በዳዊት እንደሻው
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የአዳሚ ቱሉ የፀረ አረም መድኃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበርና የአዋሽ መልካሳ የአልሙኒየም ሰልፌት አክሲዮን ማኅበር፣ በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ሥር ለማድረግ ጥያቄ አቀረበ፡፡
ሚኒስቴሩ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረቡን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ሚኒስቴሩ ሁለቱን ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
መጀመርያ በክፍት ጨረታ ቀጥሎም በስምምነት ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም ፍሬ ሳያስገኝ ቀርቷል፡፡
በቅርቡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ በስምምነት ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ሚኒስቴሩ ጉዳዩን ለወራት ሲያየው የቆየ ቢሆንም፣ ይህም አልተሳካም፡፡
በዚህም ሳቢያ ሚኒስቴሩ ሌሎች አማራጮችን እንዲያይ አስገድዶታል፡፡ በዚህም መሠረት ፋብሪካዎቹን ወደ ኮርፖሬሽኑ መቀላቀልን እንደ አማራጭ በማየት፣ ፕሮግራሙን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርቧል፡፡
ከተመሠረተ 23 ዓመታት ያስቆጠረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አሁን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፣ እስካሁን ድረስ ባለው አፈጻጸም ከ370 በላይ የሚሆኑ በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ ድርጅቶችን ወደ ግል አስተላልፏል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ የፕራይቬታይዜሽን ታሪክ ትልቅ የተባለውን ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ገቢም የተገኘው መንግሥት በትምባሆ ሞኖፖል ውስጥ የነበረውን 40 በመቶ ድርሻ በ510 ሚሊዮን ዶላር ጃፓን ቶባኮ ለተባለ ኩባንያ በመሸጥ የተገኘ ነው፡፡
በሚኒስቴሩ የቀረበው ጥያቄ ከፀደቀ ሁለቱ ፋብሪካዎች በኮርፖሬሽኑ ሥር ያሉ ድርጅቶችን ቁጥር ወደ አምስት ያሳድጉታል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 280/2012 በ21.71 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ይህ ኮርፖሬሽን፣ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የተሰማራው የኬሚካል ምርቶች ላይ ነው፡፡ በሥሩም ሙገር ሲሚንቶን ጨምሮ የተፈጥሮ ጎማ ልማትና ማምረቻ ይገኛሉ፡፡
በ1990 ዓ.ም. የተመሠረተው አዋሽ መልካሳ በአሁኑ ወቅት እንደ አልሙኒየም ሳልፌት፣ ሳልፈሪክ አሲድና ኃይድሮጂን ፔሮ ኦክሳይድ ያመርታል፡፡ ፋብሪካው 322 ሠራተኞችን አሉት፡፡
በ2008 ዓ.ም. በነበረው አፈጻጸም አዋሽ መልካሳ የ81 ሚሊዮን ብር ሽያጭ በማስመዝገብ፣ ሰባት ሚሊዮን ያልተጣራ ትርፍ አግኝቷል፡፡
በ1980ዎቹ የተመሠረተው አዳሚ ቱሉ በተመሳሳይ ዓመት በነበረው አፈጻጸም 352 ሚሊዮን ብር ሽያጭና 51 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ አዳሚ ቱሉ በዚያው ዓመት በ27 ሚሊዮን ብር ወጪ የማስፋፊያ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡