Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጥጥ ልማት ወደ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር እንዲዛወር ሐሳብ ቀረበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳዊት እንደሻው

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች በተካሄደ ጥናት፣ በጥጥ ማምረትና መዳመጥ ዘርፍ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሔ ሐሳብ ቀረበላቸው፡፡ ከመፍትሔ ሐሳቦቹ አንዱ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የጥጥ ልማት፣ ወደ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተዘዋውሮ ራሱን የቻለ ተቋም እንዲሆን ይጠይቃል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የጥጥ ልማትን የሚከታተልና የሚደግፍ ተቋም በፌዴራል ደረጃ ቢኖርም፣ እስከ ታችኛው የአስተዳደራዊ መዋቅር ድረስ በመውረድ ለጥጥ አምራቹ የኤክስቴንሽን፣ የግብዓት፣ የግብይት፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማትና ከግብርና ምርምር ጋር ያለው ግንኙነት የላላና ተፈላጊውን ድጋፍ እየተሰጠ እንዳልሆነ በጥናቱ ጠቁሟል፡፡

‹‹ሲጀምር አሁን ያለው የጥጥ ልማት ዳይሬክቶሬት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር መሆኑ የጥቅም ግጭት አለው፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጥጥ እርሻ ባለሀብት ይናገራሉ፡፡

‹‹ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ ያሉ ባለሀብቶችን የማበረታታትና የድጋፍ ሥራ ያከናውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ከአገር ውስጥ ጥጥ ከመግዛት የውጭ ጥጥ ይመርጣሉ፤›› በማለት ባለሀብቱ የሚፈጠረውን የጥቅም ግጭት በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ የአገር ውስጥ ጥጥ አምራቾችን እየጎዳ ነበር፡፡ ይህን ለማስቆም እምብዛም ጥረት አልተደረገም፡፡ ስለዚህ ጥጥ ወደ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን መታሰቡ ለሥራው ትኩረት እንዲሰጠው ያደርጋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ጥናቱ ከዚህም በተጨማሪ በጥጥ ምርት መቀነስ፣ በፋይናንስ፣ በጥጥ ግብይት ላይ ያሉ ችግሮች፣ እንዲሁም ከቀረጥና ከታክስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለይቶ አውጥቷል፡፡

ከምርት መቀነስ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር ሲተዳደር የነበረው አራት ሺሕ ሔክታር መሬት የሚሸፍነው የኦሞ ሸለቆ እርሻ፣ በአሁኑ ጊዜ ከጥጥ ልማት መውጣቱን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡

ጥናቱ ከምርታማነት መቀነስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮችንም አንስቷል፡፡ ከጥጥ መዳመጥ ጋር በተያያዘ በዘርፉ ውስጥ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረገው የፋይናንስ እገዛ የተወሰነ መሆን ለዘርፉ ማነቆ እንደሆነም በጥናቱ ተገልጿል፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ የመዳመጫ ፋብሪካዎች በእርጅና ምክንያት እየተዘጉ መሆኑን፣ ያሉትም ከአቅማቸው በታች እያመረቱ በመሆናቸው ችግር መፈጠሩንም ጥናቱ አመልክቷል፡፡

ጥናቱ አያይዞ ለተጠቀሱት ችግሮች የተዘረዘሩ የመፍትሔ ሐሳቦች ተግባራዊ የሚሆኑበትን የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ለችግሮቹ እልባት ለመስጠት ወጥነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ይወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች