Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሙስናን አከርካሪ መስበር የሚቻለው ሕዝብ ግንባር ቀደም ሲሆን ብቻ ነው

የሙስናን አከርካሪ መስበር የሚቻለው ሕዝብ ግንባር ቀደም ሲሆን ብቻ ነው

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

        እሑድ ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ዕትም ላይ “መንግሥት ሙስናን ለመታገል ቁርጠኝነት ካለው የራሱን ጓዳ ይፈትሽ›› በሚል ርዕስ በተለይ ፓርላማ ላይ በቀረበ የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የቀረበ ጽሑፍ አንብቤ ነበር፡፡ ይህ ክፉኛ የነገሠውን ሙስናና ማጭበርበርን ለመነካካት የሞከረ ጽሑፍ ጠለቅ ብሎ አሁን ከተሃድሶ በኋላ ያለውንና ያልተነቀለውን ችግር አልዳሰሰም፡፡ በልበ ሙሉነት ሕዝብ የውስጥ ምሬትንም አጉልቶ አላወጣም ባይ ነኝ፡፡ ይሁንና በጉዳዩ ላይ የግል አተያይም ቢሆን መነሳቱን አከብራለሁ፣ እኔም የበኩሌን ሐሳብ ለመጠቆም እሻላሁ፡፡

በመሠረቱ የሙስና ትንሽና ትልቅ የለውም፡፡ ወይም ደረጃው ቢለያይም ሙስና በወንጀልነቱ መቼም አንድ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያለው ዘራፊም ሌባ . . . ሌባ ነው፡፡ መቼም ቢሆን ግን እንደ መጠኑና እንደ ዓይነቱ ተጠርጣሪን በሕግ መጠየቅ፣ ዳኝነት ማግኘት፣ የተዘረፈውን የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ለባለቤቶቹ መመለስ አለበት፡፡ ሕግ ነፃ ያውጣው፡፡ ሕግም ጥፋተኛ ነህ ብሎ ማስረጃውን መርምሮ ይቀጣው ዘንድ መታገል የሁሉም ድርሻ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በእርግጥ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ራሱ እስካሁን ለተፈጠረው ስህተት ሁሉ  ችግሩ የአመራሩና የቢሮክራሲው ነው ብሎ አምኖ በመቀበል ‹ጥልቅ ተሃድሶ› ውስጥ መግባቱን በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ እውነታው ግን በወቅቱ እነዚህን በስሙ ሲነግዱና ሕዝቡን ሲያስለቅሱ የኖሩ ዋልጌዎች ቢያርም፣ ቢቀጣና ከኃላፊነት ቢያነሳ ኖሮ ጉዳዩ ‹‹ይህቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም›› አይሆንም ነበር፡፡ በሕዝብ ሀብት የከበሩና የደለቡ፣ ፈሪኃ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ መንግሥትና ሕዝብን በዘረፋ ተግባራቸው ሆድና ጀርባ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ፣ ዘርፈውም፣ ነጥቀውም የማይጠግቡ የቀን ጅቦችን በጊዜው ማረም ነበረበት፡፡ አንዳንዴ የተፈቀደ ሌብነትና አየር በአየር እስኪመስል ድረስ በይፋ መታየቱ ለሕዝቡም ከማስገረም ያለፈ እንደነበር አይካድም፡፡

    ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ወይም እንደ ፓርቲ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ በአገሪቱ በየትኛውም ጊዜ ያልነበሩ፣ ያልታዩና ያልተሠሩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ዛሬም በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬም ሆነ ትናንት በውስጡ ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸው ከብረት የጠነከረና ‹በሕይወቴ እስከ ዕለተ ሞቴ የምቆመው ለሕዝብ ጥቅም ነው› ብለው የቆሙ ብርቱዎች የመኖራቸውን ያህል፣ ከታች ጀምሮ ሙስናን መተዳደሪያ ያደረጉም አሉ፡፡ ‹ድህነቴን መንግሥትና ኢሕአዴግ የሰጠኝን ወንበር ተጠቅሜ አሸንፈዋለሁ› ብለው የተነሱ ማፈሪያዎች አሁንም አልተራገፉም፡፡ ድርጅቱም ሆነ መንግሥት ለአገር የሠሩትን ታላላቅ የልማትና የዕድገት ሥራዎችን ጥላሸት የሚቀባ ድርጊት በመፈጸም፣ ሕዝብና መንግሥትን አናክሰው እንደነበርም አይካድም፡፡ ያለፈው አልፏል እንኳን ቢባል፣ አሁንም በአዲስ አበባ የግብር ግመታ ላይ፣ በሆቴሎች የጤና አጠባበቅ ላይ፣ የባህልና ቱሪዝም መሥፈርት ፍተሻ ላይ፣ እንዲሁም በመንግሥት የዕቃና አገልግሎት ግዥ  በኩል የከፋ መደራደር እየታየ ነው፡፡ በየአቅጣጫው በዘረፋ ላይ የተሰማሩ ሌቦች አሁንም እያገሱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹማ ‹የማጣሪያ ሽያጭ› የሚመስል ዘረፋ ላይ ተጠምደዋል፡፡

ትልቁ ችግር ደግሞ መንግሥት ቢዘገይም እነዚህን ጉድፎች ለማፅዳት ያደረገው ሙከራ የተጣለውን ተስፋ ያህል አለመሆኑ ነው፡፡ ከሕዝባዊው ተቃውሞ በኋላ ዘረፋን ለመታገል በጀመረው መንገድ አበጥሮና አንጠርጥሮ በመታገል በሕግ ተጠያቂ ማድረግ አልቻለም፡፡ ምናልባት በየክልሉ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ የታችኛው እርከን አመራሮችና በሕግ ከተጠየቁ በጣት የሚቆጠሩ ከፍተኛ አመራሮች በስተቀር አብዛኛው ሳይነካ ታልፏል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነቱ በመንግሥትና በሕዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለግል ጥቅም አሳልፎ በማዋልና በዘረፋ በከበሩት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በወንጀል ተባባሪዎቻቸውና በሸሪኮቻቸው ላይ መሆንም ይገባው ነበር፡፡ የሰሞኑ የእሥር ዘመቻም ጠለቅ ብሎ በብዙዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነት ካላመጣ የይስሙላ ይሆናል፡፡

አንዳንዶች በፖለቲካ ላይም ይሁኑ በሌላ መስክ ዘርፈው ከጣሪያ በላይ ስለከበሩ አይነኬ የሆኑ መስለዋል፡፡ በየትኛውም ፍትሐዊ መንገድ በሁለት አሥርት ዓመታት ሊገኝ የማይችል የሀብትና የቅንጦት ማማ ላይ ወጥተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም እነሱ ከተነኩ አገር ይፈርሳል የሚለው ኢአመክኗዊ አስተሳሰብ በሕዝቡ ውስጥ እንዲናፈስ ያደርጋሉ፡፡ ይህ አስተሳሳብ ግን በምንም መንገድ ቢሆን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ አሁንም ሊፈተሽ የሚገባው የተዛባ አስተሳሳብ ነው፡፡

  በመሠረቱ ተደጋግሞ እንደተባለው ሌብነት የብሔር ኮፍያ ሊበጅለት አይችልም፡፡ ከየትም ይምጣ፣ የትም ይኑር ጥገኛና ሙሰኛ መጋለጥ አለበት፡፡ ከድርጊቱም መታረም ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች ታላቅ አገር ውስጥ ያለው ሕዝብ በብዙ ሺሕና ሚሊዮኖች ድር የተሳሰረ፣ የተዋለደ፣ የተጋባ፣ አብሮነቱን አጥብቆና አክብሮ የኖረና የሚኖር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል በዘራፊዎችና በሙሰኞች አልጠግብ ባይነት በተፈጸመ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ዝርፊያ አገር አትፈርስም፡፡ አትበተንም፡፡ ጥንትም ዛሬም የአገሩ ዋና ጠባቂ ዘብ ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ሠራዊቱም፣ ደኅንነቱም፣ ፖሊሱም የኢትዮጵያ ልጅ ነው፡፡ የሕዝብ ልጅ ነው፡፡ አገሩን ከሕዝቡ ጎን ቆሞ ይጠብቃል፡፡ ይልቁንም መንግሥት አሁንም ፀያፉን ሙስና ከሕዝብ ጎን ቆሞ ይታገል፡፡ ካልሆነ ግን ዳፋው ለሥርዓቱ ለራሱ እንደሚተርፈው ጥርጥር የለውም፡፡

ብርቱ ትግል ከተደረገ ሙሰኞችና አልጠግብ ባዮች በሥርዓቱ በሕግ ጥላ ሥር ውለው ተጠያቂ ይሆናሉ እንጂ፣ በእነሱ ምክንያት የምትፈርስ በአንድ ጀንበር የተገነባች ኮሽ ሲል የምትናድ አገር የለችንም፡፡ በመሠረቱ አሁን ተጀምሮ ቆመ እንጂ አገርና ሕዝብ የበደሉና የዘረፉ ለሕግና ለፍትሕ ማቅረብ ዓይነቱ ቢለያይም ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡ ወደፊትም ግልጽነትና ተጠያቂነት እስካሉ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

መንግሥት ችላ ካላለና በተሃድሶው መንፈስ ላይ ውኃ ሊቸልስበት ካልሞከረ፣ ሕዝቡም አጋርነቱን የሚነሳው አይመስለኝም፡፡ በተለይ እውነተኛ የሆኑ ዜጎች ሁሉ ሙሰኞችንና ዘራፊዎችን ፀንተው በመዋጋት፣ ጥቆማ በመስጠትና ማንኛውንም ዓይነት ትብብር በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በመሠረቱ አጥፊዎች ሳይሸሸጉ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጎች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ ግን መንግሥት በሕዝብ ይተማመን፡፡ የሕዝብን ድምፅ ይስማ፡፡

ሌባው ኃይል ነጋዴም ይሁን ቄስ፣ ፖለቲከኛም ይሁን ሼህ አልያም ደላላም ይሁን ዳያስፖራ ለአገር የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሌባው ሕንፃ ቢገነባ፣ ዘመናዊ መኪና ቢይዝና ልማታዊ ኢንቨስተር ቢመስል በስርቆትና በማጭበርበር የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በመዝረፍ ከብሮ የተገኘ ከሆነ ሌባ . . . ሌባ ነው፡፡ ያውም ሞላጫ ሌባ፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጧጧፍ ቸል ቢል እንኳን ሙሰኛውንና ዘራፊውን ለሕግ ለማቅረብ በሚደረገው ትግል ሕዝብ በፅናት መቆም አለበት፡፡ ዘራፊዎችን ማጋለጥም እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ትግሉ የጋራ መሆንም አለበትና፡፡

የፀረ ሙስና ትግሉ በሥርዓት መልክ ተጠናክሮ ይቀጥል እንጂ፣ በአንድ ጀንበር አገራዊ ለውጥ እንዲያመጣ አይጠበቅም፡፡ ግን በቁርጠኝነት ጥገኝነትን ማክሰም እንደሚቻል የብዙ አገሮች ተሞክሮ አለ፡፡ በሁሉም ተራማጅ የፀረ ሙስና ታጋይ አገሮች እንደታየው ግን፣ መንግሥት ሕዝብን ግንባር ቀደም አድርጎ ካልተንቀሳቀሰና ካልሠራ ለውጥ ከሰማየ ሰማያት አይወርድም፡፡ ስለሆነም ሳያሳልሱ ተባብሮ መታገል ያስፈልጋል፡፡

ሙሰኛውና አልጠግብ ባዩ በየቦታው ከላይ እስከ ታች በሕዝቡም ውስጥ ከከተማ እስከ ክልል የዘረጋውና የገነባው የተሳሰረ የኔትወርክ መዋቅር አለው፡፡ አሁንም ድረስ ‹ከተመደበልህ ባለሙያ ጋር ጨርስ› የሚል የሥራ ኃላፊ በኔትወርክ በመሞዳሞድ ላይ ነው፡፡ ፍርድ ቤትንና የፀጥታ ኃይሉን ጭምር ይኼ አስተሳሳብ ሽርሽሮት ሲታይ ደግሞ ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ስለሆነም ይህንን አጥርቶ ለመለየትና መረቡን ለመበጣጠስ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ የተመዘበረውን የአገርና የሕዝብ ሀብት ለማስመለስ እጅግ ሰፊ ጊዜና ገንዘብ የሰው ኃይል ይጠይቃል፡፡ ትብብርና ቁርጠኝነትንም ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት የለብ ለብ ሥራ ሌሎች ዘራፊዎች እንዲፈጠሩ፣ የበፊቶቹ እንዲያንሰራሩና አገር ለማውደም በር ይከፍታል፡፡  

በመሠረቱ የፀረ ሙስና ትግሉ  በችኮላ፣ በፍጥነት፣ በግርግርና በስሜት የሚከናወን አይደለም፡፡ ማስረጃዎች ሊኖሩ ቢችሉም መረጃን በአግባቡ ማጠናከር ይጠይቃል፡፡ እንደ መንግሥት ሲታሰብ ደግሞ ግለሰቦች በወንጀል ተጠርጥረው ቢያዙም፣ ወንጀል ነው ብሎ የሚያፀናው ወይም የሚሽረው በተጨባጭ የቀረበለትን የሰዎችና የሰነድ ማስረጃና መረጃ መርምሮ ውሳኔ የሚሰጠው ፍርድ ቤት ነው፡፡ የሕግ የበላይነትም የሚረጋገጠው በዚህ መንገድ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚለካው ደግሞ ተጠርጣሪዎች በአግባቡ ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡ እነሱ ፈጸሙ የተባሉትን ወንጀል ሌላው ፈጽሞት ዝም መባሉ የሕግ የበላይነትን እንደማያመላክት መረዳት ይገባል፡፡ ተጠያቂነት ሲመጣ አድሎአዊ መሆን ስለሌለበት፡፡

በሙስና ትግል ስም ያላግባብ በበቀል ስሜት በመነሳት ንፁኃን እንዳይወነጀሉና ሰብዓዊ መብታቸው እንዳይነካ፣ መንግሥት ጥበቃና ጥንቃቄ ማድረግም አለበት፡፡ በስሜት መነዳትና ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በመረጃ ተደግፎ መሄድ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ልዩ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው የሚታመነው፡፡ መጠየቅ ያለባቸው ግን አሁንም ሊታለፉ አይገባምና ይጠየቁ፡፡ ለሕግና ለፍትሕም ይቅረቡ፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ የሚሆን ምንም ነገር የለም፡፡ ግለሰቦች ከአገርና ከሕግ በላይ አይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ በሕግ መጠየቅ ያለባቸው ሲጠየቁ ነው ሥርዓት እንደ ሥርዓት ሊቆም የሚችለው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሥራው ላይ ለተሰማሩት የፀረ ሙስና ኮሚሽን አካላት  ብቻ ተሰጥቶ የነበረውን ሥራ ለማጠናከር እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ ተቋማት መዋቀራቸው ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ብቻውን ተይዞ ከሌላ ሥራ ጋር ሳይቀላቀል የሚሠራና ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ነው ተብሎም ኢትዮጵያዊ ‹ኤፍቢአይ› እንደተቋቋመ ተሰምቷል፡፡ ለሙስና ወንጀሎች ብቻ ተሰይመው የሚሠሩ፣ የሚያጣሩና የሚከታተሉ ዓመታትን ብቻ የሚያስቆጥሩ ሳይሆን፣ በቀረበላቸው ተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመርኩዘው አጣርተው ፍርድ የሚሰጡ የተለያዩ ልዩ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋምም ካልተቻለ ዳፋው ለትውልድ ሊተርፍ ይችላል፡፡ ወንጀልን ከማጣራት ጀምሮ እስከ ፍርድ አሰጣጡ ድረስ ሕግና ሕግን ብቻ መከተል ተገቢ ነው፡፡

 በየደረጃው በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር በደልና በፍትሕ ዕጦት የሚማረሩ ዜጎች አሁንም ሊደመጡ ግድ ይላል፡፡ በደላላውና በአቀባባዩ አማካይነት በአገር፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንም ሕዝቡ የሚያጋልጥበት ሥርዓትና መድረክ መስፋፋት አለበት፡፡ በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን ክልል፣ ክፍለ ከተማ፣ ዞንና ወረዳ ድረስ አዋቅሮ በየደረጃው ያሉ ሙሰኞችና ዘራፊዎችን እንደ ጥፋታቸው መጠንና ደረጃ ለማጋለጥ የሚያስችል ትግል መቀጣጠል አለበት፡፡ ሕዝቡ በየደረጃው የሚሰጠው ተጨባጭ ማስረጃም ቅሬታን ባስነሱበት መጠን ራሱ በሚገኝበት፣ በሚያይበትና በሚከታተልበት ግልጽ ችሎት የዳኝነት ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ በዚህ ደግሞ መንግሥት አሁን በተጨባጭ ይፈተንበታል፡፡

ከወራት በፊት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጾ ነበር፡፡ የሙስና ወንጀሎችን መመርመር ከተጀመረ በኋላ ከሕዝብ፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት 260 የሚሆኑ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች እንደደረሰው ጠቅሶ፣ በሙስና ወንጀል ከተጠረጠሩ 260 ግለሰቦች መካከልም 130 በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ እስካሁን ያልታወቀው ግን ተጠርጣሪዎቹ እነማን ናቸው? ጥቆማውስ ለምን ተጠናክሮ መቀጠል ተሳነው? ወይስ ወንጀል ፈጻሚዎቹ እነዚህ ብቻ ናቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሰጠ የለም፡፡ አሁን ደግሞ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ቢዘገይም ማንነታቸው ታውቋል፡፡ ቀሪዎቹ እነ ማን ናቸው የሚለውን የሕዝብ ጥያቄ መመለስ ያለበት ራሱ መንግሥት ነው፡፡

ከወራት በፊት ከታሰሩት ውስጥ በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ የሀብት ንብረት ዕገዳ መጣሉ፣ በስምንት ትልልቅ አክሲዮኖች፣ በአራት ሕንፃዎች፣ በ49 ተሽከርካሪዎች፣ በ22 መኖሪያ ቤቶችና በሁለት ፋብሪካዎች ላይ ዕገዳ መደረጉ ተገልጾ ነበር፡፡ የተቀሩት  የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደነበረም ተሰምቷል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የመንግሥት አመራር አካላትና ባለሙያዎች እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል፡፡ ከዚያ በኋላስ ምነው ስለሒደቱ ሕዝብ መረጃ እንዳያገኝ ሆነ? የተዘረፈው ሀብትስ ዕውን ይኼው ብቻ ነው? ማለትም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ካለው ልምድስ አንፃር የፍርድ ሒደቱ ቅልጥፍና አለው? ወይስ ያው በምልልስ ዕድሜ ለመግፋት ነው? የሚለው ጉምጉምታም በብዙዎች ሲነሳ ይደመጣል፡፡ በቅርቡ በቁጥጥር ስለዋሉት ተጠርጣሪዎችና ፈጸሙት ስለተባለው የሙስና ወንጀል ዝርዝር ሕዝብ በግልጽ የማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው መዘንጋት አይገባም፡፡  

ሙስና በባህሪው ውስብስብና ብርቱ የመረጃና የማስረጃ ማሰባሰብ ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሁንና ቁርጠኝነቱ ካለ ግን በሕዝብ ተሳትፎ ውስብስቡን ድርጊት ማጋለጥ ይቻላል፡፡ ‹በእከክልኝ ልከክልህ› አጉል መሞዳመድ ሙስናን መታገል ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ ከትንሿ ቀበሌ እስከ ፌዴራል ትልቅ ተቋም ድረስ፣ እንዲሁም በክልሎች ውስጥ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች ከሕዝብ የተሰወሩ አይደሉም፡፡ ሥርዓቱ በሕግ አገር ማስተዳደር ከፈለገ ሕዝብን (የሥልጣን የመጨረሻው ባለቤት) በግንባር ቀደምትነት ያሠልፍ፡፡ ‹‹የሙስናን ዋርካ ቅርንጫፉን ሳይሆን ግንዱን ይቆርጡታል›› እንደሚባለው፣ ሕዝብ ያልተሳተፈበት የሙስና ትግል ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የሙስናን አከርካሪ መስበር የሚቻለው ደግሞ የሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...