ከአንድ ሳምንት በላይ ሲካሄድ የቆየው የለንደኑ 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ (ነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም.) ይጠናቀቃል፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዓርብ ምሽት (ነሐሴ 5 ቀን) ድረስ በነበራት ደረጃ በ1 ወርቅና 2 ብር አምስተኛውን ስፍራ ይዛለች፡፡ ብቸኛው ወርቅ የተገኘው በአልማዝ አያና በ10 ሺሕ ሜትር ሲሆን፣ ብሮቹን ጥሩነሽ ዲባባ በተመሳሳይ ርቀት፣ እንዲሁም ታምራት ቶላ በማራቶን አስገኝተዋል፡፡ አስቀድመን ማተሚያ ቤት በመግባታችን የቅዳሜውን የወንዶች 5 ሸሕ ሜትር ፍጻሜ ውጤት ለመያዝ አልቻልንም፡፡ በማጣሪያው ሦስቱ ተወዳዳሪዎች ዮሚፍ ቀጀልቻና ሙክታር እድሪስ 1ኛ እና 3ኛ ሆነው፣ እንዲሁም በሌላኛው ምድብ የተወዳደረው ሰለሞን ባረጋ 1ኛ ሆኖ በማሸነፍ ለፍጻሜው መብቃታቸው ይታወሳል፡፡
የሴቶች 5 ሺሕ ሜትር ሩጫ
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1975 ዓ.ም. ሲጀመር ከተካሄዱት ውድድሮች አንዱ የወንዶች 5 ሺሕ ሜትር ሲሆን፣ የሴቶቹ ግን የተጀመረው 12 ዓመት ቆይቶ ነው፡፡
በ1987 ዓ.ም. ጉተንበርግ ባስተናገደችው ሻምፒዮና ቀዳሚዋ አሸናፊ የአየርላንዷ ሶኒያ ኦ ሱሊቫን ነበረች፡፡ ተከታዮቹን ሁለት ቦታዎች የፖርቱጋሏ ፈርናንዳ ቤርዮና የሞሮኮዋ ዛህራ አዚዝ አሸንፈዋል፡፡
በተከታታይ በአቴንስ፣ ሲቪላና ኤድመንተን በተካሄዱት ሻምፒዮናዎች የውድድሩ ባለድሎች አውሮፓውያን ነበሩ፡፡ በ1991 ዓ.ም. በሲቬላ፣ በ1993 ዓ.ም. ኤድመንተን በተካሄዱት ውድድሮች ኢትዮጵያ በአየለች ወርቁ አማካይነት ሁለት ነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡
ኢትዮጵያ በነሐስ ላይ የተወሰነው ድሏ የተለወጠው ውድድሩ በተጀመረ በስምንተኛው ዓመት፣ ሴንት ዴንስ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ ስትከሰት ነው፡፡ በወቅቱ ያጠለቀችው ወርቅ፣ በ1997 ዓ.ም. ሔልሲንኪ ላይ ደግመዋለች፡፡ የሔልሲንኪው ውድድር ኢትዮጵያውያቱ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርና እጅጋየሁ ዲባባ ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ሦስቱንም ሜዳሊያዎች አጥልቀዋል፡፡
በ1999 ዓ.ም. ኦሳካ ላይ መሠረት ደፋር ድሉን ስትቀጥል፣ በሁለተኛነት የገባችው ኬንያዊቷ ቪቪያን ቺሪዮት ከሁለት ዓመት በኋላ በበርሊን በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር ድሉን ስትጨብጥ መሠረትም ነሐሱን አግኝታለች፡፡ በ2003 ዓ.ም. የዳጉ ዓለም ሻምፒዮኗ ቺሪዮትና መሠረት ተገናኝተው እንደ ቅደም ተከተላቸው ወርቁንና ነሐሱን ተቀዳጅተዋል፡፡
የሞስኮው የ2005 ውድድር ድል የመሠረት ነበር፡፡ ኬንያዊቷ ሜርሲ ቼሮኖ ጣልቃ ስትግባ፣ አዲሷ አትሌት አልማዝ አያና ነሐሱን ይዛለች፡፡ ሃቻምና በቤጂንግ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪና ገንዘቤ ዲበባ ተከታትለው በመግባት ኢትዮጵያን ያለጣልቃ ለሁለተኛ ጊዜ ባለድል አድርገዋታል፡፡
በዘንድሮው የለንደን ሻምፒዮና አልማዝ አያና፣ ለተሰንበት ግደይና ሰንበሬ ተፈሪ የፍጻሜው ተፎካካሪ ይሆናሉ፡፡
በሃያ ዓመት ውስጥ ከተካሄዱበት 11 ውድድሮች ኢትዮጵያ 5 ወርቅ፣ 2 ብር፣ 4 ነሐስ በድምሩ 14 ሜዳሊያዎች በማግኘት ቁንጮች ላይ ትገለኛለች፡፡ ኬንያና ሮማንያ ሁለት ሁለት ወርቅ አግኝተዋል፡፡