የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 የሒሳብ ዓመት 14.6 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡ ተጠቆመ፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ70 ቢሊዮን ብር በማሳደግ ከ359 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ተጠቆመ፡፡
ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ ባለፈው ዓመት አግኝቶ ከነበረው ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡
ንግድ ባንክ ባለፈው የሒሳብ ዓመት (2008) አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ መጠን 13.9 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በ2009 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የትርፍ መጠን ዕድገት ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ዕድገቱ አነስተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡
በ2008 የሒሳብ ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት 13.9 ቢሊዮን ብር ሲያስመዘግብ፣ በ2007 ዓ.ም. ከ12.3 ቢሊዮን ብር በላይ፣ በ2006 ደግሞ 9.7 ቢሊዮን ብር አትርፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ያልተጣራ ትርፍ መጠን ዕድገት በቀዳሚዎቹ ዓመታት በተከታታይ ይታዩ ከነበሩ ዕድገቶች ጋር ሲነፃፀር በተወሰነ ደረጃ ዝቅ ያለ እንደሆነ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያ የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህ አስተያየታቸው በአስረጅነት የሚያቀርቡት ደግሞ ባንኩ ከቀድሞ የኮንስትራከሽንና ቢዝነስ ባንክ ጋር መቀላቀሉን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 88 ቅርንጫፎችን ጨምሮ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ያለውን ሀብት በሥሩ የጠቀለለ መሆኑ የባንኩን አቅም አሳድጎለታል፡፡ ‹‹ይህም ከፍተኛ አቅም ያገኝ የነበረውን የትርፍ መጠን ዕድገት ከፍ ሊያደርግለት ይገባ ነበር፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ባንኩ ከውህደቱ በፊት በየዓመቱ ሲያሳይ የነበረውን የትርፍ ዕድገት እንኳን እንዳላስመዘገበ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ባንኩ በ2009 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የትርፍ ዕድገት ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች መሆኑን ለአብነት ይጠቁማሉ፡፡
አስተያየት ሰጪው በአንድ ዓመት ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ የትርፍ ዕድገት የተመዘገበበት ጊዜ እንደነበር በማስታወስ፣ ‹‹ውህደቱ በባንኩ የትርፍ መጠን ዕድገት ላይ ብዙም ለውጥ አላመጣም፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መዋሀዳቸው ይፋ በተደረገበት ወቅት የንግድ ባንክ ጠቅላላ የሀብት መጠን 310.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ደግሞ 7.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ 5.4 ቢሊዮን ብር፣ ንግድ ባንክ ደግሞ 214.7 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ይዘው መዋሀዳቸውና የኮንስትራክሽን ባንክ ደንበኞች ወደ ንግድ ባንክ እንዲገቡ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ውህደቱ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ማስገኘት በማስቻሉም የባንኩን ዓመታዊ የትርፍ መጠን ዕድገት እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ ነበር፡፡
የባንኩ የትርፍ መጠን ዕድገት ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፡፡ በተለይ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ የታየው ዕድገት ከፍተኛ መሆኑን የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡ በ2002 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ 2.7 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2005 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
ከአገሪቱ ባንኮች በአጠቃላይ አቅሙ ቀዳሚውን ደረጃ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በ2009 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛውን የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመትም 70 ቢሊዮን ብር የሚሆን አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደተቻለ ይጠቁማል፡፡ ይህም በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ359 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንዳስቻለው መረጃው ያስረዳል፡፡
ቀደም ያሉ የባንኩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2003 ዓ.ም. የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 55 ቢሊዮን ብር፣ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ 241.7 ቢሊዮን ብር፣ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ 46.8 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 288.5 ቢሊዮን ብር በማድረስ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን አሳድጓል፡፡ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት በተከታታይ እየጨመረ እንዲመጣ ከረዱ ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚቀመጠው የአስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር ማሳደጉ ነው፡፡
በተለይ ከ2002 ዓ.ም. ወዲህ የታየው የአስቀማጮች ቁጥር መጨመር የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን እንዳሳደገለት ይታመናል፡፡ ባንኩ በ2003 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን ያነሰ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም 55 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
ይህ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር በ2007 ደግሞ የሒሳብ ዓመት ደግሞ 10.7 ሚሊዮን፣ በ2008 የሒሳብ ዓመት 13.3 ሚሊዮን በማድረስ፣ በተጠናቀቀው በ2009 ዓ.ም. ደግሞ 15 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ በ2002 ዓ.ም. 220 የነበረውን የቅርንጫፎች ቁጥር በ2009 ዓ.ም. ከ1,300 በላይ ማድረስ ችሏል፡፡
ንግድ ባንክ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን (ከ2002 እስከ 2007) በድምሩ 42.8 ቢሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት አጠቃላይ የትርፍ መጠኑ 27.5 ቢሊዮን መድረሱን የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡