የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2009 ዓ.ም. 48 የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች መልቀቁን አስታወቀ፡፡ ከተለቀቁት መካከል አሥራ አራቱ በሌሎች የምርምር ተቋማት የተሠሩ ናቸው፡፡ ከተለቀቁት መካከል ሁለት የቴምር፣ ሁለት የፓልማርዝ ዝርያዎች እንደሚገኙበትና ሲለቀቁም ይህ የመጀመሪያ መሆኑ ታውቋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ምርምር የተደረገባቸው 33 ገና ያልተለቀቁ የሰብል ዝርያዎችም አሉ፡፡
በኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክተሩ እሸቱ ደርሶ (ዶ/ር) ‹‹ምርምሩ የሚደረገው በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ነው፡፡ በነበረው አለመረጋጋትና ድርቅ የተቀሩትን 33 የሰብል ዝርያዎች መልቀቅ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡
የወጡት ዝርያዎች ለምግብና ሥነ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ለአገሪቱ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሏል፡፡ ከ10 እስከ 20 በመቶ የምርት ብልጫ እንዳላቸው፣ ተባይና በሽታን እንዲሁም ዝናብ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች የሚሆኑ ሰብሎች እንደሆኑ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ (ዶ/ር) የተቋሙን የ2009 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ባቀረቡበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡
በሰብል ብዛትና አቅርቦት ረገድ በ33 ሰብሎችና ከ200 በላይ የሰብል ዝርያዎች 11,861.6 ኩንታል የሰብል ዘርና 102,125 የሰብል ችግኝ ቁርጥራጭ ለማብዛት ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የተሳካው 10525.8 ኩንታል የሰብል ዘርና 101,875 የሰብል ችግኝ ቁርጥራጭ ማብዛት ነው፡፡
በተመሳሳይ በእንስሳት ምርምር መስክ 1,300,655 የተለያዩ እንስሳት፣ 465,000 የሰብል የችግኝ ቁርጥራጭና 209 ኩንታል የእንስሳት መኖ ዘር አባዝቶ ለማሠራጨት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማሳካት የቻለው 890,918 የተለያዩ እንስሳት፣ 467,500 የእንስሳት መኖ ቁርጥራጭና 88.15 ኩንታል የእንስሳት መኖ ዘር ማቅረብ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በግብርና ሜካናይዜሽን ምርምር ዘርፍ እንዲሁ 626 የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎች ማባዛት (በስፋት እንዲሠሩ ማድረግ) ተችሏል፡፡ 7,500 ፓኬት ህያው የጥራጥሬ ማዳበሪያ፣ 5.63 ኩንታል የቀልዝ ትል በበጀት ዓመቱ በመሬትና ውኃ ሀብት ምርምር የቀረቡ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍም እንዲሁ፣ በበጀት ዓመቱ 500,000 የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች፣ በቲሹ ካልቸር፣ የተሻሻሉ ጥጆችን በሲንክሮናይዜሽንና በፅንስ ዝውውር እንዲሁም ተፈላጊውን ፆታ ለማግኘት በሚቻልበት የአሠራር ዘዴ ለማስወለድና ለማባዛት ተይዞ የነበረው ዕቅድም 75 ከመቶ መሳካቱን በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
እንደ ዶክተር ድሪባ ገለጻ፣ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አርብቶ አደር ምርምር ተቋማት ጋር በትብብር የተሠሩ ሥራዎችም አሉ፡፡ ተቋማቱ በመቀናጀት ለአካባቢው ተስማሚ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ፣ የማስተዋወቅና የዘር ብዜት ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል፡፡ በ153 ሔክታር ቦታ ላይ በተለያዩ የመኖ ዝርያዎች፣ በምግብ ዋስትና ሰብሎች፣ በፍራፍሬ በአትክልትና በሥራሥር ሰብሎች ውጤታማ የሆነ የማላመድና የማስተዋወቅ፣ እንዲሁም የመነሻ ዘር ብዜት ተከናውኗል፡፡
የተቋሙን ተደራሽነትና ልማቱን ለማገዝ በኩራዝ፣ በተንዳሆ፣ በበለስ ስኳር እርሻዎች እንዲሁም ተደራሽ ባልነበሩ በደቡብ ኦሞና በአፋር አርቶ አደር አካባቢዎች 9434.2 ኪሎ ግራም ሰብሎችና የተለያዩ ዝርያዎችን ማሠራጨት መቻሉን፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ መኖ፣ አኩሪ አተርና ለውዝ በመዝራት የማላመድ ተግባር እንደተከናወነ፣ ለተጨማሪ ሥራም 38 ኩንታል የማሽላ ዘር ለደቡብ ኦሞ ዞን መሠራጨቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹ኢንስቲትዩታችን በዋና ዋና ሰብሎች፣ በእንስሳት እርባታና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድ ውጤታማ የሆኑ የተጠቃሚውን የኑሮ ደረጃ መለወጥ የቻሉ የምርምር ውጤቶችን ለማቅረብ ችሏል፤›› ያሉት ዶክተር ድሪባ ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት የበቆሎ ምርት በምርምር ጣቢያው በሔክታር 130 ኩንታል የደረሰ ሲሆን፣ በአርሶ አደሩ ማሳ ደግሞ በአማካይ በሔክታር 34.3 ኩንታል ነው፡፡ የስንዴ ሰብልን በተመለከተም የዋግ በሽታ ተቋቋሚ ዝርያዎችን በማቅረብ የስንዴን ምርታማነት በምርምር ጣቢያው በሔክታር 80 ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ደግሞ በሔክታር እየተመረተ ያለው በአማካይ 24 ኩንታል ነው፡፡ የጤፍ ሰብልን በምርምር ለማሻሻል በተደረጉ ሥራዎችም እንደ ቁንጮና ኮራ ያሉ የጤፍ ዝርያዎችን በማቅረብ በአርሶ አደሩ ደረጃ በአካማይ በሔክታር 15.8 የነበረውን በምርምር ተቋሙ በሔክታር 35 ኩንታል ለማድረስ ተችሏል፡፡
የአንቀጭራ ችግርን የሚቋቋሙ፣ ፈጥነው የሚደርሱ፣ የማሽላ ዝያዎችን በማቅረብ የማሽላ ምርት እንዲስፋፋና ምርታማነቱ በአርሶ አደሩ ማሳ በአማካይ በሔክታር 23.7 ኩንታል የነበረውን በምርምር ጣቢያ በሔክታር 60 ኩንታል እንዲደርስ ማድረግ ተችሏል፡፡
በሌሎች የሰብል ዓይነቶችም በተለይ የቦለቄ፣ የተሻሻሉ የሰሊጥ ዝርያዎች፣ የቅመማ ቅመም ዝርያዎችን በማቅረብ ለውጭ ምንዛሪ ዕድገት የማይናቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ዶ/ር ድሪባ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በምግብ ዋስትናና ድህነት ቅነሳ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ልማትና በውጭ ንግድ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት የሚያስችል ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ‹‹የግብርና ምርቶች የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፋዊ ሁኔታዎችን ተከትለው የሚከሰቱ ልማቱ በየደረጃቸው የሚፈልጋቸውን አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን በዓይነት በብዛትና በተከታታይ ማቅረብ የኢንስቲትዩታችን ቀጣይ ሥራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከተቋቋመ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአገሪቱ ግብርና ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ እስካሁን 1,115 የሰብል ዝርያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የተለቀቁ ሲሆን 801 የሚሆኑት ከተቋሙ የተገኙ ናቸው፡፡ ምርታማነትን መጨመር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና በሽታን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ማቅረብና ሌሎችም ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል፡፡
‹‹ዝርያ የመልቀቅ ግቡ ምርታማነትን መጨመር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሀብት ክምችት መጨመር፣ የአርሶ አደሩንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ኑሮ ማሻሻል ነው፤›› የሚሉት ዶክተር እሸቱ በግብርናው ዘርፍ ያሉትን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ የበኩሉን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ግብርና መር በሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርት በግብርና የሚገኘው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ አገሪቱ ከምታገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪም 86 በመቶ የሚሆነው ከግብርናው ዘርፍ የሚገኝ ነው፡፡ የአመዛኙ ኢትዮጵያዊ ኑሮ የተመሠረተውም በዚሁ ግብርና ላይ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን የግብርና ዘርፍ ማዘመንና በምርምርና በሳይንስ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ለኢኮኖሚው ዕድገት ወሳኝ መሆኑም አያጠያይቅም፡፡
በአገሪቱ በተበታተነ መልኩም ቢሆን ከ1920ዎቹ ጀምሮ ነበር የግብርና ምርምር እንቅስቃሴዎች የተጀመሩት፡፡ በ1940ዎቹ በቀድሞው በአለማያ እርሻ ኮሌጅ፣ በጅማ እርሻ ኮሌጅ፣ በአምቦ እርሻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት፣ በ1950ዎቹ ደግሞ በግብርና ሚኒስቴር ሥር ግብርና ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይቶ የካቲት 18 ቀን 1958 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ራሱን ችሎ ተቋቋመ፡፡ ከተቋቋመ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ኢንስቲትዩቱ እስካሁን የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ለማኅበረሰቡ አቅርቧል፡፡ እያቀረበም ይገኛል፡፡