ ቢያይ በረየ፣ እባብ ለባብ ይተያያል በካብ፡፡ ክፉ ተንኮለኛ ሰው፣ ነገረ መርዝ ለማለትም እባብ ይጠቀስበታል፡፡ ‹‹እከሌ እባብ ነው መሔጃው አይታወቅም›› እንዲሉ፡፡
እባቦች እግር ስለሌላቸው በደረታቸው እየተሳቡ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መፋተግ የሚፈጠር በመሆኑ ይህንኑ መቋቋም የሚችል ጠንካራ ቆዳ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶቹ የእባብ ዝርያዎች ሸካራ ቅርፊት ባለው የዛፍ ግንድ ላይ ይወጣሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ቆዳን በሚፈትግ አሸዋ ውስጥ ሰርስረው ይገባሉ። የእባብ ቆዳ ይህን ያህል ጠንካራ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? ሲል የሚጠይቀውና ምላሹንም የሚሰጠው ንቁ! መጽሔት ነው፡፡
በጄደብሊው ዶት ኦርግ ድረ ገጽ እንደተገለጸው፣ የእባብ ቆዳ ውፍረቱም ሆነ አሠራሩ ከአንዱ ዝርያ ወደ ሌላው ሊለያይ ይችላል። ይሁን እንጂ የሁሉም የእባብ ዝርያዎች ቆዳ አንድ የጋራ ባሕርይ አለው፤ ውጩ ድርቅ ያለ ሲሆን ወደ ውስጥ እየገባ ሲሄድ ለስላሳ ይሆናል። ይህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ማሪ ክርስቲን ክላይን የተባሉ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል፦ ‹‹ውጫቸው ድርቅ ያለ ሆኖ ውስጣቸው እየለሰለሱ የሚሄዱ ነገሮች፣ የሚወጋ ወይም የሚጫን ነገር ሲያጋጥማቸው ግፊቱ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲሰበጣጠር ማድረግ ይችላሉ።››
በልዩ መንገድ የተሠራው የእባብ ቆዳ፣ ሰውነቱ መሬቱን በደንብ እንዲቆነጥጥ በማድረግ እንደ ልብ እንዲንቀሳቀስ ያስችለዋል፤ እንዲሁም እንደ ሹል ድንጋይ ያሉ ነገሮች ሰውነቱ ላይ የሚያደርሱት ግፊት እንዲበተን በማድረግ ቆዳው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ይከላከላል። እባቦች ቆዳቸውን የሚቀይሩት በየሁለት ወይም በየሦስት ወር በመሆኑ ጠንካራ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው።
ከእባብ ቆዳ ጋር የሚመሳሰል ባሕርይ ያላቸው ነገሮች በሕክምናው መስክ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፣ የማይንሸራተቱና ልዩ ጥንካሬ ያላቸው ሰው ሠራሽ አካሎችን ለመሥራት ያገለግላሉ። በተጨማሪም የእባብ ቆዳን ንድፍ በመኮረጅ የሚሠሩ ባለቺንግያ የዕቃ ማጓጓዣ ኮንቬየሮች የሚፈልጉት ማለስለሻ ቅባት አነስተኛ ነው፤ ይህ ደግሞ እነዚህ ቅባቶች የሚያስከትሉት ብክለት እንዲቀንስ ያደርጋል።