Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የመኪና ጎማን ከብልሽት የሚታደግ አዲስ ቴክኖሎጂ ለገበያ ቀረበ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በዓመት ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለጎማ ግዥ እንደሚውል ይገመታል

  ምንጩ ከእንግሊዝ የሆነ፣ ታየር ፕሮቴክተር ሲላንት የተባለና ከ14 የዕፅዋት ዓይነት እንደተቀመመ የተነገረለት ድርድር ፈሳሽ በመኪና ጎማ እየተሞላ ከመፈንዳትና ከመተንፈስ ጉዳት የሚከላከል ብሎም በጎማ ብልሽት ምክንያት የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን ከመቀነስ አኳያ ጠቀሜታው እንደሚጎላ የታመነበት ቴክሎጂ ለገበያ ቀረበ፡፡

  ቴክኖሎጂውን የፈበረከው ታየር ፕሮቴክተር ኢንተርናሽናል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ሲሆን፣ ወደ አገር ቤት ማስመጣት የጀመረው ደግሞ ታየር ፕሮቴክተር ኢትዮጵያ የተባለው የግል ድርጅት መሆኑ ታውቋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ ስለቴክሎጂው ለአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲያስተዋውቁ፣ ቴክኖሎጂው ለጎማ ዕድሳት ከሚወጣው ወጪ ውስጥ እስከ 75 በመቶ እንደሚያስቀር አስታውቀዋል፡፡ በዋናው አውቶቡስ ተራ መናኸሪያም ስለቴክኖሎጂው ጠቀሜታዎች በተግባር አሳይተዋል፡፡

  ከመነዳሪ በሌላቸው ጎማዎች ውስጥ በተሞላው መከላከያ ፈሳሽ ሳቢያ፣ ተሽከርካሪዎች ጣውላ ላይ በተመቱ ትልልቅ ሚስማሮች ላይ ተነድተው ጎማቸው ቢበሳም ሳይፈዳና ሳይተነፍስ እንደቀድሟቸው ያለ ችግር ሲሽከርከሩ አሳይተዋል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በቤት አውቶሞቢል ጀምሮ እጅግ ግዙፍ ለሆኑ የግንባታ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች እንደሚውል ተገልጿል፡፡

  እንደ ጄኔራል ባጫ ማብራሪያ፣ የታየር ፕሮቴክተር ጠቃሜታዎች ከሚባሉት ውስጥ ጎማ እንዳይተነፍስ፣ በሙቀት የተነሳ ተለጥጦ ጥንካሬውን እንደያጣ እንዲሁም በከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያትም እንዳይኮማተር በመከላከል የጎማውን ዕድሜ ይጨምራል፡፡ ከዚህም ባሻገር በስለታም ድንጋይ፣ በሚስማርና በማናቸውም ስለታም ነገሮች የተወጋ ጎማ እንዳይተነፍስ ከማድረግ ባሻገር የተወጋውን ክፍል በፍጥነት በመጠገን የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይሰተጓጎል የሚያስችል ነው፡፡ ቴክሎጂው በቀላል ተሽከርካሪዎች ጎማ ላይ እስከ ስድስት ሚሊ ሜትር፣ በከባድ ተሽከርካሪዎች ጎማ ላይ ደግሞ እስከ 12 ሚሊ ሜትር ስፋት ያለውን ቀዳዳ በፍጥነት የመድፈን አቅም እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ለጎማ ጥገና በየጊዜው ከሚወጣው ወጪ እስከ 75 በመቶ እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡

  ለአንዱ ሊትር የጎማ መከላከያ ከ1,000 ብር በታች እንደሚሸጥ ያስታወቁት ጄኔራል ባጫ፣ ቴክኖሎጂው በአገሪቱ በሚገኙ ጎሚስታዎችና በወኪል አከፋፋዮች በኩል እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡ ቴክኖሎጂው እስኪለመድና አጠቃቀሙ በአግባቡ እስኪታወቅ ድረስ በኩባንያው የሠለጠኑ ባለሙያዎች አማካይነት በመኪኖች ጎማ ውስጥ እንደሚሞላ ጄኔራሉ ጠቅሰዋል፡፡

  የታየር ፕሮቴክተር ኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሚ ሚሊዮን በበኩላቸው፣ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ለዓመታት በማጥናት ለውጤት ያበቁት ይህ ቴክኖሎጂ ለገበያ መቅረብ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2005 ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከ80 በላይ አገሮች እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካም ግብፅ፣ ጋና፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ታንዛኒያ፣ አንጎላ፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በናይጄሪያ ጥቅም ላይ የዋለው ይህ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ በታየር ፕሮቴክተር ኢትዮጵያ አማካይነት እንደሚሠራጭ አስታውቀዋል፡፡

  ለመነሻ ያህልም በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ለ30 ሺሕ መኪኖች የሚዳረስ አቅርቦት እንደሚመጣ የተገለጸ ሲሆን፣ ቅድሚያውን ከሚያገኙት መካከል የግንባታ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት እንደሆኑም ጄኔራል ባጫና አቶ ሳሚ አስታውቀዋል፡፡ 

  አቶ ሳሚ ከዚህ ቀደም በእንግሊዙ ኩባንያ ውስጥ መሥራታቸውን የጠቀሱት ጄኔራሉ፣ በዚያ ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም በኢትዮጵያም ምርቱን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ወደፊት ምርቱ እዚሁ ተቀነባብሮ ለገበያ የሚቀርብበት ሐሳብ እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡ ድርድር ፈሳሽ የሆነውና የማጣበቅ ባህርይ ያለው የጎማ መከላከያ፣ በሰውም ሆነ በአካባቢ ላይ ምንም ጉዳት እንደማያደርስ፣ ከኬሚካል ነፃ እንደሆነ ለማስረዳትም በምላሳቸው በመቅመስ ለታዳሚው አሳይተዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን በመኪና ጎማ ውስጥ ለመሙላት አሥር ደቂቃ ብቻ እንደሚጠይቅ፣ የሚሞላውም መኪናው ላይ በተገጠመ ጎማ ውስጥ ብቻ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ የተሞላው መከላከያም እስከ ጎማው የአገልግሎት ዘመን ማብቂያ ድረስ እንደሚያገልግል ተነግሯል፡፡ ሳይበላሽ የሚቆይ መሆኑም ለየት እንደሚያደረገው ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ሳሚ ማብራሪያ ከሆነ፣ ለቤት አውቶሞቢሎች ለአራቱም ጎማዎች የሚሞላው መጠን አንድ ሊትር እንደሆነ ሲገመት፣ ለትልልቅ መኪኖች ሁለት ሊትር፣ ለትልልቅ የግንባታ መኪኖች እስከ አራት ሊትር እንዲሁም ግዙፍ ለሆኑ የመስክ ተሽከርካሪና ማሽነሪ ጎማዎች እስከ ስምንት ሊትር መጠቀም እንደሚመከር ተጠቅሷል፡፡ 

  የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ መሥሪያ ቤቶቹ የሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ አውቶቡሶቹ (በተለምዶ ቢጫዎቹ አውቶቡሶች ለሚባሉት) በሙሉ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም መስማማቱ ተጠቅሷል፡፡

   በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የተሽከርካሪ መጠን የ30 በመቶ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ ያሉት የኩባንያው ኃላፊዎች፣ ቴከሳይ የተባለ የምርምር ተቋም በየካቲት ወር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2022 ጀምሮ ኢትዮጵያ በየዓመቱ የ180 ሚሊዮን ዶላር የጎማ ግዥ እንደምትፈጽም መተንበዩን ጠቅሰዋል፡፡

  በእንግሊዙ ኩባንያና በኢትዮጵያውያን የታየር ፕሮቴክተር ድርጅት መሥራቾች መካከል ከሦስት ዓመታት በፊት በተደረገ የፍራንቻይዝ ስምምነት መሠረት በሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው አገር በቀሉ ኩባንያ፣ በጎማ ጥገና የተሰማሩትን ጨምሮ ወደፊት ከ30 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጄኔራል ባጫ ተናግረዋል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች