Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግማሽ ቢሊዮን ብር የማስፋፊያ ግንባታ ያቀደው ናሽናል ሲሚንቶ ለድሬዳዋ ሕዝብ አክሲዮን እንደሚሸጥ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር፣ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የፋብሪካውን የባለቤት ድርሻ ለመጋራት የሚያስችለው የአክሲዮን ሽያጭ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡ አዲስ የማስፋፊያ ግንባታ እንደሚጀምር ገለጸ፡፡

ናሽናል ሲሚንቶን ጨምሮ ሌሎች ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ መሥራችና ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ በኩባንያው ዓመታዊ በዓል ላይ እንዳስታወቁት፣ የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ባለቤትነት ድርሻን መሠረት ለማስፋት በማሰብ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ለመሸጥ ያቀደውን አክሲዮን በቅርቡ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ኩባንያቸው የድሬዳዋና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማቀድ በቅርቡ የሚያካሂደው የአክሲዮን ሽያጭ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለባለሀብቶችም እንደሚሸጥ ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በድሬዳዋ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ወቅት አቶ ብዙአየሁ አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ኩባንያው ምን ያህል አክሲዮኖችን ለድሬዳዋና ለአካባቢዋ ማኅበረሰብ እንደሚሸጥ ይፋ ያላደረገ ሲሆን፣ ኩባንያው ከነበረበት ችግር ወጥቶ ወደ አትራፊነት መሸጋገሩን ይፋ ባደረገበት ማግሥት የናሽናል ሲሚንቶን የባለቤትነት መሠረት ለማስፋት ተብሎ የተወሰነው የአክሲዮን ሽያጭ፣ የፋብሪካው ሠራተኞችንም እንደሚያሳትፍ ከአቶ ብዙአየሁ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ወደ አትራፊነቱ የመጣው ናሽናል ሲሚንቶ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አክሲዮን ለመሸጥ ማቀዱ የፋብሪካው የባለቤትነት ስሜት በሕዝቡ ዘንድ እንዲንሠራፋ ከማድረጉም በላይ፣ ሕዝቡ የትርፉ ተቋዳሽ እንዲሆን ታስቦበት የተደረገ እንደሆነም በክብረ በዓሉ ወቅት ተገልጿል፡፡

ፋብሪካው በ2009 ዓ.ም. ወደ 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ እንዳገኘ የሚገልጹት የኩባንያው ኃላፊዎች፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ 450 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት እንዳቀደም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ የአክሲዮን ሽያጭ ጎን ለጎን የፋብሪካውን የማምረት አቅም ለማሳደግ የማስፋፊያ ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ የማስፋፊያ ሥራውን በተመለከተ የኩንያው መረጃ እንደሚያመላክተውም፣ የማስፋፊያ ግንባታው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ተብሎ ይገመታል፡፡

የፋብሪካውን የማምረት አቅም ዕውን ለማድረግ የረዥም ጊዜ ራዕያችን ነበር ያሉት አቶ ብዙአየሁም፣ የፋብሪካውን የማምረት አቅም ለማሳደግ በተደረገው ጥናት በቀን 3,500 ቶን የማምረት አቅም ወደ 5,000 ቶን ለማሸጋገር ያስችላል ብለዋል፡፡ በዚህ ወር ተጀምሮ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ትልልቅ የሰሚንቶ ፋብሪካ አንዱ ሊያደርገው እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመንፈስ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የማስፋፊያ ግንባታው አዳዲስ የሲሚንቶ ምርቶችን ለማውጣት የሚያስችል ዕድል ይፈጥርለታል፡፡

በ2009 ዓ.ም. 826,500 ቶን ክሊንከር ለማምረት አቅዶ 835,855 ቶን ክሊንከር እንዳመረተ የሚገልጸው የኩባንያው መረጃ፣ በዛው ዓመት 923,339 ቶን ሲሚንቶ መሸጡንም ያስረዳል፡፡

በተለይ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የኢንዱስትሪና የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ከመደገፍ በተጨማሪ ምርቱን ወደ ጎረቤት አገሮች በስፋት ለመላክ ያስችላል ተብሏል፡፡

ፋብሪካው በእስካሁኑ ጉዞው በየዓመቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም. አምስት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ ምርቱን ለሶማሊያና ለጂቡቲ አቅርቧል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ ወደ ሁለቱም አገሮች ከተላከው ሲሚንቶ 8.8 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አቶ ዘመንፈስ ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ፋራህ እንደገለጹት፣ ፋብሪካው ለድሬዳዋ ከተማ አበርክቷል ያሉትን ዕገዛና ድጋፍ አትተው አሁንም ያቀዷቸውን ዕቅዶች ለማሳካት አስተዳደሩ እንደሚደግፋቸው አረጋግጠዋል፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የምርት ግብዓቶች በሚገኙበት አካባቢ እየተካሄደ ያለው ሕገወጥ የቤቶች ግንባታ እንዲቆምላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፣ የከተማው አስተዳደር መፍትሔ እንደሚሰጠው ከንቲባው ቃል ገብተዋል፡፡

ቀድሞ ድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ እየተባለ ይጠራ የነበረውን ፋብሪካ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በመግዛት የጠቀለለው በ1997 ዓ.ም. ነበር፡፡ ፋብሪካውን ለማስፋትና ለማጠናከር እስካሁን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ ጠቅላላ ሀብቱም 4.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከ1,300 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የካይዘን ሥርዓትን በመተግበር ዓመታዊ የምርት መጠኑን በማሳደግ ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በሥሩ የሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች ከ6,330 በላይ ሠራተኞችን የያዙ ሲሆን፣ በዓመት 370 ሚሊዮን ብር ለሠራተኞች ደመወዝ ወጪ የሚያደርጉ ኩባንያዎችን ያሰባሰበ የንግድ ተቋም እንደሆነም ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ብዙአየሁ በቅርቡ በፎርብስ መጽሔት ሚሊየነሮች ተርታ ስማቸው ከሠፈሩ አምስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች