በቀንጢጫ የሚገኙትን የታንታለምና ሊቲየም ማዕድናት በጋራ ከኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ጋር በማልማት እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ማምረቻ ፋብሪካዎችን ሊገነቡ የሚችሉ አጋር ኩባንያዎችን ለመምረጥ የሚያስችል ግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በዝግጅት ላይ እንደሆነ ታወቀ፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጉጂ ዞን፣ ሰባ ቦሩ ወረዳ ልዩ ስሙ ቀንጢቻ በተባለ አካባቢ የታንታም ኮንሰንትሬት በማምረት ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጥሬ ታንታለም ወደ ውጭ ከመላክ አጣርቶ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች እየተመረቱ ኤክስፖርት ቢደረግ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ በመታመኑ፣ እሴት የታከለባቸው ምርቶች ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ታቅዷል፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ሲያመርት የነበረው ታንታለም ኮንሰንትሬት ብቻ ነው፡፡ በቅርቡ በተካሄደው ጥናት ከታንታለሙ ጋር በተጓዳኝ ከፍተኛ መጠን ያለው የሊቲየም ማዕድን መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡
የታንታለም ማዕድን የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስና የሕክምና መሣሪያዎች ለማምረት የሚውል ሲሆን፣ የሊቲየም ማዕድን የሊቲየም ባትሪዎች ለማምረት በግብዓትነት ያገለግላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሊቲየም ባትሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ በመሆኑ፣ የሊቲየም ማዕድን ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡
ዕድሜ የተጫናቸውን የቀንጢቻ የታንታለም ማምረቻ መሣሪያዎች በአዲስ ማሽኖች በመተካት፣ ሻኪሶ አካባቢ የታንታለምና የሊቲየም ማዕድናት ማጣሪያና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ማምረቻ ሁለት ፋብሪካዎች ለመገንባት መታቀዱን አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከታንታለም ማዕድን የሞባይል ስልኮችን ክፍሎችና የኮምፒዩተር ቺፒሶች ማምረት እንደሚቻል የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ ልምዱና የፋይናንስ አቅም ካላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለመሥራት መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡ የሁለቱ ፋብሪካዎች ጠቅላላ ወጪ 500 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡
ከማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርና ከማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን የተውጣጣ ኮሚቴ የቴክኒክ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ጨረታውን በቅርቡ እንደሚያወጣ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የታንታለም ማውጫውን በከፊል ወደ ግል ለማዞርና የታንታለም እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች በሽርክና ለማልማት የሚችል አጋር ኩባንያ ለማፈላለግ የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ ቀደም ሲል የተደረጉ ጥረቶች ያልተሳኩት ኩባንያዎች ለአገር የሚጠቅም ዕቅድ ይዘው ባለመቅረባቸው እንደሆነ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አጋር ለማፈላለግ የሚያስችለውን ጨረታ ለማውጣት የጨረታ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡ ኩባንያዎች ለአገር የሚጠቅም ዕቅድ ይዘው እስከመጡ ድረስ ግልጽ በሆነ ጨረታ መሳተፍ እንደሚችሉ አቶ ወንድአፍራሽ ገልጸዋል፡፡
የቀንጢቻ ማዕድን ክምችት በቀድሞ የሩሲያ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች በ1980 ዓ.ም. የተገኘ ሲሆን፣ ከታንታለም በተጨማሪ የተለያዩ ማዕድናት በተጓዳኝ ይገኛሉ፡፡ የታንታለም ኮንሰንትሬቱ እስከ 0.5 በመቶ ዩራኒየም ይዘት እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል፡፡ አዲስ የሚገነቡት ፋብሪካዎች ዩራኒየሙን ከታንታለሙ ለይቶ የሚያወጣ ቴክኖሎጂ እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡
የአውስትራሊያ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና የቻይና ኩባንያዎች የማዕድን ልማት ፕሮጀክቱን በጋራ ለማልማት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡