Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ባንክ የፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ብድር ላይ እየተመከረ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ይሰጥ የነበረው ብድር እንዲቋረጥ ተላልፎ የነበረውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ ለማሻሻልና ወደ ቀድሞው አሠራር ለመመለስ እየመከረበት መሆኑ ተገለጸ፡፡ ብድሩ የተቋረጠው ከሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር፡፡

ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ይሰጠው የነበረው ብድር የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውለት ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ አንድ የባንኩ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቶች ሥራ ማስኬጃ ብቻ ብድር እንዲሰጥ ታዞ ነበር፡፡

በንግድ ባንክ ይስተናገዱ የነበሩ የፕሮጀክት ብድሮች ወደ ልማት ባንክ እንዲተላለፉ አድርጎ የነበረው መመርያ፣ ለጊዜው እንዲታገድ መደረጉ ይታወሳል፡፡ የአሁኑ ውሳኔ ሁለቱም ባንኮች ለፕሮጀክትም ሆነ ለሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲሰጡ የሚያስችል እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፕሮጀክት የሚሰጣቸው ብድሮች እንዳይስተናገዱ የተላለፈው ውሳኔ፣ ለተጀመሩ ፕሮጀክቶቻቸው ማስፈጸሚያ የሚውል ብድር ተፈቅዶላቸው ብድሩን ለመውሰድ እየተጠባበቁ የነበሩ በርካታ ተበዳሪዎችን አስተጓጉሎ ነበር፡፡

ከሰሞኑ ግን ይህንን መመርያ ለማስተካከል የሚያስችልና ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ እንዲቻል መግባባት ላይ ተደርሶ፣ አፈጻጸሙን በተመለከተ እየተመከረበት እንደሆነ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሦስት ወራት በፊት ይህንን ውሳኔ ሲወስን ዋነኛ ምክንያት አድርጎ ያስቀመጠው ንግድ ባንክ የሥራ ማስኬጃ ብድር የመስጠት ኃላፊነት እንጂ፣ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆነውን ብድር መስጠት ያለበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደሆነ የተቀመጠ ግልጽ ፖሊሲ አለ የሚል ነበር፡፡

ሆኖም ለፕሮጀክት ፋይናንስ የሚሆን ብድር ከጠየቁ የአንዳንዶች ብድር ተፈቅዶ ስለነበር፣ በዚህ መመርያ መውጣት የተፈቀደላቸው ብድር በመቋረጡና ሥራቸው በመስተጓጎሉ ጥያቄያቸውን ለብሔራዊ ባንክ እስከ ማቅረብ ደርሰው ነበር፡፡

አሁን ሁለቱም ባንኮች እንደ ቀድሞው ተበዳሪዎችን እንዲያስተናግዱ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ የሚደረገው ምክክር ከታመነበት፣ ብሔራዊ ባንክ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ተግባራዊ መሆን እንደሚጀመር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች