Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየለንደን ዝግጅትና የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሞክሮ

የለንደን ዝግጅትና የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሞክሮ

ቀን:

የሁለት ቀናት ዕድሜ የቀረው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዳዲስ ክስተቶችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ከዓለም ድንቅ አትሌቶች መካከል ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት የውድድር ዘመኑ ማጠናቀቂያና የ5,000 እና 10,000 ሜትር ተፎካካሪው ሞ ፋራ የመሞ የሩጫ መቋጫ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ከሐምሌ 28 እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በለንደን ከተማ በሚሰናዳው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችና ልዑካኖች ሐምሌ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡ በነባርና በአዲስ አትሌቶች የተዋቀረው ብሔራዊ ቡድኑ ካለፈው ጊዜ በተሻለ መልኩ ውጤት ሊያስመዘግብ እንደሚችል እየተገለጸ ይገኛል፡፡

በተለይ በወንዶች ማራቶን አገሩን የወከለው ታምራት ቶላ፣ በሴቶች 5,000፣ 10,000 ሜትር አልማዝ አያና፣ በ1,500 እና 5,000 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ፣ በሴቶች ማራቶን የሪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ማሬ ዲባባ ግምት ከተሰጣቸው  ውስጥ ይመደባሉ፡፡ 14 የለንደን ስታዲየሞች ለሻምፒዮናው የተዘጋጁ ሲሆን፣ 660 ሺሕ ትኬቶች ለተመልካቾች መሸጣቸው ተገልጿል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር አማካይነት በ1975 (1983) ዓ.ም. ሲጀመር በአራት ዓመት ውስጥ ለማካሄድ ነበር፡፡ የመጀመርያዎቹ ሻምፒዮናዎች በ1975 እና በ1979 ዓ.ም. ከተካሄዱ በኋላ ከሦስተኛው ሻምፒዮና ጀምሮ በየሁለት ዓመት እየተካሄደ ዘንድሮ 16ኛው ላይ ደርሷል፡፡

የ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማዘጋጀት በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማኅበር (አይኤኤፍ ኮሚሽን) ለንደንና ኳታር ላይ ግምገማ ያካሄደ ሲሆን፣ ሁለቱን ተፎካከሪዎች ለመለየትም በሁለቱም አገሮች ጉብኝት በማድረግ እ.ኤ.አ. በ2011 ላይ ለንደን እንድታሰናዳ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ከሐምሌ 22 ቀን ጀምሮ ወደ ከተማዋ እየገቡ ያሉት አትሌቶች ቁጥር ከሁለት ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ ከ200 በላይ አገሮችም ተሳታፊ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ግንቦት ወር ላይ የሜዳሊያ ዓይነቱን ለሕዝብ ያሳወቀችው ለንደን በሜዳሊያው ዲዛይን ውስጥ የመሮጫ ትራክና በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችን ያካተተ ነው፡፡  የሜዳልያ ዲዛይኑም ለፖራሊምፒክ ውድደሮችም እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሞንዶ ትራክ የተሰኘ የቅርብ ጊዜ የመም ዓይነት በስታዲየሞቹ እንዳስገጠመችና ለአትሌቶቹም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር አዲስ ፈጠራን ማካተት ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል አትሌቶቿን አበረታች ንጥረ ነገር በመጠቀማቸው ከዓለም አቀፍ ውድድሮች የታገደችው ሩሲያ 47 አትሌቶቿ ንፁህ መሆናቸው ስለተረጋገጠ በግላቸው መሳተፍ እንደሚችሉም ሌላኛው በሻምፒዮናው የተካተተ ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የነበራት ተሳትፎና ያገኘችው ውጤት  እ.ኤ.አ. 1983 ሄሊሲንኪ ላይ ከበደ ባልቻ በማራቶን ብር ያመጣበትና በአፍሪካ አንደኛና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰንጠረዥ 15ኛ ደረጃ የያዘችበት ይታወሳል፡፡

እንዲሁም እ.ኤ.አ. 2001 በካናዳ ኤድመንተን በተከናወነው ስምንተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ገዛኸኝ አበራ በማራቶን 2፡12፡52 በመግባት ወርቅ፣ ደራርቱ ቱሉ በ10,000 ሜትር 31፡48.81 ወርቅ በማምጣት፣ ሚሊዮን ወልዴ በ5,000 ሜትር፣ አሰፋ መዝገቡ በ10,000 ሜትር፣ ብርሃኔ አደሬ በ10,000 ሜትር ብር በማምጣት፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ 10,000 ሜትር፣ አየለች ወርቁ በ10,000 ሜትርና ጌጤ ዋሚ በተመሳሳይ ርቀት ነሐስ በማምጣት በአጠቃላይ ስምንት ሜዳሊያ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝና ከዓለም ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትውስታዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 ቤጂንግ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ 1,500 ሜትር ርቀቱን 4፡08፡09 በማጠናቀቅ ወርቅ፣ አልማዝ አያና በ5,000 ሜትር 14፡26.83 የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን በመስበር ጭምር ወርቅ በማምጣትና ሌላኛዋ  አትሌት ማሬ ዲባባ በማራቶን ውድደር 2፡27፡35 በማጠናቀቅ ወርቅ ያመጡ እንስቶች ናቸው፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያ 3 ወርቅ 3 ብርና 2 ነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያ በማምጣት አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡

በዘንድሮ የምታስመዘግበው አጠቃላይ ውጤት ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ በምታከናውነው ውድድር መልስ የሚያገኝ ይሆናል፡፡

ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን በሚጀምረው 16ኛው የዓለም ሻምፒዮና የወንዶች የ10,000 ሜትር ፍጻሜ የሚካሄድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑ አባዲ ሐዲስ፣ ጀማል ይመርና አንዱዓለም በልሁ በተፎካካሪነት ይጠበቃሉ፡፡ እንዲሁም ማታ 1፡35 ላይ በ1,500 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ ገንዘቤ ዲባባ፣ ጉዳፍ ፀጋዬ፣ በሱ ሳዶና ፋንቱ ወርቁ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

በሌላ መርሐ ግብር መሠረት ሐምሌ 29 የሴቶች 10,000 ሜትር ፍጻሜ አልማዝ አያናና ደራ ዲዳ ተጠባቂ ናቸው፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...