Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመኢአድ አመራር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሱ

የመኢአድ አመራር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሱ

ቀን:

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራር የነበሩትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለሌሎች አመራሮች ጋር በተፈጠረ ልዩነት ከአባልነት የራቁት አቶ ማሙሸት አማረ፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

አቶ ማሙሸት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን ተላልፈው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማሴር መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. መልምለው ያደራጇቸውንና በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን አስተባብረው፣ በአማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች የሽብር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ማዘጋጀታቸውን በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት ኃላፊነት ወስደው እንቅስቃሴውን ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ለመምራት ኬንያ ለመሄድ ሞያሌ ከተማ እንደገቡ፣ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም.  በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ ገልጿል፡፡

ተከሳሹ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አባል አማካይነት እንደተመለመሉ የሚገልጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ተልዕኮ በመቀበል ከቡድኑ በሚላክላቸው ገንዘብ የጦር መሣሪያ በመግዛትና ማሠልጠኛ በማመቻቸት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረውን ሁከት እንዲቀጥል ሲያደርጉ እንደነበር ገልጿል፡፡

በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በምርጫ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ማስወገድ እንዲቻል፣ በውጭና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር የሽብር ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አባላት በመመልመልና በማደራጀት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ እንዲልኩም ተልዕኮ እንደተሰጣቸው አክሏል፡፡

ተከሻሹ በ2007 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ለቡድኑ አባላትን መልምለውና ወታደራዊ ቤዝና ማሠልጠኛ ወዳላት ኤርትራ በሁመራ በኩል መላካቸውን፣ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ከተለያዩ አካባቢዎች 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሰብስበው መንግሥትን ከሥልጣን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝባዊ አመፅ መሆኑን፣ አመጽ ለመፈጸም ደግሞ የጦር መሣሪያ ስለሚያፈልግ እያንዳንዱ አባል ሌላ አባላት በመመልመል፣ በማደራጀትና በማስፋፋት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል አንዱን ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ ማድረግ እንዳለባቸው ተልዕኮ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

ተከሳሹ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ውስጥ ለሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ቤዝ የሚሆን ቦታ በመምረጥ፣ ከደብረ ብርሃንና አዲስ አበባ የተመለመሉ ዘጠኝ አባላትን ወደ ማሠልጠኛ በመላክ ሥልጠና ማስጀመራቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. አቶ ማሙሸት ዘመነ ምሕረቱ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አመራርና ለገሰ ወልደሀና ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመሰብሰብ፣ በጎንደር ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ሰሜን ሸዋ ጫካ ውስጥ በመግባት፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲደርስ ተልዕኮ መስጠታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ አቶ ማሙሸት የሽብርተኛነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የማቀድ፣ የመዘጋጀት፣ የማሴርና የማነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ቀረቦባቸዋል፡፡ ተከሳሹ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆኑ፣ በግላቸው ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...