Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበባህር ዳር የንግድ መደብሮችና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ለሁለት ቀናት ተቋርጠው ነበር

በባህር ዳር የንግድ መደብሮችና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ለሁለት ቀናት ተቋርጠው ነበር

ቀን:

  • ቦምብ በማፈንዳት የተጠረጠሩ ተይዘዋል

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በሦስተኛ ቀኑ የአማራ ክልል መቀመጫ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት የንግድ መደብሮችና የትራንስፖርት አገልግሎቶች በከፊል ተቋርጠው ዋሉ፡፡ አገልግሎቶቹ የተቋረጡት ባለፈው ዓመት በዕለቱ ሕይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች መታሰቢያ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የባህር ዳር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ ዋና ዋና በሚባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የንግድ ተቋማት በከፊል ዝግ ሆነው ውለዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በአብዛኛው መቋረጣቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በማግሥቱም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች መስተዋላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ ይህ ክስተት መፈጠሩ እንዳሳዘናቸው የገለጹት አቶ በሰላም፣ ከእሑድ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት እናደርሳለን የሚሉ  መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተለቀው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

 ሰፈረ ሰላም ተብሎ በሚጠራው ክፍለ ከተማ ውስጥ ባሉ የንግድ ተቋማት ማለትም በአዴትና በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙት እንደ ጣና ሐይቅና ዓባይ ያሉ የገበያ ማዕከላት ችግሩ ጎልቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የንግድ መደብሮችን የመዝጋትና የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠው እስከ ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንደ ዘለቀ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የመደብሮች መዘጋት መነሻ የሟቾች መታሰቢያ እንደሆነ ቢገለጽም፣ አቶ በሰላም ግን ትክክለኛ ምክንያቱ አልታወቀም ብለዋል፡፡

 የከተማው አስተዳደርም ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በተዘጉ የተወሰኑ መደብሮችን ማሸጉን ነጋዴዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ የክልሉ መንግሥት መደብሮችን መዝጋት በመተው፣ ከንግዱ ማኅበረሰብና ከታክሲ ባለንብረቶች ጋር ውይይት ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በኋላ ከማክሰኞ ጀምሮ በአንፃራዊነት ውስን የንግድ መደብሮችና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባህር ዳር ከተማ ዘጠኝ ክፍላተ ከተሞች፣ ሦስት ክላስተር ከተሞችና ዘጠኝ የገጠር ከተሞች ሲኖሯት፣ ሥራ ማቆሙ በአብዛኛው በዘጠኙ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ እንደተከሰተ አቶ በሰላም  ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እሑድ ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት በባህር ዳር ከተማ የቦምብ ፍንዳታም ነበር፡፡ የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኛው ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከምሽቱ 3፡25 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ፖሊ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቦምብ ፈንድቷል፡፡ የቦምብ ፍንዳታውን አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አክለዋል፡፡ በፍንዳታው ተሳትፈዋል የተባሉ ሦስት ዋነኛ ተጠርጣሪዎችና ሁለት ግብረ አበሮች የተባሉ ከነተሽከርካሪያቸው መያዛቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተወረወረው ቦምብ ዝም ብሎ በከተማዋ ቦምብ ጣልን ለማለት ያህል ነው እንጂ፣ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ያነጣጠረ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ቀድሞውንም መረጃ ነበረን፡፡ የቦምብ ፍንዳታው ከተከሰተበት በቅርብ ርቀት የእኛ የፀጥታ ኃይሎች ስለነበሩ ተጠርጣሪዎች በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለዋል፤›› ስሉ ኮማንደር ዋለልኝ ተናግረዋል፡፡

ለአሥር ወራት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. መነሳቱ ይታወሳል፡፡ አስቸኳይ አዋጁ እንዲነሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሳብ ያቀረቡት የአገር መከላከያ ሚኒስትርና የአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ‹‹በአንዳንድ በውል የሚታወቁ አካባቢዎች የቀሩ አነስተኛ ሥራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የሕግ አግባብ መቆጣጠር ይቻላል፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ እነዚህ አንዳንድ አካባቢዎች የተባሉትን እንዲጠቅሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠይቀዋቸው የነበረ ቢሆንም መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ክልል ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...