Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጥንታዊቷ ሰይፍ አጥራ

ጥንታዊቷ ሰይፍ አጥራ

ቀን:

ከወራት በፊት ጎንደርን በጎበኘንበት ቀናት የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋሞችም እየሠሩ ያሉትን እንድንመለከት ጋብዘውን ነበር፡፡ የኪነ ጥበብ ማዕከላት፣ ሙዚየሞችና ሌሎችም ታሪካዊ ሥፍራዎችን እንድንመለከት በርካታ ጥሪዎች ቀርበውልናል፡፡ ከነዚህ መካከል ከጎንደር በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት በምትገኘው ማክሰኚት ወረዳ ደጎማ ቀበሌ የሚገኘው ጥንታዊው ደብረ ፀሐይ ሰይፍ አጥራ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል፡፡

ከጎንደር እስከ ማክሰኚት ያለውን የአስፓልት መንገድ ዘና ብለን በመጓዝ ላይ ሳለን ድንገት ሚኒባሱ ወደ ቅያስ መንገድ ታጠፈ፡፡ ያልጠበቅነው ወጣ ገባ መንገድ ባይመችም በጉዟችን ማገባደጃ የሚጠብቀንን ታሪካዊ ቦታ ተስፋ በማድረግ ተወጣነው፡፡ ጥንታዊ ታሪካዊ ሥፍራዎችን የሰዎች ሠፈራ በሳሳባቸው አካባቢዎች ማግኘት የተለመደ በመሆኑ ቀስ በቀስ ከተማውን ወደ ኋላ ትተን ስንጓዝ አልተገረምንም፡፡ አልፎ አልፎ የማገዶ እንጨት ተሸክመው ከሚጓዙ ሴቶችና የቀንድ ከብት ከሚነዱ ወንዶች ባለፈ ብዙ ሰው አይታይም፡፡

በመንገዳችን ያለፍናቸው አነስተኛ ቀበሌዎች በእግረኛ መንገድ አቅራቢያ ካሉ ቤቶች በዘለለ መኖሪያ አይታይባቸውም፡፡ ከሰዓታት ጉዞ በኋላ በሩቁ ወደ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን መቃረባችንን የሚጠቁሙ ምልክቶች ይታዩ ጀመር፡፡ ከሚኒባሱ እንደ ወረድን ወደ አንድ ቅጥር ግቢ ተጋበዝን፡፡ በግቢው ውስጥ ያሉት በተመሳሳይ ቅርፅ የተሠሩ ጎጆ ቤቶች ከአንድ ሰው በላይ የሚያኖሩ አይመስሉም፡፡ አንዳቸውን ከሌላቸው ለመለየት ከሚያዳግቱ ጎጆ ቤቶች አቅራቢያ በርካታ ጠፍጣፋ ድንጋዮች በክብ ቅርፅ ተደርድረዋል፡፡

በአንድ ከፍ ያለ ድንጋይ ዙሪያ በስልት የተደረደሩት ድንጋዮች መሬት ላይ ተቀምጦ በጀርባ ደገፍ ለማለት እንዲቻል ታቅደው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ጀርባቸውን ድንጋዩ ላይ ያሳረፉት የአብነት ተማሪዎችም ሁኔታው የተመቻቸው ይመስላል፡፡ ተማሪዎቹ በዙሪያቸው ለሚከናወን ከትምህርታቸው ውጪ የሆነ ነገር ትኩረት የላቸውም፡፡ መምህራቸውን እየተከታተሉ ቅኔውን ሳያዛንፉ ይመልሳሉ፡፡

ፍፁም ጥሞና በሞላበት አካባቢ የአብነት ተማሪዎቹን ዜማዊ ምልልስ ብቻ ማድመጥ መንፈስን ያድሳል፡፡ ዓመታት ያስቆጠሩ ዛፎች በአካባቢው ጥላ ማውረዳቸው ሲታከልበት ልዩ ደስታ ያጭራል፡፡ ጥንታዊቷ ሰይፍ አጥራ፣ የአብነት ትምህርት ከሚሰጥባቸው አጥቢያዎች አንዷ ናት፡፡ ምንም እንኳ የተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም፣ ዛሬም ዕውቀትን ሽተው ወደ መምህራኑ የሚሄዱ አሉ፡፡

ከአብነት ተማሪዎች መካከል ወደ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች እየፈለሱ ትምህርቱን  የሚያቋርጡ፣ በተቃራኒው በትምህርቱ የሚዘልቁም አሉ፡፡ የተማሪዎቹ መኖሪያ የሆኑት ጎጆ ቤቶች ከሚገኙበት ቅጥር ግቢ በቅርብ ርቀት ጥንታዊቷ ሰይፍ  አጥራ ትገኛለች፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ጥግ ይዘው በአርምሞ የተቀመጡ አባቶች ይገኛሉ፡፡ በግቢው አማካይ ሥፍራ በጅማሮ ላይ የሚገኝ ግንባታ ይታያል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗን ጥንታዊነት የሚያውቅ ሰው አዲስ እየተከናወነ በሚገኘው ግንባታ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የተመሠረተችው በ1335 ዓ.ም. በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ አፄ ሚናስ አቡነ ማቴወስ በተባሉ ጳጳስ እጅ ቅብዐ መንግሥት ተቀብተው የነገሡባት ንጥታዊ ገዳም ናት፡፡ አፄ ዮሐንስ በ1867 ዓ.ም. የአካባቢውን አየር ንብረት ምቹነትና ለጤና ተስማሚ መሆኑን ከግምት በማስገባት ገዳም ማድረጋቸውንም ታሪክ ያስነብባል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ በአራት የአብነት ትምህርት ቤቶች ማለትም በድጓ፣ በአቋቋም፣ በቅኔና በቅዳሴ ትምህርት ቤቶች ለዘመናት ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

በደብሩ ከሚከበሩ በዓላት መካከል በየዓመቱ ኅዳር 21 ቀን ዳግማዊ አክሱም ጽዮን ተብላ የሚከበረውና በየዓመቱ ጥር 11 እና 12 የሚከበሩት ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ ይጠቀሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በይበልጥ የምትታወቀው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ኢማም አህመድ ኢብራሂም (ግራኝ) ቤተ ክርስቲያኗን ሊያቃጥል ሞክሮ ባለመቻሉ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናቱ ታሪክ እንደተገለጸው፣ ‹‹በወቅቱ በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ዙሪያ ነጭ የንብ ሠራዊት እንደ ሰይፍ ሲነሳ የተመለከተው ግራኝ አህመድ በተፈጠረው ነገር ተገርሞ መጠሪያ ስሟን ሰጥቷታል፡፡ በወቅቱ ደብሩ አጠገብ በሚገኝ ወይራ ዛፍ ላይ ሆኖ ሲያለቅስ ያገኘውን ባላባት ማን እንደሚባልና የቤተ ክርስቲያኗ ስም ማን እንደሆነ ሲጠይቅ፣ ባላባቱ ስሙ አብርሃም እንደሆነና ደብሯ ጽዮን ማርያም እንደሆነች ይነግረዋል፡፡ ግራኝም ከዚያን ዕለት በኋላ ባላባቱ ‘ጊዜው ሞላ’ ቤተ ክርስቲያኗም ‘ሰይፍ አጥራ’ የሚል ስም ሰጣት፡፡

ከአፄ ዮሐንስ አራተኛ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከቆላና ከደጋ ማለትም ከቆላ ከዋረብ፣ ከጋይንሆ፣ ከማር ታዴዎስ፣ ከደጋ ደግሞ ከዛንተራ፣ ከአንባጨራና ከሌሎችም አካባቢዎች ለመተዳደሪያ የሚሆን ገቢ ለቤተ ክርስቲያኗ ይመደብ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ሕንፃ ለረዥም ዓመታት ሳይታደስ በመቆየቱ መፈራረስ የጀመረው ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ ለሰዎች ሕይወት እንዲሁም ለጥንታዊ ቅርሶች ደኅንነት አሥጊ እየሆነም መጣ፡፡ ለዓመታት ጥገና ያልተደረገለትን ሕንፃ ለማደስ መሞከር በራሱ አሥጊ ነበር፡፡

ሕንፃው ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ የተመለከቱ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች፣ የዘመመውን ጥንታዊ ሕንፃ አፍርሰው አዲስ ለመገንባት ተገደዱ፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረው ግንባታ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑን የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መላከ ፀሐይ ካሳሁንና የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሊቀ ትጉሀን መለሰ በላይ ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ጥንታዊው ቅርስ ፈርሶ በአዲስ መተካቱ ትክክለኛ ዕርምጃ ባይሆንም፣ ሕንፃው ካለበት ሁኔታ አንፃር አማራጭ እንዳልነበር ያስረዳሉ፡፡

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቅርሶች በሃይማኖት ተቋሞች ሥር የሚገኙ ሲሆኑ፣ በያሉበት አካባቢ ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው ለማለት አይቻልም፡፡ እንደ ሰይፍ አጥራ ያሉ ጥንታዊ ደብሮች ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያተረፉና የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት የመዘገባቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ አደጋ ያንዣብብባቸዋል፡፡

የጥንታዊቷ ሰይፍ አጥራ ሕንፃ መፈራረስ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በግባቡ ሊጠበቅ ይገባ ነበር፡፡ ሕንፃውን ማዳን ባይቻልም ቢያንስ የአዲሱ ሕንፃ ግንበታ መፋጠን አለበት፡፡ ሆኖም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪዎች እንደሚሉት፣ ሕንፃውን ለማጠናቀቅ የሚፈለገው ገንዘብ ካልተሰበሰበ ግንባታው ለዓመታት መጓተቱ አይቀርም፡፡

በሕንፃው ግንባታ ወቅት የቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በሚል በቅጥር ግቢው ውስጥ በሚገኝ አንድ ክፍል ተቀምጠዋል፡፡ ቅርሶቹ በዚህ ሁኔታ መከማቸታቸው ጥንታዊ ይዘታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ሰይፍ አጥራን ከጎበኘን ከጥቂት ቀናት በኋላ ላሊበላ ውስጥ በቅርስ ጥበቃና ጥገና ዙሪያ የተዘጋጀ ወርክሾፕ ተካፍለን ነበር፡፡

በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የተዘጋጀው ወርክሾፕ፣ በዋነኛነት በሃይማኖት ተቋሞች የሚገኙ ቅርስ አስተዳዳሪዎችን ያማከለ ነበር፡፡ በአብዛኞቹ የሃይማኖት ተቋሞች የሚተዳደሩ ቅርሶች በአያያዝ ጉድለት ከመበላሸታቸው ባሻገር ለስርቆትም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ቅርሶቹ ለሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ከመጋለጠቸው ባሻገር ጉዳት ሲደርስባቸው ተገቢውን ጥገናም አያገኙም፡፡ ይህም ከባለሙያና ከግብዓት እጥረት እንዲሁም ትኩረት ከመንፈግም የመነጨ ነው፡፡

ሰይፍ አጥራ በሃይማኖት ተቋሞች ሥር ያሉ ቅርሶች ምን ያህል ቸል እንደተባሉ ማሳያ የሚሆን ሥፍራ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1995 ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያኗ ቅርሶች ተዘርፈው ነበር፡፡ መዝባሪው ከቀናት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ እንጦጦ አካባቢ እጅ ከፍንጅ ቢያዝም፣ ቅርሶቹ በቀጣይም ለአደጋ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡

ሰይፍ አጥራ ጥንታዊ ከመሆኗ ጎን ለጎን በአቅራቢያው ዕውቁ ጎንድ ተክለ ሃይማኖት ገዳምና በቅዱስ ላሊበላ የተመሠረተ ቤተ ክርስቲያን መኖሩ ሥፍራውን የቱሪስት መዳረሻ ያደርገዋል፡፡ የደብሩ ቅርሶች ካልተጠበቁ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው የሚያመሩበት ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ ምንም እንኳን ጥንታዊው ደብር ቢፈርስም፣ ቢያንስ አዲሱ ተገንብቶ ቢጠናቀቅ ለጉብኝት ምክንያት ይሆናል፡፡

ሊቀ ትጉሀን መለሰ እንደሚሉት፣ ቅርሱን ጠብቆ ማቆየት እንዲቻል ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ‹‹ቅርሱን ለመታደግ የድረሱልን ጥሪ እያሰማን ነው፡፡ ቅርሱ ታሪካዊና የቱሪስት መስህብም ነው፤›› ይላሉ፡፡ አስተዳዳሪው መላከ ፀሐይ ካሳሁን በበኩላቸው፣ ‹‹ቅርሱን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል በአዲሱ ደብር ግንባታ ሁሉም አካል ሊረባረብ ይገባል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በተለይ በአብነት ትምህርት የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት እንደመሆኗ ትኩረት ያሻታል ይላሉ፡፡ የደብሩ የገንዘብ አቅም እያሽቆለቆለ ሲሄድ ግን የአብነት ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ አልቀረም፡፡ በአሁን ወቅት ያሉት የአብነት ተማሪዎች ከ50 አይበልጡም፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪዎች እንደሚሉት፣ የቤተ ክርስቲያኗን ቅርሶች በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ከማሸጋገር በተጨማሪ የጎብኚዎችን ቁጥር የመጨመር ዕቅድ አላቸው፡፡ ቅርሶቹን በመጠበቅ ረገድ፣ ሕንፃው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበትና አፋጣኝ ዕድሳት እንደሚያስፈልገው ለአካባቢው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቢያሳውቁም አፋጣኝ ምላሽ ስላላገኙ በግላቸው እንቅስቃሴ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያኗን ቅርሶች በመጠበቅ ረገድ፣ በተለይም ዘረፋ ከተካሄደ በኋላ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢወስዱም፣ አሁንም የቅርሶች አየያዝ መዘመን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ቅርሶቹን ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የደብሩ ንብረት ስለመሆናቸው የሚገልጽ ማኅተም በቅርሶቹ ላይ ባያደርጉ፣ ቅርሶቹ በተዘረፉበት ወቅት ከፖሊስ ማስመለስ ይቸገሩ እንደነበር አስተዳዳሪው ያስረዳሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቷን ጥንታዊ ከሚያደርጓት ቅርሶች መካከል የቅጥር ግቢው አሠራር ይጠቀሳል፡፡ ቅጥሩ የጎጃም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ራስ መንገሻ አቲከምን መድበው ያሠሩት መሆኑን ታሪክ ያስነብባል፡፡ ተመሳሳይ ታሪክ ያለውን ሕንፃ ለመታደግ ባለመቻሉ፣ አፍርሶ ወደ መገንባት መሄዳቸውን የሚገልጹት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሊቀመንበር፣ ‹‹ድጋፍ እንዲደረግልን ጥሪ ስናቀርብ በአፋጣኝ ምላሽ አላገኘንም፡፡ በሕይወትና በንብረት ጉዳት ከመድረሱ በፊት እንቅደም ብለን ጥንታዊውን አፍርሰን አዲስ ለመሥራት ተገደድን፤›› ይላሉ፡፡

በአንድ ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው አዲሱ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እንደሚያሻው የገለጹልን አስተዳዳሪው በበኩላቸው፣ የአቅም ማነስ ከሕንፃ ግንባታው ባሻገር በአብነት ተማሪዎች ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖም ይናገራል፡፡ ‹‹ከማጣት የተነሳ የአብነት ተማሪዎችና ካህናትም ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ይሰደዳሉ፤›› ይላሉ፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የሥራ አማራጮች እንደሚያስፈልጉም ያክላሉ፡፡

አገሪቷ ከምትጎበኝባቸውና ትውልዱ ከሚኮራባቸው ቅርሶች መካከል በተለያዩ የሃይማኖት ተቋሞች ስር ያሉ ቅርሶች ተጠቃሽ እንደመሆናቸው፣ የጥበቃቸው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የቅርሶቹ ይዘትና ታሪክ ተጠንቶ በአግባብ መመዝገብ እንዳለባቸው በርካታ የቅርስ ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡ የቅርሶቹ አቀማመጥና ጉዳት ሲደርስባቸው የሚደረግላቸው ጥገናም ትኩረት ያሻዋል ይላሉ፡፡ የሰይፍ አጥራን ጥንታዊ ይዞታ ማዳን ባይቻልም አሁን ያለውን ለመንከባከብና ለመጠበቅ ጊዜው አልረፈደም፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...