ዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ካሌብ ፓርክ ለሠፈሩ ነዋሪዎች እንደ መዝናኛ ቦታ ያገለግላል፡፡ በልዩ ልዩ ዕፀዋት የተሞላው ፓርክ ውስጥ ከዕረፍት ቀናት በተጨማሪ በሥራ ቀናት የምሳ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉበትም አሉ፡፡ በግልም ሆነ በቡድን የፓርኩን ፀጥታ ፈልገው ወደ ካሌብ የመመልከት አማራጭ የተፈጠረላቸው በቅርቡ ነው፡፡
ካሌብ ፓርክ ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ከወትሮው የተለየ አገልግሎት መስጠት የጀመረበት ዕለት ነው፡፡ ፓርኩን የሚያዘወትሩ ሰዎች የፓርኩን መግቢያ በር እንዳለፉ ለወትሮው ባዷቸውን በሚያዩዋቸው ዛፎች ላይ ሥዕልና ፎቶግራፍ ተሰቅሎ ይመለከታሉ፡፡ ከፓርኩ ተፈጥሯዊ አቀማመጦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ኦፕን ኤር ጋለሪ (ከቤት ውጪ በማንኛውም ክፍት ቦታ የሚገኝ ጋለሪ) የተከፈተው ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ነበር፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ከአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በተመረቀው ተስፋዓለም ሸዋንግዛው የተመሠረተው ጋለሪ፣ ሆፕ ጋለሪ ይባላል፡፡ ጋለሪው በይፋ መከፈቱን ለማብሰር የተዘጋጀው መርሐ ግብር የሥዕልና የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ያካተተ ነበር፡፡ ፓርኩ መግቢያ ላይ ከዐውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች የሆነው ዳሪክ በላቸው ሥራዎች ይገኛሉ፡፡
የዳሪክ ሥራዎች የአብዛኛውን የአገሪቱን ማኅበረሰብ የዘወትር ሕይወት የሚያስቃኙ ናቸው፡፡ በአካባቢያችን በቀላሉ ልናገኛቸው ከምንችላቸው እንደ ፕላስቲክ፣ አፈርና የልብስ ቅዳጅ ያሉት ግብዓቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ በመንደሮች ውስጥ ያለውን ሕይወት የሚያንፀባርቁት ሥራዎች፣ በሰፌድ ላይ የተሰጣ እንጀራ፣ አርጅተው የተጠገኑ ቤቶችና የተሰጣ ልብስም ያሳያሉ፡፡ ከከተሞች ፈጣን ለውጥ ጋር በተያያዘ ቀስ በቀስ እየተለወጠ የሚገኘውን የአኗኗር ዘዬ የሚያስታውሱ ናቸው፡፡
በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዛፎችና ድንጋዮችን ተከትለው የተደረደሩት የተቀሩት ሥራዎች የተለያዩ ይዞታ ያላቸው ናቸው፡፡ በዐውደ ርዕዩ የተሳተፉት አብዛኞቹ አርቲስቶች በቅርብ ጊዜ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች የተመረቁ ሲሆነ፣ ሥዕልና ፎቶግራፍን በማዋሃድ ምልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኦፕን ኤር ጋለሪው የተከፈተው በክረምት ወቅት በመሆኑ ሥራዎቹን ከዝናብ ለመከላከል ድንኳን ተጥሎ ነበር፡፡ ክረምት ሲገባደድ ግን ድንኳኖቹ ተነስተው የሥነ ጥበብ ሥራዎቹ በፓርኩ በአጠቃላይ እንደሚታዩ አዘጋጆቹ ገልጸውልናል፡፡
አሁን አገልግሎት እየሰጠ ባይሆንም ፈረንሣይ ፓርክ ውስጥ ይገኝ የነበረው ነፃ አርት ቪሌጅ ይታወሳል፡፡ አርቲስቶች ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት፣ ስለሥነ ጥበብ የሚወያዩበት እንዲሁም ማንኛውም ጥበባዊ ክንውን የሚያካሂዱበት ቦታ ነበር፡፡ በአገሪቱ ያሉት ጋለሪዎች በቤት የሚገኙ እንደመሆናቸው ክፍት ቦታን እንደ አማራጭ የሚያቀርቡም ያስፈልጋሉ፡፡ ቦታዎቹ አርቲስቶች እየተገናኙ ሐሳብ የሚለዋወጡባቸውና ሥነ ጥበብ ነክ መርሐ ግብሮች የሚስተናገዱባቸው መሆንም ይችላሉ፡፡
ከቤት ውጭ የሚገኙ ተፈጥሯዊ አካባቢዎች መንፈስ የሚያድሱ እንደመሆናቸው፣ ሥነ ጥበብ ሲታከልባቸው ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ጠቀሜታ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይም አገሪቱ በበርካታ ሕንፃዎች እየተሞላች ከመምጣቷ አንፃር፣ የብዙዎች የሥራ ቦታና መኖሪያም ፎቅ ላይ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ቦታዎችን ማግኘት ሲፈለግም ብዙም ኪሎ ሜትሮች አቆራርጦ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ከተማው ውስጥ የሚገኙ ፓርኮች ኅብረተሰቡን የሚስቡና ብዙዎች ጊዜያቸውን ለማሳለፍ የሚመርጧቸው ማድረግ የሚያሻውም ለዚህ ነው፡፡
ተስፋዓለም ከአለ ከወጣ በኋላ ሰዎች ሥነ ጥበብን የሚያደንቁበት ተፈጥሯዊ ቦታ አለመኖሩንና አርቲስቱም በነፃነት የሚሠራበት ቦታ ውስን መሆኑ ያሳስበው ነበር፡፡ የዲዛይን ምሩቁ ተስፋዓለም፣ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ መሥሪያ ቦታ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ ቦታው ጠባብ በመሆኑ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ እንደሱ ሁሉ ከአለና ከሌሎችም የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ አርቲስቶች ተመሳሳይ ፈተና እንደሚገጥማቸው በመገንዘብም መፍትሔ ያፈላልግ ጀመር፡፡
‹‹ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ መሥሪያ ቦታ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ሥራዎቼ ጋለሪ ውስጥ እንዲታዩ ሳስገባም የራሱ ውጣ ውረድ ነበረው፤›› ይላል፡፡ አማራጭ ቦታዎችና በሚፈልግበት ወቅት የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ በአዲስ አበባ ፅዳትና ውበት መናፈሻ ሥር የሚገኘውን ካሌብ ፓርክ አገኘ፡፡ ለክፍለ ከተማው ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት በማግኘቱም ሥራውን ጀመረ፡፡ የመጀመሪያ ዓላማው ወጣት ሠዓሊያንና ፎቶ አንሺዎች በማንኛውም ጊዜ ሊገለገሉበት የሚችሉ ቦታ መፍጠር መሆኑን ይናገራል፡፡
ከአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤትና ከተፈሪ መኰንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተመረቁ ፎቶ አንሺዎችና አሥር ሠዓሊያንን አሰባስቦ የጋለሪው መክፈቻ ዐውደ ርዕይ እንዲያሳዩ አደረገ፡፡ በቀጣይ በየሁለት ሳምንቱ የአርቲስቶች የውይይት መድረክና በየሦስት ወሩ ዐውደ ርዕይ እንደሚካሄድም ይገልጻል፡፡ ከጋለሪው አጠገብ በሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የሚታከሙ ሕሙማን እንደ ማገገሚያ ሥዕል እንዲሥሉ የመጋበዝ ዕቅድም አለው፡፡
‹‹ሥዕሎቹና ፎቶግራፎቹ በየዛፉ ተሰቅለው ሰው ነፃ ሆኖ መመልከት ይችላል፡፡ ለሠዓሊያንም ምቹ የሥራ ቦታ ይሆናል፤›› ይላል፡፡ ጋለሪው ከሥነ ጥበብ ባለሙያዎች በተጨማሪ በፓርኩ አካባቢ ያሉና በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦች በትርፍ ጊዜያቸው ስለ ሥነ ጥበብ ያላቸውን ዕውቀት ለማዳበር የሚጠቀሙበት ነው፡፡ በተለያየ ሙያ ውስጥ የሚገኙ ሆኖም የሥነ ጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ወደ ፓርኩ እየሄዱ ሥዕል መሣል መጀመራቸውንም ተስፋዓለም ይናገራል፡፡
‹‹ጋለሪው ለአለ፣ ለተፈሪ መኰንን፣ ለኢንላይመትና ለአቢሲኒያ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች ቅርብ ስለሆነም ተማሪዎችም መጥተው መሥራት ይችላሉ፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ጋለሪው አቅራቢያ እንደ ሐበሻ ስቱዲዮ ያሉ የሥነ ጥበብ ስቱዲዮዎች መኖራቸው አካባቢውን የሥነ ጥበብ ማዕከል እንደሚያደርገው ያምናል፡፡ ከሥነ ጥበቡ ጎን ለጎን የሥነ ጽሑፍና የሙዚቃ መርሐ ግብሮች በፓርኩ የማካሄድ ዕቅዳቸውንም ያክላል፡፡
ክፍት የሕዝብ ቦታዎችን ለማግኘት አዳጋች ከመሆኑ አንፃር ካሌብ ፓርክን እንዲጠቀም ፈቃድ በማግኘቱ መደሰቱን የሚገልጸው ተስፋዓለም፣ ‹‹ቦታው የኔ ብቻ ሳይሆን የጋራ ስለሆነ ሁሉም ሰው በነፃነት መጥቶ ሊጠቀምበት ይችላል፤›› ይላል፡፡
በጋለሪው መክፈቻ ዐውደ ርዕዩ በሴቶችና ሕፃናት ላይ ያተኮሩ ሥዕሎችን ለዕይታ ያበቃ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚኖሩ ዐውደ ርዕዮች ይዘት በመምረጥ ወጣት አርቲስቶች በስፋት የሚሳተፉበት እንደሚሆን ይናገራል፡፡ ‹‹የሴቶችና የልጆች ውበት ይማርከኛል፤›› የሚለው የጋለሪው መሥራች ሆፕ ኦፕን ኤር ጋለሪ በተጨማሪ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በአጠቃላይ ማዕከል እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋል፡፡
ሥራቸውን በጋለሪው መክፈቻ ካቀረቡት አንዱ የሆነው ዳሪክ በላቸው፣ ለመጀመሪያ ዙር የመረጠው በፈጣን ለውጥ ተፅዕኖ እያደረበት የሚገኘውን የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ኑሮ ማሳየት ነው፡፡ ‹‹የምጠቀመው ዘወትር የምንገለገልባቸውን ግብዓቶች ነው፡፡ ለምሳሌ አፈርን እንደ ቀለም እጠቀማለሁ፡፡ አስመስሎ ከመሥራት የዛገውን ቆርቆሮ ራሱን እጠቀማለሁ፤›› ይላል፡፡
ሥራዎቹን በኦፕን ኤር ጋለሪ ማቅረብ አስደሳች መሆኑን የሚናገረው ዳሪክ፣ በየትኛውም ቦታ ሥነ ጥበብ ማሳየት እንደሚቻል ማሳያ ነው ይላል፡፡ ተማሪዎች ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተመርቀው ከወጡ በኋላ መሥሪያና ሥራዎቻቸውን ማሳያ ቦታም ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጾ፣ አማራጮች ሊሰፉላቸው እንደሚገባ ያክላል፡፡ ዳሪክ ከአለ ከተመረቀ በኋላ የመመረቂያ ዐውደ ርዕይ በትምህርት ቤቱና ለአንጋፋው የሥነ ጥበብ ሰው አለ ፈለገሰላም መታሰቢያ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ ዐውደ ርዕይ አሳይቷል፡፡
‹‹በሥነ ጥበቡ አገሪቷ ውስጥ ካሉ ፈታኝ ነገሮች አንዱ ቦታ ነው፡፡ በፊት ነፃ አርት ቪሌጅ ነበር፡፡ አሁን አዲስ መኖሩ ጥሩ ነው፤›› ይላል፡፡ ሥነ ጥበብን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ማኅበረሰቡ በሚያዘወትራቸው ቦታዎች ማሳየት የተሻለ መሆኑም ያክላል፡፡ ባለሙያው ከማኅበረሰቡ ጋር የሚገናኝበትና ሐሳብ የሚለዋወጥበት እንዲሁም ለጥበብ ሥራዎች የሚያነሳሳ ቦታ እንደሚሆንም እምነቱ ነው፡፡