Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ አደረጃጀት በኤርፖርት ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የሆልዲንግ ኩባንያ መመሥረቻ ሕግ እየተረቀቀ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ አቪዬሽን ቡድን ሥር ተናበው እንዲሠሩ መንግሥት የወሰነው ውሳኔ፣ በኤርፖርት አገልግሎት ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኤርፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመመሥረት ላይ ያለው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ቡድን አየር መንገዱን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጀትና ሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ድርጅት የሚያቅፍ ነው፡፡ ይህም የአቪዬሽን ቡድኑ የተቀናጀ የአየር ትራንስፖርት፣ የኤርፖርት አገልግሎትና የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎቶች መስጠት ያስችለዋል ብለዋል፡፡

አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰባት የትርፍ ማዕከላት በመያዝ ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆኑ ዋና መናኸሪያው ከሆነው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ያለው አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ መንግሥት አየር መንገዱና ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ አቪዬሽን ቡድን ሥር ተባብረውና ተናበው እንዲሠሩ መወሰኑ፣ በኤርፖርት አገልግሎት ዘርፍ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚያስችል በመሆኑ መደሰታቸውን አስረድተዋል፡፡  

የአቪዬሽን ቡድኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ፣ የአቪዬሽን አካዳሚ፣ የጥገና ማዕከል፣ ግራውንድ ሃንድሊንግና የበረራ ምግብ ዝግጅት ክፍሎችን አቅፎ በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል እንዲቋቋም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ወስኗል፡፡

የአቪዬሽን ቡድኑ በሒደት ወደ ሆልዲንግ ኩባንያ እንደሚያድግ ተገልጿል፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ የሆልዲንግ ኩባንያ ማቋቋሚያ አንቀጾች የሌሉት በመሆኑ፣ መንግሥት በዚህ ላይ እየሠራ እንደሆነ አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ዘርፎች የሚያገለግል የሆልዲንግ ኩባንያ መመሥረቻ ሕግ እየተዘጋጀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ተወልደና የስታር አሊያንስ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ጄፍሬይ ጐህ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አቶ ተወልደ ስታር አሊያንስ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ለአባል አየር መንገዶቹና ደንበኞቹ የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥበትን ማዕከል ማቋቋም እንደሚፈልግ ገልጸው፣ ኤርፖርቱ የስታር አሊያንስ ደረጃዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤርፖርቱ ሕንፃ ብቻ ላይ ሳይሆን በአገልግሎቶች ላይና በቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈስ ተናግረዋል፡፡ በኤርፖርት አገልግሎት አሠራሮችና ደንበኞች ላይ ለውጥ በማምጣት የመንገደኞችን ቆይታ አስደሳች እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ የሚደረጉት የአሠራር ለውጦች ሌሎች አየር መንገዶችና ባለድርሻ አካላት ሁሉ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

አንዳንድ የአቪዬሽን ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ አቪዬሽን ቡድን ሥር እንዲተዳደሩ መወሰኑ ሥጋት እንደፈጠረባቸው መግለጻቸውን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አቶ ተወልደ እንደሚሉት ግን ሥጋቱ የተፈጠረው አዲስ ስለሚቋቋመው አቪዬሽን ቡድን ትክክለኛ መረጃ ስላልደረሳቸው ነው፡፡

‹‹ኤርፖርቶች ድርጅት ከአየር መንገዱ ጋር አይዋሀድም፡፡ የራሱን ማኔጅመንት ይዞ በአቪዬሽን ቡድኑ ውስጥ ከአየር መንገዱ ጎን ለጎን ይሠራል፡፡ ሁሉንም ወገን ያለምንም ልዩነት እኩል ያገለግላል፤›› ብለዋል አቶ ተወልደ፡፡

በአገሪቱ በእንጭጭ ደረጃ ላይ የሚገኘው የጄኔራል አቪዬሽን ዘርፍም እንዲያድግ እንደሚፈለግ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ ደረጃውን የጠበቀ ኤርፖርት ለጄኔራል አቪዬሽን የተለየ የአውሮፕላን መንደርደሪያና የመንገደኛ ማስተናገጃ ሕንፃ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የጄኔራል አቪዬሽን ዘርፍ ቢያንስ በኬንያ ካለው ጄኔራል አቪዬሽን ዘርፍ የሚስተካከል መሆን ይገባዋል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት የጄነራል አቪዬሽን ኦፕሬተሮች የተሻለ መሠረተ ልማትና አገልግሎት እንደሚያገኙ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ ለዕድገት የተሻለ ዕድል ይኖራቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

አየር መንገዱና ኤርፖርቶች ድርጅት አንድ ላይ መሆን የለባቸውም ለሚለው አስተያየት በሰጡት ምላሽ፣ በተለያዩ አገሮች የተለያየ አሠራር እንዳለ አስረድተዋል፡፡ በአሜሪካ ኤርፖርቶች በባለቤትነት የያዟቸው የከተሞች አስተዳደሮች እንደሆኑና ተርሚናሎቹ በረዥም ጊዜ ለዋና ዋና አየር መንገዶች በኪራይ እንደተላለፉ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በአውሮፓ የኤርፖርት ኩባንያዎች ገለልተኛ የግል የንግድ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ አንዳንድ አየር መንገዶች በኩባንያዎቹ ላይ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው፡፡ አቶ ተወልደ እንደ ዋነኛ ማሳያ የጠቀሷቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ኤርፖርቶችን ነው፡፡ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የዓለም የአቪዬሽን ማዕከል ከአውሮፓ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲዞር ማድረግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አቡዳቢ፣ ዱባይና ዶሃ የአቪዬሽን ገበያውን ከአውሮፓ ሊቀሙ የቻሉት፣ የተለያዩ የአቪዬሽን ዘርፎችን አቀናጅተው በአንድ ላይ መምራት በመቻላቸው ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ በዶሃ ሃማድ ኢንተርናሽናል ኤርፖርትና ኳታር ኤርዌይስ በኳታር አቪዬሽን ቡድን ሥር እንደሚተዳደሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹በዱባይም ተመሳሳይ አሠራር ነው ያለው፡፡ እኛ አዲስ ነገር እየፈጠርን አይደለም፡፡ በሌሎች አገሮች ያለ አሠራር ወስደን ሊያሳድገንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሊያደርገን በሚችል መንገድ አደረጃጀታችንን እየለወጥን ነው፡፡ በየዕለቱ እየጠነከረ የመጣውን ውድድር ማሸነፍ ካለብን ቤታችንን ማስተካከል አለብን፡፡ የአየር መንገዱ ፈጣን ዕድገት በዋና መናኸሪያችን ባሉ ችግሮች ምክንያት መስተጓጎል የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ባለፈው ሳምንት የጎበኙት የስታር አሊያንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጄፍሬይ ጐህ የአቶ ተወልደን ሐሳብ ደግፈዋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ካለ የኤርፖርት ባለቤትነት ጥያቄ አሳሳቢ እንደማይሆን ጄፍሬይ ጐህ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አቶ ተወልደ እንዳሉት በዶሃ ኤርፖርቱና ኳታር ኤርዌይስ የሚተዳደሩት በአንድ አቪዬሽን ቡድን ነው፡፡ ኳታር ኤርዌይስ በሂትሮ ኤርፖርት 20 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አለው፡፡ በአውሮፓ ያሉ የስታር አሊያንስ አባሎቻችን በኤርፖርት ኩባንያዎች ላይ አክሲዮን ይገዛሉ፡፡ የገቢ ምንጮችን ለማስፋት አየር መንገዶች በኤርፖርትና በመሰል ተቋማት ላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ፣ ይህ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ዋናው ነገር የኃላፊነት ክፍፍል፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሚስተር ጐህ ኳታር ኤርዌይስ በሂትሮ ኤርፖርት ላይ 20 በመቶ ድርሻ ስላለው በኤርፖርት ኩባንያው ሥራ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኤርፖርት ኩባንያው ለመንገደኞችና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተጠያቂ በመሆኑ ለአንድ ባለ አክሲዮን መወገን አይችልም፤›› ያሉት ጐህ፣ ተፅዕኖ የሚኖር ከሆነ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሥርም በሚተዳደሩበት ወቅት ሊከሰት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ስታር አሊያንስ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ለአባል አየር መንገዶች የጋራ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ለማቋቋም ማቀዱን ገልጸው፣ አየር መንገዱና ኤርፖርቶች ድርጅት በአንድ አቪዬሽን ቡድን ሥር መተዳደራቸው ሥራውን እንደሚያቀለው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች