ኢትዮጵያ ለዓመታት ከግብፅና ከሱዳን ጋር ያወዛግባት የነበረውን የውኃ ፖለቲካ ክርክር አሸናፊ ሆኖ እንድትወጣ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምክር ቤት የታቀፉ ኤክስፐርቶች እየሠሩ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የውኃ፣ ኤሌክትሪክና መስኖ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡም ሆነ በሌሎች የዓባይ ውኃ ፖለቲካ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ በርካታ ሥራ እያከናወነች ነው፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ አሥራ ስምንት ሰዎችን የያዘው የኤክስፖርቶች ቡድን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ተመድቦለት እየሠራና ሰፊ እውቀት እያካፈለ ነው፡፡ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር በሚኖሩ ክርክሮች ቀድሞ በመተንተን፣ አስፈላጊውን የመነጋገሪያና የመወያያ አጀንዳ በመቅረፅ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ አሸናፊ እንድትሆን እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሦስቱ አገሮች መካከል ያለው የውኃ ፖለቲካ ውይይትና ድርድር በሚቀጥሉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚታሰብም ገልጸዋል፡፡ በሦስቱ አገሮች መካከል የሚደረገው ውይይትና ክርክር የመጀመርያው ጉዳይ ስለግድቡ የውኃ ሙሌት ዘዴ፣ ሁለተኛው ደግሞ ግድቡ በታችኞቹ አገሮች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳድራል በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል፡፡
ጥናቱ ቢጠቃለልም ባይጠቃለልም ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባች ያለችው ጉልህ ጉዳት ሳያስከትል በመሆኑ የግንባታ ሒደቱ እንደማይቋረጥ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይፋ የሚሆነው የጥናት ውጤት ከዚህ የተለየ ነገር ያመጣል ብለን አንጠብቅም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በህዳሴ ግድቡ ዘጠነኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የቀረበው ሪፖርት፣ ከግብፅና ሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለምን እንዳላካተተ ጠይቀዋል፡፡
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የህዳሴ ግድቡ ምክር ቤት አባል አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ በዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎች በጎና የሚያበረታቱ ቢሆንም፣ ከግብፅና ከሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አለመካተቱን ክፍተት ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ቡድኖችን ወደ ግብፅ በመላክ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጥረት ማድረጉን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት በመቅረቱ ግን ቅር እንደተሰኙ ገልጸዋል፡፡
ስማቸውን ያልጠቀሱ ሌላው የምክር ቤት አባል ደግሞ፣ ‹‹ከተለያዩ የሕዝብ አደረጃቶችና የግል ተቋማት የተውጣጣ ቡድን ወደ ግብፅ በመሄድ ከግብፅ ሕዝብና መንግሥት ጋር ጥሩ የሆነ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አድርጎ ተመልሷል፡፡ በዚያን ጊዜም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይኼ የዲፕሎማሲ ቡድን ቋሚ ሆኖ ሁሌም ወደተለያዩ አገሮች በመሄድ፣ የኢትዮጵያን አቋም እንደሚያስረዳ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይኼ ለምን ተቋረጠ?›› በማለት ለምክር ቤቱ ኃላፊዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራና የቢዝነስ ጉዳዮች ኃላፊ አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የምታደርገው የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደፊት ቀጣይነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከእነዚህና ከሌሎች አገሮች ጋር የሚደረገውን የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሕግና በመርህ እንዲመራ ለማድረግ ፖሊሲ ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የፖሊሲው ረቂቅ የተጠናቀቀ በመሆኑ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የሚደረገው የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ሊዘገይ የቻለውም በአንዳንድ ቴክኒካዊ ሥራዎች ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በግንባታ ላይ ያለው የህዳሴ ግድብ በታችኞቹ አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ዓለም አቀፍ የአጥኚዎች ቡድን ጥናት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይኼ ቡድን በአሁኑ ወቅት ጥናቱን ወደማጠቃለያ ምዕራፍ ማድረሱን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ዋነኛ የጥናት ውጤቱንም በአሥራ አምስተኛው ዙር በካይሮ በሚካሄደው የሦስቱ አገሮች ውይይት ላይ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡