Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጣቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብረትነቱ የቻይና ባለሀብቶች በሆነው ፍሬንድሺፕ ታነሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የፋብሪካ ሠራተኞች፣ የተለያዩ የአካል ጉዳቶች እየደረሱባቸው እንደሆነ ተጠቆመ፡፡

በባለፈው ሳምንት በተፈጠረ አደጋ ሞጆ በሚገኘው የቆዳ ፋብሪካ ውስጥ በማሽን አንቀሳቃሽነት የሚሠሩ ሁለት ሠራተኞች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በተለይም አበሩ ንጉሤ የተባሉ ሠራተኛ በአንደኛው እጃቸው ላይ በደረሰው ከፍተኛ አደጋ፣ ኮሪያ ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንደገለጹት፣ በአደጋው ምክንያት አቶ አበሩ የአጥንት መሰበር ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በሞጆ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ይህ የቆዳ ፋብሪካ 1,500 ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡ አብዛኛዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡ በፋብሪካው ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አደጋዎች በመኖራቸው ይህ የመጀመርያ አይደለም ተብሏል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ በአንዲት ሠራተኛ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶ ሁለት እጆቿን ማጣቷን፣ በተጨማሪም በርከት ያሉ ቀላል አደጋዎች በተደጋጋሚ መድረሳቸው ታውቋል፡፡

‹‹ለሠራተኛው ደኅንነት የሚደረገው አናሳ በመሆኑ የተፈጠረ አደጋ ነው፤›› ሲሉ የፋብሪካው ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አታቄ አዶ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከሥራቸው የታገዱት አቶ አታቄ፣ በርካታ በደሎች ፋብሪካው ውስጥ እንደሚፈጸሙና መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

ስለራሳቸው ከሥራ መታገድ ሲገልጹ፣ ያለ ኩባንያው ፈቃድ ለሚዲያ መረጃ ሰጥተሃል ተብሎ ጉዳዩ እስኪጣራ ከሥራ መታገዳቸውን  አስረድተዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ ለእኛም ሪፖርት ተደርጎልን እያየነው ነው፤›› ሲሉ በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የኢንዱስትሪ ሰላምና የማኅበራት ስምምነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ፋብሪካው ከአሁን ቀደም ችግር እንዳለበት እናውቃለን፡፡ እንዲያስተካክልም በተደጋጋሚ ተነግሮት ነበር፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የሠራተኞች ቅጥርን በተመለከተ የሚወቀሰው ኩባንያው፣ አሁን ከአጠቃላይ ሠራተኞች ውስጥ ከ200 የማይበልጡ ብቻ የሥራ ቅጥር ስምምነት ሲኖራቸው ቀሪዎቹ ግን በሠሩት ልክ የሚከፈላቸውና ከኩባንያው ጋር ምንም ዓይነት የሥራ ውል እንደሌላቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡

‹‹ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው፤›› ሲሉ የሞጆ ከተማ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት የተመሠረተው ይህ ፋብሪካ ወደተለያዩ አገሮች ያለቀለት ቆዳዎች ይልካል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሞጆና በአካባቢው ብቻ ወደ 30 የሚሆኑ ፋብሪካዎች ሲኖሩ፣  እስከ 7,000 ሠራተኞች አሉዋቸው፡፡ ካሉት ፋብሪካዎች ግማሽ የማይሞሉት ብቻ የሠራተኛ ማኅበራት ሲኖራቸው፣ ከአጠቃላይ ሠራተኞች ደግሞ 2,390 የሚሆኑት ብቻ ቋሚ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች