አቶ ሐሰን ከድር፣ በጃፓን ኮቤ ከተማ የአፍሪካ ኮቤ አገናኝ ባለሙያ
ሐሰን ከድር እድሪስ ይባላሉ፡፡ ከወንዶ ገነት ዩኒቨርሲቲ በናቹራል ሪሶርስ ማኔጅመንት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያገለገሉ ሲሆን በቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር በአፈርና ውኃ ጥበቃ ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ ጃፓኗ ሰባተኛ ግዙፍ ከተማና ዓለም አቀፍ የባህር ትራንስፖርት መናኸሪያ ኮቤ በማቅናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የኮቤ ከተማ መስተዳድር ከተማዋንና ኩባንያዎችን ከአፍሪካ አገሮች ጋር የማስተሳሰር ከፍተኛ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ተቀጥረዋል፡፡ ዮሐንስ አንበርብር በቅርቡ በጃፓን የተለያዩ ከተሞች ባደረገው የሥራ ጉብኝት ወቅት ከኢትዮጵያዊው ባለሙያ አቶ ሐሰን ከድር ጋር በኮቤ ከተማ ከንቲባ ስለተሰጣቸው ተልዕኮ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በኮቤ ከተማ መስተዳደር የተሰጡት የሥራ ተልዕኮ ምንድነው?
አቶ ሐሰን፡- በአሁኑ ወቅት የጃፓን መንግሥት ለአፍሪካ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ የጃፓን ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ እንዲገቡ በስፋት ይፈለጋል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም የተለያዩ የፖሊሲ መሣሪያዎች በአገሪቱ መንግሥት ተቀርጿል፡፡ የኮቤ ከተማ አስተዳደርም በከተማዋ የሚገኙ ኩባንያዎች ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲያተኩሩ እያበረታታ ይገኛል፡፡ የኔ ኃላፊነትም ይህንን የመስተዳደሩ ጥረት መደገፍ ነው፡፡ የጃፓን ኩባንያዎች የቆየ ልማድ አላቸው፡፡ ይኸውም ከአገራቸው ወጥተው በንግድ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ቀልባቸው ስለተሳበበት አገር አጠቃላይ ሁኔታ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አዝማሚያዎች አጥንተው ስለምቹነቱ እርግጠኛ ሲሆኑ ነው የሚገቡት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመረጡት አገር ውስጥ ያሉ አገር በቀል ኩባንያዎችን አቅም በመመዘን ከእነሱ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ እርግጠኛ ካልሆኑ በስተቀር አንድ ዕርምጃ አይራመዱም ነበር፡፡ ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ አሁን መቀየር እንዳለበት አምነዋል፡፡ ቢሆንም መጠነኛ ዕውቀት እንዲኖራቸው አሁንም ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም የኮቤ ከተማ ኩባንያዋች ከተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ጋር መጣጣም የሚችሉ የአፍሪካ ኩባንያዎችን በማጥናትና በመመዘን ለኮቤ ከተማ ኩባንያዎች መረጃ ማቅረብና ማበረታታት ነው ዋነኛ የሥራ ኃላፊነቴ፡፡
ሪፖርተር፡- የሥራ ኃላፊነቶን ከወሰዱ ጀምሮ ያደረጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎ ምን ይመስላል? በየትኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነው ቅድሚያ ትኩረት የሰጣችሁት?
አቶ ሐሰን፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የኮቤ አፍሪካ ሊያዘን ኦፊሰር ሆኜ እየሠራሁ ነው፡፡ ሥራውን የጀመርኩት በዚህ ዓመት ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው፡፡ የሥራ ኃላፊነቴ አህጉር አቀፍ ወሰን ያለው ሲሆን የኮቤ ከተማ ኩባንያዎችን በሚሰጠኝ አቅጣጫ ወሠረት ከአፍሪካ ኩባንያዎች ጋር ጥምረት መመሥረት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የአፍሪካ አገሮችን ዕምቅ አቅም በመገምገም ለኮቤ ከተማ ኩባንያዎች መረጃ ማቅረብና ወደ አፍሪካ እንዲገቡ ማበረታታት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የሚያስቀምጠው አቅጣጫ ይኖራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተስማሚ ሆኖ ቅድሚያ የተሰጠው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአፍሪካ አገሮች ኩባንያዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የኮቤ ኩባንያዎችን ወደ አፍሪካ እንዲገቡ ማበረታታት ነው፡፡ በግብርናና የትምህርት ዘርፎችም እየሠራን ነው፡፡ ቅድሚያ በተሰጠው የአይሲቲ ዘርፍ ባደረግነው እንቅስቃሴ የሩዋንዳ ኩባንያዎችን የተሻለ አቅም በመለየት የኮቤ ኩባንያዎችን ወደ ሩዋንዳ እንዲገቡ ያደረግነው ጥረትም ውጤት እየታየበት ነው፡፡ በኮቤ ከተማ የሚገኙ ኩባንያዎች በዚህ በአይሲቲ ዘርፍ ላይ በስፋት ይሠራሉ፡፡ በጃፓንና በአፍሪካ መካከል ያለውን ርቀት በዚህ ዘርፍ በመስበር መቀራረብን መፍጠር የሚቻል በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩም ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የሩዋንዳ መንግሥት ፖሊሲ ትልቅ ትኩረት ለአይሲቲ የሰጠ ሆኖ መገኘቱና በርካታ የሩዋንዳ ኩባንያዎችም በዚህ ዘርፍ በመንቀሳቀስ ላይ ሆነው መገኘታቸው ቅድሚያ ዕድሉን እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ ሩዋንዳ እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ የፈጠረባትን የግንኙነት መሰናከል በአይሲቲ ዘርፍ ለመቅረፍ እየሠራች ከመሆኑም ባሻገር የመጪው ጊዜ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የጀርባ አጥንት አድርጋ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኮቤ ከተማ ኩባንያዎችም ከፍተኛ ፍላጎትን አሳይተዋል፡፡ በእስካሁኑ ጥረት ብቻ ሁለት የኮቤ ከተማ ኩባንያዎች ወደ ሩዋንዳ በመግባት ከሩዋንዳ ኩባንያዎች ጋር ጥምረትን ፈጥረዋል፡፡ ሩዋንዳ በተራራማ መልክዓ ምድር ላይ የምትገኝ በተደጋጋሚ በመብረቅ የምትመታ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ይህንን ችግር በአይሲቲ ለመቅረፍ በመንቀሳቀስና አፕሊኬሽኖችን በማልማት ለኢኮኖሚ ገበያው ማቅረብን ትኩረት አድርገዋል፡፡ በኮቤና በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማም በቅርቡ የትብብር ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ጃፓኖች ለቴክኖሎጂ ቅድሚያ ይሰጣሉ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች መሪ አንቀሳቃሹ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በሰው ኃይል ቅጥር ላይ ብዙ ትኩረት አያደርጉም፡፡ በጥቂት ባለሙያዎች ነው ሥራዎቻቸውን የሚመሩት፡፡ በመሆኑም ሩዋንዳ ለአይሲቲ ትኩረት የሰጠች አገር መሆኗ ቀዳሚ ምርጫቸው ሆናለች፡፡ ጥቂት ባለሙያዎቻቸውን ሩዋንዳ ላይ በማድረግ ሥራዎችን ለሩዋንዳ የጥምረት ኩባንያዋቻቸው በሰብ ኮንትራት በመስጠትና በሩዋንዳ ያለውን ፍላጎት በማጤን ለመሥራት የሚመቻቸው በመሆኑ በዚህ መንገድ ለመንቀሳቀስ ሩዋንዳን በአሁኑ ወቅት መርጠዋል፡፡ ይህንን ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማስፋፋት ሌላው አቅጣጫ ነው፡፡ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ በጃፓን የሚታወቁት አይሲቲ ኩባንያዎች አቶዋ ዳንኪ እና ዋየርድ ኢን በሩዋንዳ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ አይሲቲ ዘርፍ የኢትዮጵያ ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ ያሉ ሁኔታዎች በጃፓን ኩባንያዎች ተመራጭ የመሆን አቅም አላቸው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሐሰን፡- በአይሲቲ ዘርፍ ኢትዮጵያ በስፋት ባትንቀሳቀስም ጅምር መሣሪያዎችና ፍላጎቶች እንዳሉ እገነዘባለሁ፡፡ ትልቅ ክህሎትና ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ብቅ እያሉ ነው፡፡ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለአይሲቲ ዘርፍ ትልቅ ገበያ መፍጠር እንደሚችልም ይታወቃል፡፡ የጊዜ ሁኔታ እንጂ ኢትዮጵያ በአይሲቲ ዘርፍ ዕምቅ የሆነ የቢዝነስ ዕድልና ገበያ እንዳላት ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንጂነሮች እየተመረተባት ያለች አገር በመሆኗ አቅም አላት፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንደዚህ ዓይነት ዕድል እንዳያመልጣቸው ምን ይመክራሉ?
አቶ ሐሰን፡- ቀደም ብዬ እንዳልኩት የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት በራሱ ትልቅ የገበያ ዕድል ነው፡፡ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንጂነሮች የሚመረቱበት አገር ነው፡፡ በሩዋንዳ እንዳየሁት ከሆነ አዲስ ምሩቆች የራሳቸውን ትንሽ ቢዝነስ አቋቁመው የውጭ ኩባንያዎችን መሳብ ችለዋል፡፡ የራስህ የሆነ ትንሽ አቅም የውጭ ኩባንያን እንዴት መሳብ እንደሚያስችል በተግባር ተመልክቻለሁ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም እንደዚህ ዓይነት ተሞክሮዎች ቢለመዱ እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ እንዲሁም የማርኬቲንግ ሥራና ራስን ማስተዋወቅ ላይ ብዙ መሠራት ይጠይቃል፡፡ ምን ያህል አቅም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ እያስተዋወቅን አይደለም፡፡ እኛ ስለራሳችን በተናገርነው ልክ ነው ሰዎች የሚቀበሉን፤ ስለዚህ በዚህ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ዌብሳይቶችን አልምቶ መሥራት ብቻ በቂ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ የኮቤ ከተማ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በአይሲቲ ዘርፍ መግባት የሚችሉበት አቅም አለ?
አቶ ሐሰን፡- በትክክል፡፡ በተለይ መንግሥት እያቋቋመ ነው የተባለው የአይሲቲ መንደር ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል፡፡