- የሦስቱ የመንግሥት ፋይናንስ ድርጅቶች ሀብት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል
የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ የሚከታተላቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የ2009 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸም በማስመልከት በጠራው መግለጫ፣ በተለይ የልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን 25 በመቶ መድረሱን ይፋ አደረገ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት፣ የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር፣ ከጠቅላላው ብድርና ቅድሚያ ክፍያ አንፃር ወደ 9.2 በመቶ ለማውረድ ቢያቅድም ወደ 25 በመቶ አሻቅቧል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ለማበደር ካቀደው 14 ቢሊዮን ብር ውስጥ 5.4 ቢሊዮን ብር ገደማ በማበደር ከዕቅዱ የ37 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ሊሰበሰብ ያቀደው ገንዘብ ቦንድን ጨምሮ ስድስት ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ የ4.56 ቢሊዮን ብር አፈጻጸም ማከናወኑ ታውቋል፡፡ በአንፃሩ በብድር ክምችት ረገድ በቦንድ የሰጠውን ጨምሮ ከ42.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ 33.8 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ዋና ዳይሬክተሩ በሪፖርታቸው አስረድተዋል፡፡ ምንም እንኳ ሊሰበስብ ካቀደው ብድር ውስጥ 79.6 በመቶውን ቢሰበስብም በብድር አሰጣጥ፣ ብድር በማስመለስ፣ በውጭ ምንዛሪ ግንኝት፣ በቦንድ ሽያጭ ብሎም በትርፋማነቱ ላይ ዝቅተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
አጄንሲው ባንኩ ስላስመዘገበው አነስተኛ አፈጻጸም በርካታ ምክንቶችን ጠቃቅሷል፡፡ ብድር የሚሰጣቸው ደንበኞች ማዋጣት የሚገባቸውን የብድር ድርሻ (ኢኪዩቲ ሼር) ገቢ ባለማድረጋቸው፣ በአገሪቱ በተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ባንኩ ብድር የሰጣቸው ፕሮጀክቶች በወቅቱ ሥራ ባለመጀመራቸውና ሥራ ጀምረውም ጉዳት የደረሰባቸው በመኖራቸው፣ ለእርሻ መሬቶች ተደራራቢ ብድር በመስጠቱ ሳቢያ፣ እንዲህ ባሉ ፕሮጀክቶች ብድር መስጠት መታገዱ፣ የባንኩ ደንበኞች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ጥሬ ዕቃ ከውጭ ለማስገባት ባለመቻላቸው፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የሊዝ ፋይናንስ መዘግየት ከሚጠቀሱት በርካታ ችግሮች መካከል ይመደባሉ፡፡
ትልልቅ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ አለመሆናቸው፣ ለውጭ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው ብድር በ70/30 ድርሻ (70 በመቶ የመንግሥት ብድር 30 በመቶ የራስ መዋጮ) በአሁኑ ወቅት ወደ 50/50 ድርሻ እንዲስተካከል መደረጉም ከችግሮቹ መካከል ተመድበዋል፡፡ ይህ ሁሉ ተዳምሮ ለልማት ባንክ ዝቅተኛ አፈጻጸም ብሎም ለተበላሸ ብድር መጠኑ አስተዋጽኦ ማድረጉን የኤጀንሲው ሪፖርት አመላክቷል፡፡
ይሁንና በሦስቱም የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት የ2009 ሒሳብ ዓመት ክንውን መሠረት የ523 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት መመዝገቡን ሲገለጽ፣ ከታቀደው የ517 ቢሊዮን ብር አኳያ ከ100 በመቶ በላይ ጭማሪ መመዝገቡን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ አምና ከነበረው የ440.4 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት አኳያ የ82.6 በመቶ ጭማሪ ተመዝግቧል ብሏል፡፡ ከጠቅላላ ሀብት ውስጥ በጥሬ ገንዘብ የተመዘገበው 60 ቢሊዮን ብር ገደማ መድረሱም ታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በብድር መልክ የተመዘገበው ሀብት 184 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በኢንቨስትመንት መልክ ከ269 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡
ሦስቱ ተቋማት በዓመቱ ያስመዘገቡት አጠቃላይ የዕዳ መጠን 490 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አምና የነበራቸው የዕዳ መጠን 415 ቢሊዮን ብር እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መሠረትም የፋይናንስ ተቋማቱ ካፒታል መጠባበቂያ ክምችታቸውን ጨምሮ 33 ቢሊዮን ብር መመዝገቡን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
በብድር ሥርጭት ረገድ ድርጅቶቹ 124 ቢሊዮን ብር ብድር (የብድር ቦንድ ኩፖን ታክሎበት) ማሠራጨታቸው ሲገለጽ፣ አብዛኛው ድርሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ባንኩ 94.5 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱ፣ 54 ቢሊዮን ብር ገደማ ብድር መሰብሰቡንና የብድር ክምችቱም በቦንድ የሰጠውን ጨምሮ 420 ቢሊዮን ብር ገደማ ማድረሱ ታውቋል፡፡ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከጠቅላላው ብድር ውስጥ 2.8 በመቶ መሆኑ ሲገለጽ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአስምት በመቶ የተበላሹ ብድሮች ጣሪያ አኳያ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ ከዚህም በላይ 14.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን፣ ከአምናው መጠንም የ5.2 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡