Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አስመሳይ ሲወራጭ አድርባይ ያጅበዋል!

ሰላም! ሰላም! ሰሞኑን መርካቶ እግር አበዛሁና የምሠራው ሳጣ ጥያቄ ፈጠርኩ። ሥራ ፈጠራ ከብዷላ። ለአንዳንድ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎቼ መልስ የማገኝበት መንገድ በአብዛኛው አስገራሚ ሆኖ አገኘዋለሁ። ለምሳሌ መርካቶ አካባቢ መሄድ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የማያቸው ፍየሎች (በተለይ የእርጉዝ ፍየሎች አበዛዝ)…፣”የማን ይሆኑ? ምን ውስጥ ያሳድሩዋቸዋል?” እና “መሀል ከተማ ፌስታልና ጫት የሚበላ ፍየል ለዕርድ ይሆን የሚያረቡት?” የሚሉ ጥያቄዎች ይመላለሱብኝ ነበር። የ”ሊሆን ይችላል” መልሱን ግን ፍፁም በማልጠብቀው ቦታ የባሻዬ ልጅ አዙሮ አዙሮ አመጣው። አንድ ስለሳዑዲ ዓረቢያ የጻፈ ጸሐፊ ነው አለኝና በታላቋ የነዳጅ መናኸሪያ ሳዑዲ በርከት ያሉ ፍየሎች ዓይቶ ‘እረኛቸው ወዴት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅ አሉ ‘እረኛ የላቸውም። ሥራ ግን አላቸው። ሥራቸውም የሳዑዲን ቆሻሻ እያመነዠኩ መዋጥ ነው። ሳይታሰብ ይሁን ታስቦበት የሚሠራበት ቆሻሻ አወጋገድ ዘዴ ነው’ አለው አለኝ አንድ አልፎ ሂያጅ።

ይኼን እያሰብኩ የፀጋዬ ገብረ መድኅንን መርካቶና የጥንት ነዋሪዎቿ ዓረቦች፣ አርመናውያን፣ ግሪካውያንና ህንዶች አሰብኩ። ቆሻሻቸውን እንዲያነሱላቸው ዓረቦች እንደ ፅዳት ሠራተኛ ያረቧቸው የነበሩ ፍየሎች የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ፣ ልጆች ናቸው ማለት ነው? ብዬ ራሴን ጠየኩ። ‹ሥራ የለህም እንዴ አንተ?› ከማለታችሁ በፊት መጀመርያ የሥራ ማቆም አድማን አስቁሙ። እኔ ስለፍየልና ፍየላውያን ማሰቤን እስከዚያው እቀጥላለሁ። ታዲያ ለእኔ ስሜት ስለሰጠኝ ነው ይህንን ያህል ያልኩት። መፍትሔ ማመንጨትም እኮ ራሱን የቻለ ‹ኃይድሮ ፓወር› ነው። እግረ መንገዴንም ለአዲስ አበቤ ቅጥ የለሽ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትና መጣያ ሥፍራ ውዝግብ፣ በዛ ያሉ ፍየሎችን ማሰማራት ቢታሰብበት ምን ይመስላችኋል? ለማለት ነው። ሐሳቡ ተቀባይነት ካገኘ የፍየል ባለቤቶች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር… አራት ኪሎ ቅርንጫፍ በኩል ኮሚሽኔን ማስገባት እንዳትረሱ።

ስለቆሻሻና አወጋገዱ ካነሳን አይቀር ብዙ ነገር አለ። የቆሻሻ መገለጫ መንገዶች ስንት ናቸው? ሲባል ‹ሦስት› የሁሉም መልስ ነው። ደረቅ፣ ፈሳሽና ጋዝ። አስተሳሰብ የሚቆሽሽ የማይመስላቸው ብዙ አሉ። የዋህ ብላችሁ ትምሩዋቸዋላችሁ። ወይም በቆራጦች ዓይነት ዕርምጃ ዝቃጭና ቆሻሻ አስተሳሰብ ላይ በተመሠረተ የግል ጥቅም አጋባሽነት ላይ ዘመቻ ከፍታችሁ ታስተምራላችሁ። ምርጫው የእናንተ ነው። ግን ግን ‹አንድም መሞት ነው አንድም መኖር ነው› የሚዘፈነው አሁን መሆን አለበት። አይመስላችሁም? የዘንድሮ ሰውና የዘመኑ መስተዋት ግን አልግባባ ብሏል። ነውርን እንደ ክብር መቁጠር ስለበዛ ነው መሰል መስታወት ፊት ቆሞ ውሎ ነውሩን ሳይሸፍን እያቅራራ ከቤት ይወጣል። ምነው ስትሉት መልሱ ‹ፋሽን› ነው።

‹‹ያራባናቸው ፍልፈሎች ቤታችንን ሲንዱብን አቤት ባይ፣ ማርገጃ ሥፍራ ያጣን ሆንን፤›› ይላሉ ባሻዬ ስለቆሻሻና ቆሻሻ አስተሳሰብ ተሸክመው ስለሚያሸክሙን ሃይ ባይ አጣሾች ሲያነሱ። ታዲያ ሰሞኑን ባሻዬ ደስተኛ መስለው መታየት ጀምረዋል። “እውነት ያረገዋል እሱ መድኃኔዓለም፤” እያሉ ቴሌቭዥን ላይ አፍጠው ይውላሉ። ይኼ ›ጥልቅ ተሃድሶ› መንፈሳቸውን ‹ያደሰው› ይመስላል። ‹እውነት ከሆነ› የሚለው ሳይረሳ። ምን ማለቴ ነው? በቃ ማለት የፈለግኩትን ለማለት ማለቴ ነው። በዚህ የቅኔ አገር ማለት ምን ማለቴ ነው እየተባለ ወሬ የሰለቸው ካለ ‹እውነቴን ነው ስልሽ እውነት እንዳይመስልሽ፣ ውሸት እንዳይመስልሽ› ያለውን ገጣሚ ያፈላልገው። ለ . . . ለማለት ነው!

እውነት እንደ እኛ የታደለ ሕዝብ ይኖር ይሆን? ኤድያ፣ ‹ኢትዮጵያ ቀደምት ምድር› የሚባለው አዲስ መለያ የተካውን የጥንቱን ‹የ13 ወር ፀጋ› ልታነሳ ባልሆነ እንዳትሉኝ አደራ። ‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል› በተከበረበት አገር እንኳን እኛ ወራቱም ከተፋረሱ እኮ ቆዩ። በመፍረስ መፈራረስ ዘመናችን ሲያልቅ አንዴ ቆመን ሽቅብ፣ አንዴ ተቀምጠን ቁልቁል ዕድሜን ሸኘነው። አናሳዝንም በናታችሁ? አዎ! ምናልባት ባትሰሙ ነው እንጂ ማየቱንስ እያያችሁ ነው። ጠቁመን ካለችሁኝ ከወራት የአየር ፀባይ መፈራረቅ ይልቅ እያንዳንዱ ቀን የራሱን የመሰለውን አየር ሲያናፍስብን የምንውለውን መጠቆም በቂ ነው። ተግባባን መሰለኝ? ዘመኑ የ’ግሎበላይዜሽን ነው!’ ቢባልም የፅንፈኛው ብዛትና የተገንጣዩ ቁጥር እያደር በረከተ።

“ጊዜው ሁሉም ራሱን አጉልቶ ለማሳየት የሚሯሯጥበት የመሆኑ ጉዳይ እጅግ እየተለጠጠ መጣ። አገር የሚባል ድባብ የማይዋጥላቸው ወገኖች በጎሳ ተደራጅተው ስለጎሳ መብት ብቻ ተሟጋች ሆኑ። ሰውነት፣ ሰው መሆን፣ አንድ አምሳል ተረሳ። በሰውነታችን ብቻ የሚጨነቀው ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን አልቀረም አሁንስ?” የሚሉት ባሻዬ፣ ለመጪው ፍልሰታ ፆም ከሚፀልዩባቸው ዓብይ አጀንዳዎች መካከል መፋረስን አንዱ አድርገውት ሰንብተዋል። ‘ከአገር ዓለም ትሰፋለች’ ብለው ለትልቅነት የበቁትን ማስታወስ ለምን ከበደን? የታላቁ እስክንድርን ህልም፣ የናፖሊዩንን ራዕይ፣ የታላቁ ጴጥሮስን ብልኃት አላድለን ያለው እንዲያው ይኼን ያህል ምን ቢጎድለን ነው?” የሚለው ደግሞ የባሻዬ ልጅ ነው። በየጉራንጉሩ በየአደባባዩ አገርን ዓይተን አገርን ባሰብን ቁጥር ስንጫወት። ‘የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ዛሬ፣ ተቃጥሏል መሰለኝ ሸተተኝ አገሬ!” ያሉት ባለቅኔ ትዝ አሉኝ። የራሳችን ስንትና ስንት የሚጠቀሱ ዘመን አይሽሬ አርበኞች፣ ጸሐፍት፣ ለዛቸው የማይጠገብ ሰዎች አልነበሩን እህህህ……

የእኔ ነገር ሁሌ ከእናንተ ጋር ጨዋታዬ ብሶት ነው። ለነገሩ እንኳን ክፉና ደግ ለይተው እንዲሁም ከእናት ሆድ ስንወጣ በለቅሶ ድብልቅልቁን አይደል የምናወጣው? ብሶት በአስተዳደር ከመማረር በፊት ይኼውላችሁ እዚያ ይጀምራል። በቀደም ታዲያ አንድ አራስ ልጠይቅ ከማንጠግቦሽ ጋር ፊትና ኋላ ሆነን እንጓዛለን። እሷ ፊት እኔ ኋላ። “ኧረ ሰው ምን ይለናል? መሀል ከተማ እየኖርን እንደ ጨለማው ዘመን እየነዳሁሽ ስጓዝ? ተይ ቀስ በይ እኩል እንራመድ?” ስላት አትሰማም። ይኼ ‘ሌዲስ ፈርስት’ ያላፈላው ጉድ የለም። እኔማ አንዳንዴ ሳስበው ቴክኒኩን ቀይሮ ቀስ እያለ ወደ ኋላ እየጎተተን ሳይሆን አይቀርም። እናንተስ አትታዘቡም እንዴ? የዴሞክራሲ እሴቶች ብለን ስንፎክር መብትን ደመቅ መከባበርን ደብዘዝ አድርገን መጻፍ ካላቆምን እንጃልን!

እናላችሁ የትጥቅ ታጋዮች መስለን ማንጠግቦሽና እኔ ሱክ ሱክ ስንል ባዶ እጃችንን መሆናችን ታወቀኝ። “ማንጠግቦሽ! ከእዚች ሱቅ አበባ ነገር እንግዛ እንጂ ባዶ እጃችንን ሰው ቤት እንዴት ይኬዳል?” ብላት፣ “አበባ ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ይጥቀም እንጂ ለአራስ ምን ይጠቅማል? ካልክ ስንት ነገር አለ?” አለች ኮስተር ብላ። ‘ስንት ነገር’ን እና ኮስተር አባባሏን አልወደድኩትም። “በይ ተይው እኔ ባዶ እጅ ከመንጦልጦል ይሻላል አልኩ እንጂ፣ ለ‘ቤቢ ሻወር’ ገንዘብ የለኝም። ለራሴ በወጪ ሻወር ተራቁቻለሁ፤” ብዬ ፍርጥም አልኩ። እኔስ ማን ነኝ ታዲያ?! ቆይ ግን፣ የአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ እንደተካተተ ሁሉ አራስ ደግፈን፣ ዕቁብ ጥለን፣ ዕድር አዋጥተን፣ ዓባይ ላይ ዝተን ምን ሊቀረን ነው? ግራ ገባን እኮ ሰዎች!

በሉ እንሰነባበት። በሁለት ሐሳብ እያነከስን እንዴት ልንዘልቀው ይሆን ስል ነበር ባሻዬን እያየሁ። ሰሞኑን ተጠርጥረው ከተመነጠሩት የመንግሥት ኃላፊዎች አንዱ የባሻዬ ዘመድ ሆኖ ተገኘ። ባሻዬ ባንድ በኩል በ‹ጥልቅ ተሃድሶው›ና ዕርምጃው ቢደሰቱም፣ የዘመናት ፀሎታቸውና የመልሱ ጅማሮ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ወንጌል የታሰሩትን ጠይቁ የተጨነቁትን አፅናኑ በሚለው ያምናሉና ግራ ተጋብተው ሰነበቱ። ግን ሁለት ወዶ ይሆናል? ከባሻዬ ልጅ ጋር ሰሞኑን ስንወያይ የነበረው ይኼንኑ ነበር። “በራስ ሲመጣና በሌላ ሰው ሲሆን ስሜትና ምክንያታዊነት፣ ደግሞም አስተዛዛቢና የሚያሳዝን አቋም ዋዛ አይመስለኝም፤” ሲለኝ ነበር። እውነቱን ነው።

“ታዲያ ለምን ይመስልሃል ‹አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝን ትተህ እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት› በል የሚባለው፤” ስለው፣ እሱም ሲለኝ እንቆይና ተያይዘን ወደተለመደችዋ ግሮሰሪያችን እናመራለን። እዚያ አንድ አንድ እያልን በጨዋታ መሀል አንዱ፣ “እውነት ማን ይሙት ስንቶቻችን የገዛ ጥቅማችንን፣ ዓላማችንን፣ የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችን ለላቀ ዓላማ ወገንና አገር ስንል መስዋዕት ልናደርግ ዝግጁ ነን? የምሬን ነው። መንግሥት ብቻውን ‹ጥልቅ› ቢል ‹ስምጥ› ቢል ብቻውን ምን ያመጣል? ‹ተሃድሶ› እኮ በዛሬና በነገ መሀል ትናንት ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ነው። ታዲያ ማን ነው ራሱ ላይ የሚፈርደው?” ብሎ ትክ ብሎ አየን። ስናየው ሲያየን ቆይቶ ተነስቶ ወጣ። እኛም ተነስተን ሄድን። ቅዠት ቢመስልም ሁሉም ከራሱ ጀምሮ ሲታደስና ሲነፃ አልታይህ አለኝ። ከገዛ ጎጆው ጀምሮ ፍትሕን የሚደረምስ አባወራ ስለአገር ፍትሕ ቢደሰኩር ማን ይሰማዋል? የልጆቹን እናት እየበደለ የሚኩራራ ስለሰፊው ሕዝብ በደል ቢያወራ እንዴት ሆኖ? በዘረኝነት የተለከፈ ወናፍ ‹አገሬ አገሬ› እያለ ቢያቅራራ ማን ሰምቶ? በራስ ወዳድነት አገር የሚዘርፍ ሌባ ሕዝብ ሕዝብ እያለ ቢያናፋ ማን ይቀበለዋል? አስመሳይ ሲወራጭ አድርባይ ያጅበዋል ነው የተባለው? መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት