Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መሬት አጥረው ላስቀመጡ የስድስት ወር ማራዘሚያ ተሰጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • 24 የመንግሥት ተቋማት ይገኙበታል

በአዲስ አበባ ከተማ 70 ቦታዎችን አጥረው የያዙ ተቋማት ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› የስድስት ወራት ማራዘሚያ ተደረገላቸው፡፡

እነዚህ ቦታዎች የተያዙት በመንግሥት ድርጅቶች፣ በተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎችና በሚድሮክ ኩባንያዎች ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሠራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቦታዎቹን አጥረው የያዙ ተቋማት ለመጨረሻ ጊዜ የስድስት ወራት ማራዘሚያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

‹‹ተቋማቱ የሊዝ ማሻሻያ ውል እየገቡ ነው፤›› በማለት አቶ ለዓለም አመልክተዋል፡፡ በአዲስ አበባ 156 ይዞታዎች ለዓመታት ታጥረው ተይዘዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ከዚህ ውስጥ 20 የሚሆኑት ቦታዎች ማልማት ያልቻሉት በአስተዳደሩ ችግር ምክንያት በመሆኑ በሕጉ መሠረት ማራዘሚያ ተደርጎላቸዋል፡፡

ስልሳ ስምንት የሚሆኑ ደግሞ ችግሩ የራሳቸው በመሆኑ የመጨረሻ የስድስት ወራት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ ማልማት ያልቻሉት የመንግሥት ተቋማት፣ በተለይ የአፍሪካ አገሮች ኤምባሲዎችና የሚድሮክ ኩባንያዎች ናቸው ተብሏል፡፡

በእነዚህ ሦስት አካላት የተያዙ ይዞታዎች ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የታየ ሲሆን፣ የመጨረሻ የስድስት ወራት ጊዜ እንዲሰጣቸው መወሰኑን፣ ከዚህ በኋላ ግን አስተዳደሩ ትዕግሥቱ እንደተሟጠጠና ወደ እርምጃ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በተደጋጋሚ ይኼንን ጉዳይ በማንሳት ላይ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት በተካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ወ/ሮ አረጋሽ ቸኮል የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹እናለማለን ብለው ቦታውን የያዙት አልሚዎች መቼ ነው የሚያለሙት?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ባለፈው ዓመት 148 ይዞታዎች ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደ አቶ ለዓለም ገልጸዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ሰዎች ሕጋዊ ናቸው፡፡ ውል ተዋውለው ቦታውን በሊዝ ተረክበው ወደ ግንባታ ያልገቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ እርምጃ ተወስዷል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ለዓለም፣ ‹‹በዚህ ዓመት ታጥረው የተቀመጡ 156 ቦታዎችን ለይተናል፡፡ እነዚህ ቦታዎች በጠቅላላ 136.9 ሔክታር መሬት ይሸፍናሉ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

አቶ ለዓለም ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት አልሚዎች ማነጋገር በማስፈለጉ፣ በአሁኑ ወቅት በተለይ ከሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማልማት ካልቻሉ ተቋማት ጋር ውይይት ሲካሄድ ቆይቶ ማራዘሚያ መፈቀዱን አመልክተዋል፡፡

የወሰዱትን መሬት ካላለሙ መካከል 24 የሚሆኑ የመንግሥት ተቋማት ይገኙበታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች