- አንድ የሥራ ተቋራጭ ባለቤትም ተካተዋል
ከሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር መዋል የጀመሩና በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች ቁጥር 53 ደረሰ፡፡ በመንግሥት ላይ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ሦስት የመንግሥት ኃላፊዎችና አንድ ባለሀብት፣ ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡
ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሕዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ በስኳር ኮርፖሬሽን የመስኖና ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታና ሀዚ አይ አይ ደረጃ አንድ ጠቅላላ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ዛኪር መሐመድ ናቸው፡፡
የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ምን ያህል በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡
አቶ ዓለማየሁ ጉጆ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያዘረጋውን ቴክኖሎጂ መመርያንና ደንብን መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣት ሲገባቸው፣ ለማይታወቅና በቂ ልምድ ለሌለው ድርጅት በመስጠት ከ2.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም መከፈል ያልነበረበትን 280,000 ብር ሲፒኦ በማሠራት ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ ሥልጣናቸውን በመጠቀም፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራታቸውንም አክሏል፡፡ በፍርድ ቤቱ ያቀረበው የምርመራ ሒደት መነሻ እንጂ ሙሉ ምርመራ አለማድረጉን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ለቀሪ የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፣ በተጠረጠሩበት ጉዳይ የተደራጀ መረጃ በመሥሪያ ቤቱ ይገኛል፡፡ በእሳቸው ግምት እስከተያዙበት ባለው ጊዜ ውስጥ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን እያጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፣ ታስረው የሚገኙበት ክፍል ውስጥ 20 ሰዎች በመኖራቸው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡ የስኳራቸው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ አሥጊ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከተያዙ ቀን ጀምሮ ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ማንንም ሰው ማግኘት ባለመቻላቸው፣ በቂና አስተማማኝ ዋስ ጠርተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ለተለያዩ ተቋራጮች የተሰጡ አምስት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዲዛይኖችን በማሠራት፣ የኮንትራት ጊዜያቸውን ባለመጥቀስ፣ የግንባታ ጊዜ በማራዘምና ከኮንትራክተሮች ጋር በመመሳጠር በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናትን ጠይቋል፡፡
አቶ ዛይድ በጠበቃቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ የገለጸው በሰነድ የሚታይ በመሆኑ የጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢ አይደለም፡፡ አቶ ዛይድ ባለሥልጣኑን ከለቀቁ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸውና መንግሥት ከአገር ውጭ ለሥራ መድቧቸው እየሠሩ መሆናቸውን ጠበቃው አስረድተዋል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽኑ አቶ ኪሮስ ደስታ ደግሞ የመስኖና ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ ለጣና በለስ ፕሮጀክት ቧንቧ ግዥ በጨረታ ከቀረበው ዋጋ በላይ ለሦስት ጊዜያት 2,983,396 ብር፣ 131,554,000 ብር እና 49,559,992 ብር ግዢ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ድርጅት 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት በመስጠት በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
አቶ ኪሮስ በሰጡት ምላሽ ድርጅቱን ከለቀቁ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸው ተናግረዋል፡፡ ከቤታቸውም ሆነ ከመሥሪያ ቤቱ ሁሉም ዶክመንቶች የተወሰዱ መሆኑን በመግለጽ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ አይደለም ሲሉም ተቃውመዋል፡፡
ልጃቸው ዩኒቨርሲቲ ስለምትገባ በስልክ አግኝተው እንዲያነጋግሯት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው በታሰሩት እነ ካሣይ ካቻ መዝገብ የተካተቱት የሀዚ አይ አይ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ዛኪር መሐመድ ግምቱ 3,315,200 ብር የሆነ 500 በርሜል አስፋልት በውሰት ወስደው አለመመለሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አቶ ዛኪር በሁለት ወራት ውስጥ ለመመለስ የተዋሱትን አስፋልት፣ ከኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሳይመልሱ መቅረታቸውንና ከላይ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ያህል ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡
አቶ ዛኪር በሰጡት ምላሽ መርማሪ ቡድኑ የገለጸውን ዕዳ መክፈላቸውን ገልጸው፣ ተጨማሪ 14 ቀናት ሊፈቀድ አይገባም ብለዋል፡፡ የዋስትና መብታቸውም እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ አቶ ዛኪር ቀደም ብለው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ጋር ነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ በማለት የአሥር ቀናት ጊዜ ፈቅዷል፡፡ በአቶ ዓለማየሁ፣ በአቶ ኪሮስና በአቶ ዛይድ ላይ የቀረበውን የ14 ቀናት ጊዜ በመፍቀድ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቤተሰብ፣ በሕግ ባለሙያና በሃይማኖት አባት የመጎብኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የፌዴራል ፖሊስ ትዕዛዙን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡ ሕክምናን በሚመለከትም ከመንግሥት የሕክምና ቦታዎች በተጨማሪ፣ የሚፈልጉትን ሕክምና እንዲያገኙም እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡