Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሁለገቡ ኪነ ጥበበኛ ተስፋዬ ሳህሉ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል

የሁለገቡ ኪነ ጥበበኛ ተስፋዬ ሳህሉ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል

ቀን:

በኢትዮጵያ የኪነ ጥበባት መድረክ ለአምስት አሠርታት በሁለገብ ባለሙያነት ያገለገሉት ተስፋዬ ሳህሉ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በ9 ሰዓት ይፈጸማል፡፡

ኪነ ጥበበኛው ተስፋዬ ሳህሉ በብዙዎች እንደሚታወቁት ‹‹አባባ ተስፋዬ›› ሁለገቡ ያሰኛቸው ተዋናይ፣ ድምፃዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ ገጣሚና ዜማ ደራሲ፣ የተረት መጻሕፍት አዘጋጅ ሆነው በጥበቡ ዓለም መዝለቃቸው ነው፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) በ1948 ዓ.ም. ሲቋቋም ከመጀመሪያዎቹ ባለሙያዎች አንዱ የነበሩት ተስፋዬ ሳህሉ ቀዳሚው ሥራቸው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሲሆን በትወና፣ በመድረክ መሪነትና በሙዚቀኛነት መሥራታቸው ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡

የሙዚቃ መሣሪያዎች ክራር፣ መሰንቆ፣ ዋሽንት፣ በገና፣ ፒያኖ፣ አኮርዲዮንና ትሮምቦን ይጫወቱ የነበሩት ተስፋዬ ‹‹አንቺ ዓለም››፣ ‹‹አንድ ጊዜ ሳሚኝ›› እና ‹‹ሰው ሆይ  ስማ››  ካዜሟቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በትወና ረገድ፣ ሴት ተዋንያት ባልነበሩበት ወቅት እንደ ሴት ሆነው በ‹‹ጎንደሬው››፣ ‹‹መቀነቷን ትፍታ›› እና ‹‹ጠላ ሻጭ›› የሴት ገጸ ባሕሪ ተላብሰው ከተጫወቱባቸው ተውኔቶች መካከል ናቸው፡፡ በተለያዩ ታላላቅ ተውኔቶች በ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹ኤዲፐስ ንጉሥ››፣ ‹‹ኦቴሎ››፣ ‹‹አሉላ አባነጋ›› ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› ጨምሮ እና የሌሎችን ተውነዋል፡፡

በ1950ዎቹ በነበረው የኮሪያ ጦርነት ለኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቃ ሠራዊት ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በኮሪያ በመገኘት ካቀረቡት አንዱ የነበሩት ተስፋዬ ሳህሉ የአሥር አለቃነትን ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በኮሪያ የቀሰሙት የምትሀት ጥበብ በኢትዮጵያ ያገኙት አይሁዳዊ አሠልጣኝ አጠናክሮላቸው፣ አስደናቂ ትርዒቶች ማሳየት ችለው ነበር፡፡ በአንድ ወቅትም የዓለም አቀፍ ምትሀተኞች ማኅበር አባልም ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ በ1957 ዓ.ም. ሲመሠረት በልጆች ክፍለ ጊዜ በማኅበረሰቡ የሚወደዱ ታዋቂ ተረቶችን በአዲስ መልክ እያቀረቡ ከ40 ዓመታት በላይ አስተምረዋል፣ አዝናንተዋል፡፡ ተረቶቻቸውንም በመጽሐፍና በሲዲም አሳትመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከ36 ዓመት አገልግሎት በኋላ ጡረታ የወጡት ተስፋዬ ሳህሉ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ጊዜ አገልግሎታቸው ከ1998 ዓ.ም. በኋላ ማለፍ አልቻለም፡፡

በቀድሞው አጠራር በባሌ ጠቅላይ ግዛት በሰኔ 1916 ዓ.ም. የተወለዱት ኪነ ጥበበኛው ተስፋዬ ሳህሉ፣ ከትውልድ ስፍራቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በኪነ ጥበባት ዘርፍ ላደረጉት አስተዋጽኦ ከዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት በተወካያቸው አማካይነት ያገኙት ተስፋዬ ሳህሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባቸው ሕመም በ93 ዓመታቸው ያረፉት ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ስመ ጥሩው ተዋናይ ተስፋዬ የአንድ ልጅ አባትና አምስት የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...